1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋና የህክምና ባለሙያዎች ስደት

ቅዳሜ፣ የካቲት 18 2015

የጋና ነርሶች የተሻለ የሥራ ሁኔታ ፍለጋ እየተሰደዱ ነው። ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ 3,000 የሰለጠኑ ነርሶች ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሀገር ለቅቀው ሄደዋል። አብዛኞቹ ሙያተኛ ነርሶች የወር ደመወዛቸው ከ300 ዩሮ ያነሰ ነው።

Ghana Accra | 37 Militärkrankenhaus: Nana Akufo-Addo wird geimpft
ምስል Information ministry of Ghana

«የህክምና ባለሙያዎች ስደት የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት አዳክሟል»

This browser does not support the audio element.

ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጋና የሰለጠኑ ባለሙያ ነርሶቿ ወደ ሌሎች ሃገራት እየተሰደዱባት የህክምና ባለሙያዎች እጥረት አጋጥሟታል። እንደ ጀርመን እና ብሪታንያ ያሉት ሃገራት ለአስታማሚ ነርሶች ጠቀም ያለ ደሞዝ እንደሚሰጡ በመግለጽ ባለሙያዎችን ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ትችትን አስከትሏል። የዓለም የነርሶች ኮንፌደሬሽን ከድሀ ሃገራት የጤና ባለሙያዎች ለማማለል የሚደረገው እንቅስቃሴ የህክምና ባለሙያዎቹ መገኛ በሆኑት ሃገራት የጤና ሥርዓት ላይ ችግር እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል። 

አክራ ጋና ውስጥ በሚገኝ አንድ ሀኪም ቤት የ28 ዓመቷ ጆሴፊን ለአንዲት አሁን ለወለደች እናት መድኃት በመስጠት ላይ ናት። በመጀመሪያ ስሟ ብቻ እንድትጠራ የመረጠችው ጆሴፊን በነርስነት ሙያ መሥራት ከጀመረች ገና ሁለት ዓመት ሞላት። እንደሌሎች ባልደረቦቿ እሷም የተዳከመውን የሀገሯን የጤና ዘርፍ ለመደገፍ ነው በዚህ ሥራ የተሠማራችው። በተጠሩ አካባቢ በተለይ የህክምና ተቋማት እጥረት እንዳለ አስተውላለች። 

«ህክምና ለማግኘት ወደ ሌላ ከተማ መጓዝ ግድ ነው፤ እናም ነርስ ብሆን ማኅበረሰቤን መርዳት እችላለሁ፤ በዚህም ቤተሰቦችንም እደግፋለሁ እያልኩ አስባለሁ።»

አሁን ግን ጆሴፊን ወደ ብሪታኒያ ሄዳ ለመሥራት ትፈልጋለች። እዚያ አብዛኞቹ ጓደኞቿ ሀኪም ቤት ውስጥ በመሥራት ላይ በመሆናቸው፤ ቅር እያላትም ቢሆን ለመጓዝ አመልክታለች። 

«የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ነበሩ፤ አንዳንዶቹ አሁን ከሀገር ውጪ ናቸው፤ ከእኔ ገቢ ጋር ሲነጻጸር በጣም ብዙ ያገኛሉ። በተሻለ ሥርዓት ውስጥ ለመኖር ዕድሉ ስላላቸው ብቻ በጥሩ ሁኔታ ይኖራሉ። እዚህ ጋና ውስጥ ግን እንደዚያ አይደለም። በጣም ያሳዝናል። ልብን ይሰብራል።»

የጋና ነርሶች የተሻለ የሥራ ሁኔታ ፍለጋ እየተሰደዱ ነው። ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ 3,000 የሰለጠኑ ነርሶች ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሀገር ለቅቀው ሄደዋል። አብዛኞቹ ሙያተኛ ነርሶች የወር ደመወዛቸው ከ300 ዩሮ ያነሰ ነው። የጋና የነርሶች እና አዋላጆች ማኅበር እንደሚለው በሚከፈላቸው ዝቅተኛ ገቢ ምክንያት ነው ባለሙያዎቹ አስታማሚዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ አውስራሊያ እና ሌሎች ሃገራት የሚሰደዱት። የማኅበሩ ፕሬዝደንት ፔርፔቹዋል ኦፎሪ አምፖፎ አስታማሚ ነርሶችን የሚያማልሉት ሃገራት ልምድ ያላቸው ላይ እንደሚያተኩሩ ይናገራሉ። 

ምስል Monika Hoegen

«በሚሰጠው አገልግሎት ላይ በትክክል ተጽዕኖ አለው፤ የመረጃ መዘርዝሩን ስንመለከት ከከፍተኛ ባለሙያዎች ይልቅ ረዳት ነርሶች ናቸው ያሉን። የሰለጠኑት ባለሙያዎች ናቸው ይህችን ሀገር ትተው በመሄድ ላይ ያሉት ምክንያቱም እነዚህ ሃገራት ከረዳት ነርሶች ይልቅ የሚፈልጉት እነሱን ነው።»

ብሪታንያ የሰለጠኑ ነርሶችን ቀጥራ ለመውሰድ ከጋና መንግሥት ጋር ባደረገችው ውል በአንድ ነርስ 1,000 ፓውንድ ለመክፈል ተዋውላለች። ምንም እንኳን ገንዘቡ የተዳከመውን የጋናን የጤና ዘርፍ ለማጠናከር ይውላል ቢባልም፤ የጤና ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ናና ኮፊ እንዲህ ያለው ስምምነት የሀገራቸውን የጤና አገልግሎት ሊያስተጓጉል ይችላል ባይ ናቸው።

«ይህ በመሠረታዊነት በሀገር ውስጥ ላለው የጤና ሥርዓት ምን ማለት ነው? ያ ማለት ያለውን አቅም ለመጠቀም መታገል ነው የሚሆነው። በጤናው አገልግሎት ሁሉንም የሚያዳርስ የጤና ባለሙያዎችን ለማስልጠን እና ለማከፋፈል የሚያደርገው ትግልም ይቀጥላል።»  

የህክምና ባለሙያዎቹ በብዛት መሰደድ ያሳሰበው የጋና መንግሥት እገዳ ለመጣል እያሰበ ቢሆን የጋና የነርሶች እና አዋላጆች ማኅበር ግን ፍልሰት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ነው በሚል እገዳውን እንደማይደግፍ አስታውቋል። የዓለም የጤና ድርጅት ግን በባለሙያ እጥረት የተዳከመውን የጤና ዘርፍ በመመልከት አቅም ያላቸው ሃገራት የህክምና ባለሙያዎችን እንዳይመለምሉ ማሳሰቢያ ከሰጠባቸው ሃገራት አንዷ ጋና ናት።

 ሸዋዬ ለገሠ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW