የጆ ባይደን ከምርጫ ራሳቸዉን ማግለል እና የአፍሪቃዉያን አስተያየት
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20 2016በርካታ አፍሪቃውያን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን በዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ካማላ ሃሪስን የዴሞክራቲክ እጩ አድርገዉ በመተካታቸዉ የተደሰቱ ይመስላል።
ባይደን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ራሳቸውን ማግለላቸዉብዙዎች ብልህ አካሄድ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ምንም እንኳን ባይደን ከምረጡኝ ዘመቻው ብዙ ዘግይተው ለመውጣት መወሰናቸው፤ የተሰነዘሩ አንዳንድ ትችቶች አላጧቸዉም።
ባይደን የምርጫ ውድድሩን የለቀቁት ከራሳቸው ፓርቲ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው እና ፕሬዚዳንቱ ከምርጫ ዉድድሩ ካልወጡ ህዳር ወር በሚካሄደዉ ምርጫ ቦታዉን ለመያዝ ችግር ይገጥማቸዋል እየተባለ በሚነገርበት ጊዜ መሆኑን፤ አስተያየቶችን የሚመረምሩ ምሁራን ተናግረዋል።
አፍሪቃዉያንም በርግጥ የአሜሪካ ምርጫ ብዙም ለዉጥ ባይኖረዉም፣ በርካታ አፍሪቃውያን በአሜሪካ እየተካሄደ ያለዉ የምርጫ ድራማን ለመከታተል ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል። ይሁን እና አፍሪቃ ዉስጥ ለሚገኙ አንዳንድ ሰዎች፣ የአሜሪካ የምርጫ ውድድር ቅርብ እና ወሳኝ ጉዳይም ነዉ። ባለፉት 20 ዓመታት ዋና መኖርያቸዉን ጋና መዲና አክራ ላይ ያደረጉት ፓትሪስያ ዊልኪንስ እንደሚሉት ባይደን አሁን የእረፍ መዉሰጃቸዉ ጊዜያቸዉ ነዉ።
«ጆ ባይደን ለአገራችን ላበረከቱት የረጅም ጊዜ አገልግሎት እና በዲሞክራት ፓርቲ ዉስጥ የትጋት ስራቸዉ በጣም አመሰግናቸዋለሁ። በእርግጥ ሙሉ ጤንነት ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው። እማን አሁን ጤናቸዉን የሚጠብቁበት ጊዜ እንጂ የዓለምን ጭንቀት እና ዉጥረት የሚሸከሙበት ወቅት አይደለም። »
ባለፈዉ እሁድ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በምርጫዉ እንደማይወዳደሩ ካስታወቁ እና ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ምክትላቸዉን ካማላ ሃሪስን መምረጣቸዉን ይፋ ካደረጉ በኃላ፤ ካማላ ሃሪስ የዲሞክራቶች እጩ ሆነዉ ተዘጋጅተዋል ሲሉ ፓትሪሲያ ዊልኪንስ አክለዉ ተናግረዋል። ምናልባትም የመጀመርያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዚዳንት፤ ትዉልደ ካሪቢያን እና የህንድ ዘዉግ ያላቸዉ መሆናቸዉ ለብዙዎች አስደሳች ተስፋን ሰንቋልም።
«ካማላ ሃሪስ እንደ አዲስ እጩ በመምጣትዋ በጣም ደስተኛ ነኝ። ልምዷ፣ ጽናቷ፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት ያላት ቁርጠኝነት ልዩ መሪ ያደርጋታል። ባለፉት ቀናት ይህን ዜና ስሰማ በጣም ነዉ ተደስቼ የሰነበትኩት»
ፓትሪስያ ዊልኪንስ በጋና አነስተኛ እድል ያላቸውን ተማሪዎች የሚደግፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትን ይመራሉ። ፓትሪስያ ካማላ ሀሪስ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያላቸዉ ጉጉት ከዚህ ስራቸዉ ጋር የተያያዘ ነዉ። ፓትሪስያ የሚደግፏቸዉ አንዳንድ ተማሪዎቻቸዉ፤ ካማላ ሃሪስ በቅርቡ አፍሪቃን በጎበኙበት ወቅት አግኝተዋቸዉ ነበር።
በዋይት ሀውስ አዲስ መሪን የማግኘት ተስፋ፤ ቢያንስ ለአንዳንድ አፍሪቃውያን በአገራቸዉ ዉስጥ ስላለዉ አመራር እንዲያስቡ ሊያነሳሳቸዉ ይችላል።
አፍሪቃ የዓለማችን አዛዉንት መሪዎች የሚገኙባት አህጉር ነች። የ91 ዓመቱ የካሜሩን ፕሬዚዳንት ፖል ቢያ፤ የ 81 ዓመቱ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና የ78 ዓመቱ የአልጀርያ ፕሬዚዳንት አብደልማጂድ ቴቦዩን ፤ በጥቂቱ እንደምሳሌ ተጠቃሽ ናቸዉ።
ለአንዳንድ አፍሪቃዉያን የጆ ባይደን ከቦታ መልቀቅ ዋና ምክንያት ዕድሜ ነዉ ይላሉ፤ በጋና መዲና አክራ ነዋሪ የሆነዉ ወጣቱ የዩንቨርስቲ ተማሪ ሲሪል አናኔ ፤ የባይደን እርምጃ ለሌሎች ትምህርት ሊሆን ይችላል ሲል ተስፋ ያደርጋል።
«ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከምርጫ ዉድድሩ መልቀቃቸዉ ትክክለኛ ዉሳኔ ይመስለኛል። ብዙ ነገሮችን እየተሳሳቱ ነበር። ከዶናል ትራምፕ ጋር ያደረጉትም የፉክክር መድረክ አይተናል። ስለዚህ መድረኩን በገዛ ፈቃዳቸዉ ለቀዉ፤ አቅም ያላቸዉን ሰዉ ወደ መድረኩ ማምጣታቸዉ ጥሩ ነዉ። ዳግም መመረጥ የሚፈልጉ የ80 ዓመት አዛውንት አገር ውስጥ እየተዘዋወሩ ዘመቻ ሲያደርጉ ማየት የለብንም። አዛዉንት ሰዉ ሰዉነቱ አልታዘዝ ሲል ፤ ሰዉነቱ እየዘጋ ነዉ። ሰዉነት ሲዘጋ ደግሞ ቤት መቀመጥ ያስፈልጋል።»
በአክራ መዲና ዩንቨርስቲ ተማሪዉ ሲሪል አናኔ ፕሬዚዳንት ባይደን ስልጣን ለቀዉ ትኩስ ኃይል ወደ ቦታዉ ማምጣታቸዉን በማወደስ ይህንን አክለዋል። «መሪዎቻችን ከአንዳንድ ነገሮች እንዲማሩ መገፋፋት እንዳለብን የበለጠ ሊያሳስበን ይገባል። ምክንያቱም መሪነት የብኩርና መብት አይደለም ። ባይደን እንዳደረጉት ሁሉ መሪዎች መቼ ስልጣን ለቀዉ አዲስ ጉልበትን ወደ ቦታዉ ማምጣት እንዳለባቸዉ ማወቅ አለባቸዉ።»
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ ዉድድሩ ውጪ በወጡበት በአሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ጉዳዮች ወደ አሜሪካ ፖሊሲ በግንባር ቀደምነት ሊሸጋገሩ ይችላሉ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሰጡት ናይጀርያዊዉ የማህበራዊ ስራ ፈጣሪ ቶም ክሪስ ኢዉሉ የባይድን የፕሪዚዳንታዊ የክርክር መድረክ አሳሳቢ ነበር ብለዋል።
« የባይደን ከፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ መልቀቅ አንድምታው በጣም ትልቅ ነው። ይህ ማለት በሚቀጥሉት አራት ወራት በሚካሄደዉ ፕሬዚዳንታዊ የፉክክር ዘመቻ ባይደን እና የባይደን አስተዳደር የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች በሰፊው በአፍሪቃ ጉዳዮች ላይ ብዙ ውይይትን ይደረጋል። እናም እንደኔ እምነት በመጭዉ ኅዳር ወር ላይ ካማላ ሃሪስ ፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩን ካሸነፉ በእርግጠኝነት የባይደን አስተዳደር በአህጉሪቱ ላይ ያለውን አንዳንድ ፖሊሲ ለማመቀጠል ይፈልጋሉ።»
በሌላ በኩል የአክራ መዲና ዩንቨርስቲ ተማሪዋ አናኔ፣ በአፍሪቃ ወጣቱ ትውልድ፤ የካማላ ሃሪስን ስራዎች በተሻለ ሁኔታ ከራሱ ጋር ያጣጥማል የሚል እምነት አላት። አንዲት ሴት የዩናይትድ ስቴትስ ዋና አዛዥ የምትሆንበት ጊዜ ተቃርቧል የምትለዉ አናኔ፤ ሴታዊነት አቀንቃኞችም ፤ ቀና ቀና የሚሉበት ጊዜ ይሆናል። እንደ ጋናዊትዋ የዩንቨርስቲ ተማሪ በአሜሪካ አንዲት ሴትን ለትልቅ ስልጣን ማብቃት ለአፍሪቃ ትልቅ የተስፋ መልእክትን የሚያስተላልፍ ይሆናልም።
አዜብ ታደሰ / አይዛክ ካሊጂ
እሸቴ በቀለ