የጋምቤላ ነዋሪዎች የኮሮና ሥርጭት ስጋት
ዓርብ፣ ግንቦት 21 2012
ከአጎራባች ደቡብ ሱዳን የሚገቡ ስደተኞች ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት እንደሆኑባቸው የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ፣ የክልሉ መንግስት ከ 4ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፓጋክ በተባለ ቦታ ላይ መስፈራቸውን አስታውቋል፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተደዳደር ግን ስለጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም ብሏል፡፡ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ከአጎራባች ደቡብ ሱዳን ደንበር አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞች ለክልሉ ነዋሪ የኮሮና ቫይረስ ዋናው ስጋት እንደሆኑባቸው፣ እንዲሁም የክልሉ የህብረተሰብ አስቸኳይ አዋጁን ከመፈፀም አንፃር ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ ነው የሚናገሩት፡፡የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ኡጁሉ ኡጁሉ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ 8 የጋምቤላ ወረዳዎች ከደቡብ ሱዳን እንደሚዋሰኑና በደቡብ ሱዳን በሚደረጉ ግጭቶች በየጊዜው በርካታ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ አሁንም ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ከደቡብ ሱዳን ተፈናቅለው ፓጋክ በተባለ የጠረፍ አካባቢው እንደሚገኙና ለክልሉ የኮሮና ስርጭት ስጋት መሆናቸውን አመልክተዋል።
በክልሉ የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የግንዛቤ እጥረት አለ በተባለው ላይ ደ/ር ኡጁሉ በሰጡት ማብራሪያ ˝በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል˝ ነው ያሉት:: ሰዎቹን ስደተኛ ናቸው ወይስ አይደሉም ብሎ ለመወሰን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ድንበር በተዘጋበት ወቅት የገቡ በመሁኑ ያን የመወሰን ኃላፊነት የክልሉ መንግስት ነው ብለዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊና የጠረፍ አካባቢ የፀጥታ ግብረኃይል ሰብሳቢ አቶ ኡቶው ኡኮት እንዳሉት ስደተኞቹን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተደዳደር (Administration for Refugees and Returnees Affairs-ARRA) የሚቀበል ከሆነ በኃላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የደረጋል ነው ያሉት፡፡ ይህንንም እየተነጋገሩበት እንደሆነና ይግቡ ከተባለም ተመርምረው የሚገቡ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተደዳደር የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየት ለመስጠት ኃላፊነት እንደሌለበት ጠቅሷል፡፡የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተደዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያሲን አሊ ስለጉዳዩ እንደማያውቁና የተባሉት ሰዎች ስደተኛ ስለመሆናቸውም ማረጋገጫ እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡በጋምቤላ ክልል ከ300 ሺህ በላይ የሱዳን ስደተኞች በ7 የተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች ይገኛሉ፡፡
አለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ