1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጅቡቲ ምክር ቤት ፕሬዝደንታዊ ዕጩዎች ላይ የተጣለ የዕድሜ ገደብ እንዲነሳ በድምጽ ደገፈ

እሑድ፣ ጥቅምት 16 2018

የጅቡቲ ምክር ቤት በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ላይ የተጣለው የዕድሜ ገደብ እንዲነሳ የቀረበ የውሳኔ-ሐሳብ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ። ውሳኔው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በሚያዝያ 2018 በሚካሔደው ምርጫ ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመን በድጋሚ እንዲወዳደሩ መንገድ ከፍቷል።

የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ ድምጽ ሲሰጡ ይታያሉ
የጅቡቲ ምክር ቤት በፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ዕድሜ ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ያሳለፈው ውሳኔ ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በሚያዝያ 2018 በሚካሔደው ምርጫ ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመን በድጋሚ እንዲወዳደሩ መንገድ ከፍቷል። ምስል፦ picture alliance/abaca

ጅቡቲ ምክር ቤት በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ላይ የተጣለው የዕድሜ ገደብ እንዲነሳ የቀረበ የውሳኔ-ሐሳብ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ። ውሳኔው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በሚያዝያ 2018 በሚካሔደው ምርጫ ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመን በድጋሚ እንዲወዳደሩ መንገድ ከፍቷል። 

የጅቡቲ ሕገ-መንግሥት ዕድሜው ከ75 ዓመት በላይ የሆነው ግለሰብ ለፕሬዝደንትነት መወዳደር እንደማይችል ይደነግጋል። የሕገ-መንግሥቱ ገደብ በመጪው ሚያዝያ ይካሔዳል ተብሎ በሚጠበው ምርጫ የ77 ዓመቱ ጉሌሕ እንዳይወዳደሩ ያግዳቸዋል።

ይሁንና የዕድሜ ገደቡ እንዲነሳ የቀረበውን የማሻሻያ ውሳኔ 65 አባላት ያሉት የጅቡቲ  ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ እንዳጸደቀ አፈ-ጉባኤ ዲሌይታ ሞሐመድ ዲሌይታ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ በምክር ቤቱ ይኹንታ ያገኘውን ውሳኔ ማጽደቅ አሊያም ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሔድ መጥራት ይኖርባቸዋል። 

ውሳኔው በፕሬዝደንቱ ከጸደቀ ምክር ቤቱ መቀበሉን ለማረጋገጥ በድጋሚ ድምጽ ይሰጥበታል። የጅቡቲ ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ድምጽ የሚሰጠው የዛሬ ሣምንት እሁድ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ ባለፈው ግንቦት ጅቡቲን ለሌላ አምስት ዓመታት ለመምራት በፕሬዝደንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው ነበር። 

ጅቡቲ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ቢኖራትም በቀጠናው ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ሚና ትጫወታለች።ምስል፦ XinHua/picture alliance

በፈረንሳይ በሚገኘው ሊል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪዋ ሶንያ ለ ጉርዬሌ የምክር ቤቱ ውሳኔ “የሚያስገርም” እንዳልሆነ ተናግረዋል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተቃውሞዎች መኖራቸውን የገለጹት ሶንያ ለ ጉርዬሌ “ተቃዋሚዎች በጅቡቲ ራሳቸውን ለመግለጽ የሚያስችል ቦታ አይኖራቸውም” የሚል ሥጋት አላቸው። 

የጅቡቲ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ዲሌይታ ሞሐመድ ዲሌይታ ሶማሊያኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚገኙበት “በችግር በተሞላው የአፍሪካ ቀንድ የትንሺቱን ሀገር መረጋጋት” ለማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያው አስፈላጊ እንደሆነ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ዲሌይታ ሞሐመድ ዲሌይታ “ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ይህን ይደግፋል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ አክለዋል። 

ጉሌህ በሚያዝያ 2013 በተካሔደው ምርጫ ሲያሸንፉ ከተሰጡ ድምጾች ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነውን አግኝተው ነበር። 

ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ የዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይ እና ቻይናን ወታደራዊ የጦር ሠፈሮች የሚገኙባትን ሀገር በጎርጎሮሳዊው ከ1999 ጀምሮ በመምራት ላይ ይገኛሉ። ጉሌህ ሥልጣን የያዙት “የጅቡቲ ነጻነት አባት” የሚባሉት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን በመተካት ነበር። ለ22 ዓመታት የኦፕቲዶን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። 

ጅቡቲ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ቢኖራትም በቀጠናው ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ሚና ትጫወታለች። ሀገሪቱ ከቀይ ባሕር መግቢያ የእስያ እና የምዕራቡ ዓለም የንግድ ልውውጥ አብዛኛው ከሚተላለፍበት ባብ ኤል ማንደብ ሠርጥ አጠገብ ትገኛለች። 

አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW