1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጊኒ ቢሳው ወታደራዊ ኽንታ ጀነራል ሆርታ ንታምን በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት ሰየመ

ሐሙስ፣ ኅዳር 18 2018

በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም እንጂ ፌርናንዶ ድያስ ትናንት ከመሸ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተናግረው የትናንቱ መፈንቅለ መንግሥት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሽንፈታቸውን ላለመቀበል የፈጠሩት መላ ነው ሲሉ ከሰዋል። መፈንቅለ መንግሥቱንም የተፈበረከ ብለውታል።

የጊኒ ቢሳው ወታደራዊ ኽንታ በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት የሰየማቸው ጀነራል ሆርታ ንታምን ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ
የጊኒ ቢሳው ወታደራዊ ኽንታ በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት የሰየማቸው ጀነራል ሆርታ ንታምን ቃለ መሀላ ሲፈጽሙምስል፦ Patrick Meinhardt/AFP

የጊኒ ቢሳው ወታደራዊ ኽንታ ጀነራል ሆርታ ንታም በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት ሰየመ

This browser does not support the audio element.


የጊኒቢሳው የጦር መኮንኖች የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢንባሎን ከስልጣን አስወግደው የሀገሪቱን የመንግሥትነት ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ያሳወቁት ትናንት በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ነበር ። ራሳቸውን «ስርዓት አስከባሪ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት እዝ » ሲሉ የጠሩት እነዚሁ የጦር መኮንኖቹ በዚሁ መግለጫቸው የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ለማውረድ፣ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን አስታውቀዋል።

« ብሔራዊ እና ህዝባዊ ስርዓት መልሶ እንዲሰፍን የሚሰራው ከፍተኛ ወታደራዊ እዝ፣ የጊኒ ቢሳው ሪፐብሊክ የሀገሪቱን የመንግሥትነት ሥልጣን ተቆጣጥሯል። ዓላማው የሀገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት እና ማኅበራዊ ሰላም ማስጠበቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ለጊኒቢሳውን ድንበሮች ዋስትና እንሰጣለን  እንከላከላለንም። ከፍተኛ ወታደራዊ እዙ በሀገራችን የህዝብን ስርዓት ለማዳከም በሚጥሩ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ለሚደገፍ በሀገሪቱ ለሚገኙ የተለያዩ ፖለቲከኞች ሚስጥራዊ እቅድ ምላሽ እየሰጠ ነው። »  

እዙ ትናንት በአስቸኳይ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንትን  ለማውረድ፣ የሪፐብሊክ ተቋማትን በሙሉ ፣የመገናኛ ብዙሀንን እንቅስቃሴን ጨምሮ የምርጫ ሂደቱንም ለማገድ እና የሀገሪቱን የየብስ የባህርና የብሔራዊ የአየር ክልል ለመዝጋት መወሰኑንም ጨምሮ አስታታውቋል። የጦር ኃይል መኮንኖቹፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ማውረዳቸውን እንዳሳወቁ ብዙም ሳይቆይ ነበር ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢንባሎ ከስልጣን መወገዳቸውን ያረጋገጡት። መፈንቅለ መንግሥቱ የተካሄደው ምርጫ በተደረገ በሦስተኛው ቀን ማለትም የምርጫው ጊዜያዊ ውጤት ሊነገር ከታቀደበት ከአንድ ቀን በፊት መሆኑ ነው።  ዋነኛዎቹ ተፎካካሪዎችም ፕሬዝዳንት ኤምባሎና  በቅርቡ የፖለቲካውን መድረክ የተቀላቀሉት ተቀናቃኛቸው የ47 ዓመቱ ፌርናንዶ ድያስ ነበሩ።

 

በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተወገዱት የጊኒ ቢሳው ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኤምባሎምስል፦ Michel Euler/AP Photo/dpa/picture alliance

በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም እንጂ ፌርናንዶ ድያስ ትናንት ከመሸ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተናግረው የትናንቱ መፈንቅለ መንግስት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሽንፈታቸውን ላለመቀበል የፈጠሩት መላ ነው ሲሉ ከሰዋል። መፈንቅለ መንግስቱንም የተፈበረከ ብለውታል። «በድጋሚ በቀላሉ ላሳውቃችሁ የምፈልገው እኛ የተፈበረከ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰለባዎች ነን። እኔ የምርጫው አሸናፊ ነኝ ድሌን የሚያረጋግጡ የምርጫ ጣቢያዎች ሪፖርቶች አሉኝ። ምርጫውን አሸንፌያለሁ። »

የጊኒ ቢሳው ፕሬዝዳንት ኤምባሎና ተቀናቃኝ የ47 ዓመቱ ፌርናንዶ ድያስ ድምጽ ሲሰጡምስል፦ Samba Balde/AFP/Getty Images

ፌርናንዶ ድያስ አሸንፌያለሁ ቢሉም መፈንቅለ መንግስቱን ያካሄዱት የጦር መኮንኖች ዛሬ ጀነራል ሆርታ ንታም በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሀላ መፈጸማቸውን አስታውቀዋል። በመንግስታዊ ቴሌቪዥን እንደታየው ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱት ንታና፣ ሌሎች ወታደራዊ ባለሥልጣናት በተገኙበት ነው ቃለ መሀላ የፈጸሙት። ጦሩ ንታም ለአንድ ዓመት በስልጣን ላይ እንደሚቆዩ መናገሩን ራድዮ ፍራንስ ኢንተ ርናሽናል ዘግቧል። 

የጊኒቢሳው ዋና ከተማ ቢሳው ዛሬ በአመዛኙ ፀጥታ ስፍኖባታል። በጎዳናዎች ላይ ወታደሮች ሲዘዋወሩ ይታያል። ምስል፦ Patrick Meinhardt/AFP

የአፍሪቃ ኅብረት መፈንቅለ መንግሥቱን ተቃውሞ ባወጣው መግለጫ  የጊኒ ቢሳው ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ እና ሌሎችም የታሰሩ ባለሥልጣናት በአስቸኳይና ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። የኅብረቱ ሊቀ መንበር ሞሀመድ አሊ ዩሱፍ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኅብረቱ መፈንቅለ መንግሥቱን ማውገዙንም ጽፈዋል። 
የጊኒቢሳው ዋና ከተማ ቢሳው ዛሬ በአመዛኙ ፀጥታ ስፍኖባታል። በጎዳናዎች ላይ ወታደሮች ሲዘዋወሩ ይታያል። ለሊቱን የተጣለው ሰዓት እላፊ ዛሬ ቢነሳም በርካታ ነዋሪዎች ግን ከቤታቸው አልወጡም። መደብሮችና ባንኮችም እንደተዘጉ ነው።  

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW