የገቢ አጠቃቀም ተግዳሮት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2017
የገቢ አጠቃቀም ተግዳሮት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዘጠኝ ወራት የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡ የ2017 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፍ የተከናወነው አፈጻጸም ካለፈው ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በግምገማ መድረኩ ላይ ተናግረዋል ፡፡
ያም ሆኖ በወረዳ እና በከተማ አስተዳደሮች የሚሰበሰበው ገቢ አጠቃቀም ያሳሰባቸው መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ “ በወረዳ እና ከተሞች ገቢ ይሰበስባሉ ፡፡ ነገር ግን ጠዋት የተሰበሰበው ገቢ ማታውኑ ለአስተዳደራዊ ወጪ ይውላል ፡፡ ለመስተንግዶ ፣ ለነዳጅ ፣ ለአበል ፣ ለተሽከርካሪ ጥገና ወዘተ …፡፡ በዓመቱ መጨረሻ እስቲ የወረዳችሁን ወጪ ተመልከቱ ፡፡ 20 በመቶ ያህሉ እንኳን ለልማት መዋል የለበትም ወይ ? “ሲሉ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አመራሮችን ጠይቀዋል ፡፡የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች የደመወዝ ጥያቄ
አሠራሩን ዳግም ይጤናል
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመደበኛ ገቢ 6 ቢሊዮን 116 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ የዕቅዱን 89 በመቶ ለማሳካት መቻሉ በግምገማ መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን የሚሰበሰበው ገቢ በታችኛው መዋቅር ላይ የሚተዳደርበትንና ጥቅም ላይ የሚውልበትን አሰራር ዳግም ማጤን እንደሚያስፈልግ ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ ጠቅሰዋል ፡፡ ገቢው ለወረዳዎች እና ለከተማ አስተዳደሮች እንደሚውል የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ “ በቀጣይ ገቢው በዝግ የባንክ ሂሳብ ሳጥን እንዲገባ ይደረጋል ፡፡ እያንዳንዱ የወጪ ርዕስ ግልጽ በሆነና በዞኑ አስተዳዳሪዎች ዕውቅና ብቻ ወረዳዎች እና በሚያቀርቡት ዕቅድ መሠረት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል “ ብለዋል ፡፡ግብር ያልከፈሉ 62 ሰዎች ላይ የጉዞ እገዳ መጣሉ
ሀብት ማስመለስ
ክልሉ በገቢ አጠቃቀም ረገድ ያለውን ድክመት ለይቶ በግልጽ መናገሩ የሚያስመሰግነው መሆኑን ሥማቸውና ድምጻቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉና ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ተናግረዋል ፡፡ በቀጣይም ወጪዎች በዕቅድ ብቻ እንዲከናወኑ የኦዲት ቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመን እና ማጠናከር እንደሚገባም ባለሙያው ጠቁመዋል ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልገቢን ለታለመለት ዓላማ ብቻ ለመጠቀም እየተደረገ ከሚገኘው ጥረት ጎን ለጎን የመንግሥት ሀብት ብክነትን የመከላከል ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ አለአግባብ ሊወጣ የነበረ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ሀብት ወደ ካዝና እንዲመለስ መደረጉን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታመነ ታደሰ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ