1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉጅና ጌዲዎ ዞን ተፈናቃዮች ቁጥር በእጥፍ መጨመር

ሐሙስ፣ ሰኔ 14 2010

በምዕራብ ጉጂና ጌድዮ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መድረሱን የተመ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ገለፀ። ቁጥሩ ያሻቀበዉ የአካባቢዉ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ነዉ ብሏል። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው መለዋወጥ የእርዳታ ስራዉን አስቸጋሪ እንዳደረገበት ገልጿል።

Enset-Pflanze in Äthiopien
ምስል DW/J. Breyer

West Guji-Gedeo Conflict Displacement - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

 
በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞንና በደቡብ ክልል ጌዲዎ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች ከሁለት ወራት በፊት በተቀሰቀሰዉ ግጭት ሳቢያ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ሲፈናቀሉ እንደነበር ሲገለፅ ቆይቷል።ይህንን ግጭት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት በምህፃሩ ኦቻ ከሁለቱም ክልሎች  የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 2 መቶ ሽህ መሆኑን ዘግቦ ነበር።ድርጅቱ  በዚህ ሳምንት ባወጣዉ ሌላ ዘገባ ግን ቁጥሩ በእጥፍ መጨመሩንና በጉጅ ዞን ከ170 ሺህ በላይ ሰዎች በጌዲዎ ዞን በኩል ደግሞ ከ520 ሺህ  በላይ ሰዎች ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን ነዉ ያመለከተዉ።የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ አሃዙ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ።«የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳይ ፅ/ቤት ያወጣዉ አሃዝ ከመንግስት ጋር አብሮ የሚሰራ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ቁጥር የተባለዉ ነዉ።በጉጅ በኩል የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ።በጌዲዮ ዞንም የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ።የሁለቱም ድምር ከ አምስት መቶ ሺህ በላይ ነዉ።ሪፖርቱ ላይ የተቀመጠዉ»ብለዋል።

ምስል West Arsi Zone Government Communication Affairs Office

እንደ ኦቻ ዘገባ ባለፈዉ ሚያዚያ በአካባቢዉ የተቀሰቀሰዉ ግጭት አሁንም ድረስ እልባት ባለማግኘቱ  የሚፈናቀሉና  እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ። ድርጅቱ እንደሚለው የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ግጭቱን ለማስቆም ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በምዕራብ ጉጂ ዞን በተለይ በአባያ፣በብርብርሳ ከድዋ ፣ በቡሌ ሆራ፣በገላና እንዲሁም ቀርጫን በመሳሰሉ ወረዳዎች በሰኔ ወር መጀመሪያ አዳዲስ ግጭቶች ተከስተዋል። በግጭቱም  ቤቶች መቃጠላቸዉንና ንብረት መዉደሙን እንዲሁም በርካቶች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸዉን የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል።
በመንግስት እንዲሁም በአካባቢዉ ማህበረሰብና  አመራሮች አማካኝነት እነዚህን ተፈናቃዮች ለመደገፍ ጥረት ኢየተደረገ ቢሆንም ከቁጥራቸው መብዛት አንፃር የሚደረገዉ እርዳታ በቂ ሆኖ አለመገኘቱንም ድርጅቱ ገልጿል።
የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸዉ የሚፈናቀሉ ሰዎችን ለመደገፍ በመንግስት በኩል የአቅርቦት ችግር የለም ባይ ናቸው። ይሁንና  ቁጥሩ የሚለዋወጥና በፍጥነት የሚያሻቅብ በመሆኑ  አስቀድሞ  ለማቀድና  ተጎጅዎቹን በሚፈለገዉ ደረጃ  ለመርዳት አስቸጋሪ መሆኑን ነዉ የገለፁት።« የግጭት እርዳታ አቀራረብና የድርቅ ይለያያል።የድርቅ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የምናቀርበዉ እርዳታ በተጠና አግባብ ሰዎችን ለይተን ነዉ የምናቀርበዉ።»ካሉ በኋላ «ግጭት ግን በባህሪዉ ይለያል።ግጭቱ እስከቀጠለ ድረስ የመፈናቀሉ ሁኔታ  ይጨምራል።» አያይዘዉም «ሪሶርስ ጠፍቶ ሳይሆን የአደጋዉ ባህሪ የፈጠረዉ ችግር ነዉ።»ሲሉ ነዉ የገለፁት።

ምስል West Arsi Zone Government Communication Affairs Office

ሰዎች መፈናቀል እንዲሁም  ንብረት መዉደም መንስኤ የሆነዉን የአካባቢዉን ግጭት ለማስቆም በመንግስት በኩል ምን እየተደረገ እንደሆነ የኦሮሚያንና የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤቶችን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም። 

ሙሉ ዘገባዉን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW