የጋምቤላ ክልልና የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ንግግር
ሰኞ፣ የካቲት 27 2015
ከደቡብ ሱዳን እየተሸገሩ በምዕራብ ኢትዮዮያ ጋምቤላ ክልል ውስጥ ጥቃት የሚፈፅሙ የሙርሌ ታጣቂዎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል ውይይት መካሄዱን የጋምቤላ ክልል መንግስት አስታወቀ ።ውይይቱ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ክልል ባለስልጣናት መካከል መደረጉን ክልሉ ለዶቼቬለ ተናግሯል። ቀጣይ ውይት በኢትዮጵያ እንደሚካሄድም ገልጿል።
የጋምቤላ ክልል መንግስት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀው ከደቡብ ሱዳን የሚሻገሩ ታጣቂዎች ወደ ክልሉ በመዝለቅ ግድያ ይፈፅማሉ፣ እንስሳትን ይዘርፋሉ ህፃናትንም አፍነው ይስዳሉ፣ በተለይ ሙርሌ የተባሉ የጎሳው አባላት ድርጊቱን እንደሚፈጽሙ ነው የጋምቤላ ክልል መንግስት ያስታወቀው፡፡
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል የተባለ ውይይት በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ክልል ባለስልጣናት መካከል ሰሞኑን ደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ውስጥ መካሄዱን በውይይቱ ላይ የተካፈሉት የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት አመልክተዋል፡፡
“ከእኛ የሚዋሰኑ ሶስት ግዛቶች አሉ፣ የላይኛው ናል፣ ጆንግሌና ታላቁ ፒቦር ግዛት፤ ሶስቱም ግዛቶች የምንጋራቸው የፀትታ ችግሮች አሉ፣ በተለይ ከታላቁ የፒቦር አስተዳደር ህገወጥ የታጠቁ የሙርሌ ታጣቂዎች በየጊዜው የሚያደርሱትን ጥቃት በማስመልከት ከአመራሮቹ ጋር ተነጋግረን የከብት ዝርፊያ፣ የህፃናት አፈናንና ግድያዎች በሚቀሩበት ሁኔታ ተወያይተናል፡፡”
ድንበር ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ለመከላከልና ደቡብ ሱዳናውያንም አንዳንድ ህገወጥ ታጣቂዎችን በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር ችግሮች እንዲወገዱ ውይይት መደረጉን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በውይይቱ የተሳተፉ ሲሆን፣ የጋምቤላ ክልል አዋሳኝ የሆኑት በደቡብ ሱዳን የላይኛው ናይል፣ የጆንግሌና የፒቦር ግዛቶች አስተዳዳሪዎችና ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
”በኢትዮጵያ በኩል የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በደቡብ ሱዳን በኩል ደግሞ፣ የየግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ፣ የፋይናንስ ኀሻላፊዎች፣ የፀጥታ አማካሪዎች ተገኝተዋል“ ነው ያሉት፡፡
በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የእንስሳት ዝርፊያ፣ የህፃናት ስርቆትና የግድያ ወንጀሎችን ለማስቆም ደቡብ ሱዳናውያን በውይይቱ ወቅት ፍላጎት ማሳየታቸውን የተናገሩት አቶ ኡቶው፣ በቀጣይ ውይይቶች በኢትዮጵያ እንደሚደረጉም ቀጠሮ መያዙን አስረድተዋል፡፡
“ደቡብ ሱዳናውያን ችግሮችን ለመፍታት ፍላጎት አላቸው፣ በኢትዮጵያ በኩል እንዲስተካከል የጠየቋቸው ጥቃቅን ነገሮች አሉ፣ ይሁን እንጂ ደንበር እየተሸገሩ ጥቃት የሚያደርሱ እነርሱ ናቸው፣ ቀጣይ ውይት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲደረግ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ይመቻቻል” ብለዋል፡፡
እ ኤ አ March 2/2023 በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ የተካሄደውን ውይይት ያዘጋጀው በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኢምባሲ መሆኑም ታውቋል፡
ከደቡብ ሱዳን የሚሻገሩ የተባሉ የሙርሌ ጎሳ አባላት በተደጋጋሚ ወደ ጋምቤላ ክልል በመዝለቅ በኑዌርና አኙዋ ዞኖች የእንሳሳትና የህጻናት ስርቆት እንደሚፈፅሙ፣ እንዲሁም ሰዎችን እንደሚገድሉ በተደጋጋሚ መገለፁ ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ