የጊምቢ ወረዳ መምህራን ቅሬታ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 29 2017
በጊምቢ ወረዳ ለአራት ወራት የዕድገት ደረጃ ክፍያ አለማግኘታቸውን መምህራን ተናገሩ፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በተለያዩ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን በጥር ወር ይከፈላል የተባለውን የደረጃ ዕድገት ክፍያ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለመምህራን የሚከፈለውን የዕድገት ክፍያ ለአራት ወራት ያህል በተደጋጋሚ የትምህርት ጽ/ቤት ቢያመለክቱም ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን ያነጋገርናቸው መምህራን አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም ያለስምምነት ከደመወዛቸው ገንዘብ በተለያዩ ወቅቶች እንደሚቆረጥ አስረድተዋል፡፡ ለመምህራን የዕድገት ክፍያ 2 ዓመት ካለገሉ በኃላ የሚሰጥ ነው፡፡
በጊምቢ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ3 ዓመታት ማስተማራቸውን የነገሩንና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ መምህር በወረዳው በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ 150 የሚደርሱ መምህራን የደረጃ ዕድገት ክፍያውን ለአራት ወራት እንዳላገኙ አመልክተዋል፡፡ በሌሎች ወረዳዎች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለሚሰሩ መምህራን ክፍያው ከተፈጸመ 3 ወራት እንደሆነው በመግለጽ በቅርቡ ደግሞ ያለፈቃዳቸው ከደመወዛቸው የተለያዩ ክፍያዎቸ እየተቀነሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያልተፈታው የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ
‹‹ አንደኛው ቅሬታችን ያለፈቃዳችን እና ጥያቄ ደመወዛችን መቆረጥ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜ ይቆረጣል፣ለምን እንደሚቆረጥ አናውቅም፡፡ ሌላው ደግሞ ለደረጃ ዕድገት የሚከፈል ገንዘብ ባለፉት አራት ወራት አላገኘንም፡፡ ትናንት ደግመን ጠይቀን ነበር፤ ብር የለም ፋይናንስ ብር የለውም ነው የተባል ነው፡፡ ሌሎች ወረዳዎችን ሲንጠይቅ ደግሞ እንደ ነጆ ያሉት ወረዳዎች ከተከፈላቸው 3 ወራት ሆነዋል፡፡ ››
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ያነጋገርናቸው ሌላው የ8ኛ ክፍል መምህር መሆናቸው የነገሩት መምህር በተመሳሳይ ካላቸው አነስተኛ ደመወዝ ያለፈቃዳቸው ገንዘብ እንደሚቆረጥባቸው በመግለጽ ባለፉት አራት ወራት ይሰጣቸዋል የተባለው ዕድገት ክፍያን አለማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡ ለመምህራን ሁለት ዓመት ካገለገሉ በኀላ የዕድገት ክፍያ ይሰጣቸዋል የሚል ሕግ የተቀመጠ ቢሆንም ለወራት ሳይሰጣቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹ እንደ ጊምቢ ወረዳ እስካሁን የደረጃ ዕድገት ክፍያ አላገኘንም፡፡ ኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ለመምህራን ቤት በማህበር ይሰጣል ተብሎም ነበር እሱም አልተገኘም፡፡ ሌላው ደግሞ ደመወዝ ለአንድ አንድ ነገር እንድንቆርጥ እንገደዳለን፣ ፈቃደኛ ያልሆነን ማስፈራሪያም ይደርስበታል፡፡››
‹‹ክፍያው የተጓተተው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ነው››
በወላይታ ዞን የመምህራን ደሞዝ አሁንም አልተከፈለም ፤ ትምህርትም አልተጀመረም
የጊምቢ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት በመምህራን ቅሬታ ላይ በሰጠን ማብራሪያ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከፍያው ሳይሰጣቸው መቆየቱን አረጋግጠዋል፡፡ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢታና ማሞ በመምህራን የተነሱ ያለፈቃዳቸው ለተለያዩ ጉዳዮች ደመወዝ ይቆረጥብናል ተብሎ የቀረበውን ቅሬታ አስተባብለዋል፡፡
‹‹በገንዘብ እጥረት ምክንያት ፋይናንስ ሳይከፍል ቆይቷል፡፡ በፊት ላይ አዲስ ከመጣው አደረጃጀት ጋር በአንድ ላይ ስለመጣ ነው ወደኃላ የቀረው፤አዲሱ አደረጃጀቱ ሲሰራ ከእሱ ጋር ተያይዞ የበጀት እጥረት አጋጥሟል፡፡ በዚሁ ምክንያት ነው የተጓተተው ነገር ግን አሁን የፋይናንስ ቢሮው ክፍያውን ሰርቶ ልኳል፡፡ እንደ አጠቃላይ የተደረገው ደመወዝ ጭማሪ በወረዳ ገንዘብ ላይ ጫና አሳድረዋል››
የምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ 48 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ወረዳዋ የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር ዋና መቀመጫ ናት፡፡ በዚህ ወረዳ ከ150 በላይ የሚሆኑ መምህራን ለደረጃ ዕድገት ክፍያ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ