1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉበት ጤና እክሎች እና ያሉ መፍትሄዎች

ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2015

ሰው በሕይወት እንዲቆይ ጉበቱ በየዕለቱ ከ500 በላይ ወሳኝ ተግባራትን እንደሚያከናውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል። ፕሮፌሰር ወንድወሰንም ይኽኑን በማጠናከር ጉበትን ሊጎዱ ስለሚችሉ መነሻ ምክንያቶችና ስላለው ህክምና ያብራራሉ።

Symbolbild - menschliche Leber
ምስል Fotolia/ag visuel

የጉበት ጤና እክሎች እና ያሉ መፍትሄዎች

This browser does not support the audio element.

በመላው ዓለም በየዓመቱ አንድ ሚሊየን ገደማ ሰዎች ከሄፒታይተስ ጋር በተገናኙ የጉበት የጤና እክሎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት ይገልጻል። ጉበት ብዙ ሥራ የሚያከናውን እንዲሁም ጥንቃቄ የሚፈልግ በሆድ ውስጥ የሚገኝ ትልቁ ህዋስ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለመሆኑ ጉበት ለጤና እክል የሚጋለጥባቸው መንስኤዎች እንዴት ያሉ ናቸው? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ ጉበት በተለያዩ ነገሮች ይጎዳል ይላሉ።

ስለጉበት ጤና እክል ሲነሳ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡት በተላላፊ በሽታ አምጪ ተሀዋስያን አማካኝነት የሚከሰቱት መሆናቸውን ነው የህክምና ባለሙያው ያመለከቱት። ዶክተር ወንድወሰን ጉበትን በትልቅነቱም ሆነ በውስብስበነቱ በሰውነታችን ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ህዋስ ይሉታል።

የጉበት የጤና አክል በአጭር ጊዜያት ውስጥ ማለትም በስድስት ወራት የሚወገድ እና ከዚህ ጊዜ አልፎ የሚሄደው ደግሞ ዘለቄታዊ ችግር የሚያስከትል እንደሆነ ነው የጤና ባለሙያው ያስረዱት። በህክምናው ሄፕታይተስ የሚባለውና ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት መሰራጨቱ የሚገለጸው የጉበት የጤና እክልን አስመልክተው ዶክተር ወንደወሰን እንዲህ ይላሉ።

«በእኛ ሀገር በተለምዶ የወፍ በሽታ ይባላል፤ ከሌሊት ወፍ ጋር ይያያዛል፤ ግን ምንም የሚያያይዘው ነገር የለውም ሄፕታይተስ የሚባለው። እንግዲህ በእኛም ሀገር ሆነ በዓለም ላይ ሰውን ያጠቃው ሄፕታይተስ ቢ የሚባለው ነው። ሄፕታይተስ ቢ በእኛ ሀገር ላይ ከሰባት እስከ አስር በመቶ የሚሆነው የሀገራችንን ሰው አጥቅቷል።»

ሄፕታይተስ ኤ ተሃዋሲ ምስል imago images/Science Photo Library

በነገራችን ላይ የጉበት ህመም የዕድሜ ገደብ የለውም። ሕጻናትም ሆኑ አዋቂዎች ለዚህ የጤና ችግር የተጋለጡ ናቸው። በተለይ ክትባት እንዳለው የገለጹት ሄፕታይተስ ቢ የተባለው የጉበት ህመም በርካታ የሚተላለፍባቸው መንገዶችን እንዳሉት ነው ዶክተር ወንደወሰን የገለጹት። የጉበት በሽታ ምልክትን በተመለከተም፤ «በዋነኝነት መጀመሪያ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ምግብ ማስጠላት፣ የሚጨሱ ነገሮች ማስጠላት፣ ማስመለስ፤ ቀጥሎ ዓይን ቢጫ መሆን ይጀምራል።» ነው ያሉት። የኩላሊት የጤና ችግር

ዶክተር ወንደወሰን እንደገለጹልን ብዙዎችን የሚያጠቃው ሄፕታይተስ ቢ እንደ ኤችአይቪ ተሀዋሲ ስርጭቱን ለመከላከል ከሚደረግ ጥረት እንዲሁም በእሱ ላለመያዝ አስቀድሞ በሚሰጥ ክትባት መከላከል እንጂ የሚድን አይደለም። ሄፕታይተስ ሲ በተቃራኒው ክትባት ባይኖረውም በአብዛኛው በህክምና ይድናል። ሄፕታይተስ ኤ እና ኢ ግን ጉበት በራሱ በሚያከናውነው ሂደት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሊድኑ የሚችሉ አይነቶች ናቸው። ለሄፕታይተስ ቢ መከላከያ የተከተበ ለሄፕታይተስ ዲ አይጋለጥምም ነው ያሉት ባለሙያው። 

ዶክተር ወንደሰን እንደሚሉት በዛሬ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጉበት የተሻለ ህክምና ማግኘት ይቻላል። ከተዘረዘሩት የሄፒታይተስ አይነቶች ታክመው የሚድኑም አሉ። ከተላላፊው የጉበት የጤና ችግር ባሻገር ሰዎች በራሳቸው በተለያዩ ምክንያቶች አልኮል መጠጥ አዘውትሮ በመጠጣት፣ ያልተረጋገጠ የሀበሻ መድኃኒት፤ በሀኪም ያልታዘዘ መድኃኒት መውሰድ፤ ቅባት መመገብ፣ እንዲሁም ጫት እና ትንባሆ ማጨስን በመሳሰሉት ጉበታቸውን ለችግር እንደሚዳርጉም ነው አጽንኦት የሰጡት። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘን እናመሰግናለን።

 ሸዋየ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW