1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተቃዉሞና ወቀሳ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2015

የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ጋዴፓ / በአዲሱ ክልል ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው የክላስተር አደረጃጀት ላይ ያለውን ተቃውሞ በሰላማዊ ሰልፍ ለማሰማት ቢጠየቅም ጥያቄው በዞኑ አስተዳደር መከልከሉን የፓርቲው አመራሮች ገልጸዋል ፡፡ ይልቁንም ይህን አቋም ያራምዳሉ የሚባሉ ወጣቶች አሁን ላይ በዞን የፀጥታ አባላት እሥርና ወከባ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ

የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ጋዴፓ መሪዎች መግለጫ ሲሰጡ።«አዲሱን አደረጃጀት የተቃወሙ ታስረዋል» ይላሉ
የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ጋዴፓ መሪዎች መግለጫ ሲሰጡ።«አዲሱን አደረጃጀት የተቃወሙ ታስረዋል» ይላሉምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዲሱን የክላስተር አደረጃጀት ተቃወመ

This browser does not support the audio element.

ጋዴፓ በክልል አደረጃጀቱ ላይ ምን አለ  ?
የደቡብ አካል ሆነው የቆዩት ቀሪ 11 ዞኖችና 6 ልዩ ወረዳዎች የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል ባለፈው ቅዳሜ በይፋ ምሥረታቸውን አካሂደዋል ፡፡ የክልሎቹን መዋቀር ተከትሎ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ደግሞ የከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ከአስፈጻሚ ቢሮዎች የክላስተር ድልድል ጋር በተያያዘ ቅሬታዎችን እያነሱ ይገኛሉ፡፡
የጋሞ ዞንን ጨምሮ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎችን የካተተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት መቀመጫውን በወላይታ ሶዶ ከተማ አድርጓል፡፡ ክልሉ የአስፈጻሚ ቢሮዎችና ተቋማት ግን አገልግሎታቸውን በተለያዩ የዞን ከተሞች ውስጥ ሆነው እንዲያከናውኑ በክላስተር ደልድሏል ፡፡ የክላስተር አደረጃጀቱ የከተሞችን የልማት ተጠቃሚነት ፍትሃዊ ለማድረግ በማሰብ የተከናወነ እንደሆነ  የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡
የጋዴፓ የክላስተር ተቃውሞ
በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተካሄደው የክላስተር አደረጃጀት ላይ ተቃውሞ እንዳለው የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋዴፓ አስታውቋል ፡፡ የፓርቲው አመራሮች በሀዋሳ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የአስፈጻሚ ተቋማት የክላስተር አደረጃጀት የጋሞ ህዝብ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አይደለም ”  ብለዋል ፡፡ አመራሮች የክላስተር አደረጃጀቱ ተገልጋዩን ማህበረሰብ የሚጎዳ ነው ሲሉም ተቃውመዋል  ፡፡
የዞኑ ህዝብ ጥያቄ ክላስተር ሳይሆን አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል የማግኘት ጉዳይ መሆኑን  የጠቀሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቡነካሶ ሀንጌ  “ አሁን ላይ የዞኑ ማህበረሰብ የአስፈጻሚ ተቋማት በተለያዩ ከተሞች መበታተን አገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብንም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛውን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነው ፡፡ በተለይም ተገልጋዩ ለአንድ ጉዳይ ዲላ ለሌላ ጉዳይ ደግሞ ጂንካ ከተሞች ድረስ አንዲጓዝ በማድረግ አንግልትን ይፈጥርበታል፡፡ የጋሞ ህዝብ የክልል መዋቅር ሲጠይቅ የነበረው በቅርበት በአንድ ማዕከል በመገልገል ይህን መሰሉን መጉላላት ለማስቀረት ነበር ፡፡ ነገር ግን መንግሥት የፖለቲካ ድርጅት አቅጣጫ ነው በሚል የህዝቡን ጥያቄ ሳይመልስ ቀርቷል “ ብለዋል ፡፡
እሥርና ወከባ 
የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ጋዴፓ / በአዲሱ ክልል ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው የክላስተር አደረጃጀት ላይ ያለውን ተቃውሞ በሰላማዊ ሰልፍ ለማሰማት ቢጠየቅም ጥያቄው በዞኑ አስተዳደር መከልከሉን የፓርቲው አመራሮች ገልጸዋል ፡፡ ይልቁንም ይህን አቋም ያራምዳሉ የሚባሉ ወጣቶች አሁን ላይ በዞን የፀጥታ አባላት እሥርና ወከባ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ የተናገሩት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቡነካሶ ሀንጌ  “ ከቀናት በፊት እኔን  ጨምሮ 60 የምንሆን ሰዎች በአርባምንጭና በተለያዩ የወረዳ ከተሞች ውስጥ ለሁለት ቀናት አሥረው ለቀውናል ፡፡ የታሠርንበትንም ሆነ የተለቀቅንበትን ምክንያት እንኳን የገለጸልን አካል አላገኘንም ፡፡ አሁንም ክላስተሩን አይደግፉም በሚሏቸው ወጣቶች ላይ እሥርና ወከባው ቀጥሏል “ ብለዋል ፡፡
‹‹ ››
የዞኑ አስተዳደር ምላሽ
የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ጋዴፓ / ባቀረበው አቤቱታ ላይ ምላሽ የሠጠው የጋሞ ዞን አስተዳደር የፓርቲውን ቅሬታ መሠረተቢስ በማለት አጣጥሎታል፡፡ በተለይም ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው የዞኑ የመንግሥት ኮሚኒዩኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ኤደን ንጉሴ  “የክላስተር አደራጃጀቱን በመቃወማቸው ምክንያት የታሠሩ ሰዎች የሉም “ ብለዋል ፡፡ ነገር ግን ከሦስት ቀናት በፊት 15 የሚሆኑ ወጣቶች አርባምንጭ ከተማ ውስጥ በሌሊት ጎማ በማቃጠልና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ድንጋይ በመወርወር ከተማውን ለመረበሽ ሲሞክሩ በፀጥታ አባላት ተይዘዋል ፡፡ ኋላ ላይ ግን የወጣቶቹን ቤተሰቦች በመጥራትና እንዲመክሯቸው በማሳሰብ ሁሉም እንዲለቀቁ ተደርጓል “ ብለዋል ፡፡
የፓርቲው አባላት ደረሰብን ባሉት ወከባና በሰላማዊ ሠልፍ ክልከላ ዙሪያ ከዶቼ ቬለ DW ተጨማሪ ጥያቄ የቀረበላቸው የኮሚኒዩኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊዋ “ በዞኑ አንድም የታሠረ የፓርቲው አመራርም ሆነ አባል የለም ፡፡ ባለመታሰራቸው መሰለኝ በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ከተሞች በመዘዋወር ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እየሠጡ የሚገኙት “ ብለዋል ፡፡
የሰላማዊ ሠልፍ ክልከላን በተመለከተ ቅሬታቸው እውነት መሆኑን  ያረጋገጡት ሃላፊዋ “ ይህም በክልሉ ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ምንም አይነት የአደባባይ ሰልፎች እንደማይፈቀዱ ከክልሉ መንግሥት ፀጥታ ተቋማት በወረደው መመሪያ መሠረት የተፈፀመ ነው “ ብለዋል ፡፡

ቡንካሶ ሐንገ፣ የጋዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
የጋዴፓ አርማ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW