1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዛዉ ጦርነትና ፋታዉ

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2005

አታካቹ፥ አሳዛኙ የእልቂት ፍጅት ዑደት አንድ ምዕራፍ ዘለለ። ከተለመደዉ፥ አሰልቺ ዲፕሎማሲ ልመና ተማፅኖ በሕዋላ የተለመደዉ ጦርነት፥ በተለመደዉ ተኩስ አቁም-መተካቱ ታወጀ። ሮብ።አሰልቺ፥ አስጊዉ ዉዝግብ ግን ቀጥሏል።ምናልባት እስከሚቀጥለዉ ጦርነት-እና እልቂት

The sun sets over the northern Gaza Strip November 20, 2012. A Hamas official said on Tuesday Egypt had brokered a Gaza ceasefire deal that would go into effect within hours, but a spokesman for Israeli Prime Minister Benjamin Netanyahu said "we're not there yet". REUTERS/Yannis Behrakis (ISRAEL - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
ተስፋ የለሽ ተስፋምስል Reuters

26 11 12



ጋዛዎች የቀበሩ ወገኖቻቸዉን በትክክል ቆጥረዉ ሳያበቁ፣ ሐዘን-እራሮታቸዉን እንዳመቁ፣ በፍርስራሽ፣ ትቢያ ክምር እንደታመቁ በተስፋ ፈነደቁ።ቴል አቪቮች የቁስለኞቻቸዉን ጉዳት እንዴትነት በዝርዝር ሳያዉቁ፣ በማስጠንቀቂያ ደወል የደነገጡበትን ጊዜ እንደቆጠሩ፣ በመደፈራቸዉ እልሕ እንደተንተከተኩ በእፎይታ ፈገጉ።ሮብ።የጋዛ-የእየሩሳሌሞ መሪዎች የለኮሱት፣የዓለም ፖለቲከኛ ዲፕሎማቶችን ያራወጡበት ጦርነት ቆመ።ዘላቂ ሰላም ግን የለም።ፍልስጤም-አይሁድ ቂም-በቀሉን አይረሳም።ደሞ በተቃራኒዉ ተስፋ አይቆርጥም።እና ተኩስ ቆመ ሲባሉ ፍልስጤሞች ቦረቁ፣ አይሁዶችም ፈገጉ።የቅርቡ ጦርነት ምክንያት ዉጤቱ መነሻ፥ የእልቂት ፍጅቱ አሳዛኝ፥ አሰልቺ ዑደት  መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሑኝ ቆዩ።


ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ፥-ቴል አቪቭ የማስጠንቀቂያዉ ደወል-አጓራ።«ሙዚቃ እያዳመጥኩ ነበር።ድንገት ሰዎች ሲሩጡ አየሁ።ወዲያዉ የፖሊስ መኪና ከፊት ለፊቴ ቆመ።እና ፖሊሶቹ እንድንከለል ነገሩን።አጠገቤ ስድስት ሰዎች ነበሩ።በጣም ፈርተዋል።ከአስር ደቂቃ በሕዋላ ግን ጉዞዬን ቀጠልኩ።ሁሉም ጉዞዉን ቀጠለ።»

የቴል አቪቩ ነዋሪ፥-ዳን ዮኤል።የአብዛኞቹ የጋዛ ነዋሪዎች የዕለት-ከዕለት ሙዚቃ እገዳ-ከበባ የወለደዉ የፍዳ-መከራ ሐዘን እንጉርጎሮ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ።ጋዛ የተዋጊ ጄቶች ስግግምግምታ፥ የቦምብ ሚሳዬል ፍንዳታ «ሲሞዘቅባት» ደግሞ ሐዘን እንጉርጉሮዉ በጣር-ጩኸት፥ በስቃይ-ሰቆቃ ዋይታ-ተለወጠ።
                
«የጋዛ ሕዝብ፥ ይሕ የተገደሉ ወገኖቹን የሚቀብረዉ ሕዝብ በስቃይ፥ ሰቆቃ፥ እና ድብደባ ለመኖር ተገድዷል።ሁሉም እምነትና ምግባራቸዉ ሊከበርላቸዉ በተገባ ነበር።»

የጋዛዉ ነዋሪ።በማግስቱ ሮብ፥-ተኩስ ቆመ ተባለ።ጋዛ፥-ደስታ፥ተኩስ አቁሙ ግን ለሁሴይን አብድ እንደ ብዙ የጋዛ ነዋሪዎች ሁሉ ተስፋን-ከስጋት የቀየጠ ነዉ።«ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እንፈልጋለን።ከሁሉም ወገን ዋስትና እንፈልጋለን።ካጭር ጊዜ መረጋጋት በኋላ በወር ዉስጥ ችግሩ ዳግም እንዲባባስ አንፈልግም።»

አሽኬሎን፥ ቴላቪቮች ላፍታ እፎይይ አሉ።ግን እሳቸዉ እንደሚሉት እፎታዉ በጥርጣሬ የታጀለ፥ ዛቻም ያመቀ ነዉ።
     
«እንደሚመስለኝ ይሕ ስምምነት ዋጋ የለዉም።ከልብ ካልተከበረ ከወራት በሕዋላ እንደገና ሮኬት ይተኮስብናል።እና ዳግም እንሰቃያለን።እነሱን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የእግረኛ ጦር ጥቃት አስፈላጊ ነዉ።»

እስራኤልና ሐማስ፥ እስራኤልና ፍልስጤሞች፥ እስራኤልና ሒዝቦላሕ፥ እስራኤልና ሊባኖስ፥ እስራኤልና ሶሪያ፥ እስራኤልና ግብፅ እና እስራኤልና ድፍን አረብ ሲዋጉ ተኩስ ሲያቆሙ፥ ሲደራደሩ ሲጋጩ ያሁኑ የመጀመሪያቸዉ እንዳልሆነ ሁሉ የመጨረሻቸዉም ይሆናል ብሎ የሚጠብቅ የለም።

ከዘንድሮዉ በፊት እንደ ድሮዉ ሁሉ በሁለት ሺሕ ስምንት ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጋዛ ነድዳ-ወድማ፥ የደቡባዊ እስራኤል ከተሞች በሮኬት ተጎጫጭፈዉ ነበር።ሰበቡ ያዉ እንደ ድሮ-ዘንድሮዉ ሁሉ እንደተመልካቹ ተቃራኒ ነዉ።

ግን እንዲሕ ተጀመረ።የፍልስጤሙ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስና እስራኤል በግብፅ ሸምጋይነት ሰኔ-አስራ ዘጠኝ ሁለት ሺሕ ስምንት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዘገበዉ ከሰኔ ሐያ-እስከ ሃያ ስድስት በነበረዉ ጊዜ የእስራኤል ጦር ስድስቴ፥ ከሐማስ ጋር ግንኙነት «የሌላቸዉ» የተባሉ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ደግሞ ሰወስት ጊዜ ለንቋሳዉን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰዋል።

«ሐይ» ያላቸዉ አልነበረም።ከነበረም አልሰሙትም።ሕዳር አራት 2008 እስራኤል የሐማስ መተላለፊያ ምሽግ ያለችዉን ለማጥፋት የሐማስ ይዞታቸዉን ደበደበች።ወዲያዉ የእስራኤል እግረኛ ጦር፥ ታንኮችና ቡልደዞሮች ጋዛን ይመነቃቅሩት ያዙ።ታሕሳስ አስራ-ሰባት የእስራኤል ጦር አንድ የአርባ ዓመት ፍልስጤማዊ ገደለ።በማግስቱ ሐማስ ተኩስ አቁሙ መፍረሱን አወጀ።በዘጠነኛዉ ቀን ጦርነት ተባለ።ታሕሳስ ሃያ-ሰባት።ያኔ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኤሁድ ኦልሜርት ነበሩ።

ዘንድሮ፥ቤንያሚን ኔታንያሁ ናቸዉ።ኔታንያሁ በቀደም እንዳሉት ሐገራቸዉ የጋዛን ሕዝብ የምትጎዳ፥ የምታጠቃበት ምክንያት የላትም።ሐማስን እንጂ።
                  
«እኛ ከጋዛ ሕዝብ ምንም ነገር የለንም።የሚያሳስበን ሐማስ ነዉ።እስራኤልን በሮኬት የሚደበድበዉ አሸባሪ ቡድን ነዉ-የሚያሳስበን።የዘመቻችን ምክንያትም ይሕ ብቻ ነዉ።»

ታሕሳስ-ሁለት ሺሕ ስምን በተጀመረዉ ጦርነት ግን ከአንድ ሺሕ አንድ መቶ ስልሳ-ስድስት እስከ አንድ ሺሕ አራት መቶ አስራ-ሰባት የሚደርስ የጋዛ ነዋሪ ተገድሏል።ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ንብረት ወድሟል።ከአምስት መቶ በላይ መኖሪያ ቤቶች ተደምስሰዋል።ወትሮም እስራኤል በጣለችዉ እገዳ ፍዳዉን የሚያዉ ፍልስጤማዊ ከሰማንያ ከመቶ የሚበልጠዉ ተመፅዋች ሆኗል።


እስራኤል አስር ወታደሮችና ሰወስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዉባታል።የደቡባዊ እስራኤል ከተሞች በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንት ብቻ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ያሕል ገቢ አጥተዋል።ተምሕር ቤቶች ተዘግተዉ፥ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተሰርዘዉ ከርመዋል።በሰወስተኛ ሳምንቱ ግን ጦርነቱ ቆመ ተባለ።እስራኤል «አሸባሪ» ካለችዉ ሐማስ ጋር ተኩስ ለማቆም ተስማማች።ጥር ሃያ-አንድ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ።አይሁድ ፍልስጤም ተስፋ አይቆርጠም።የሰላም ተስፋ።

ተስፋዉ ግን ከዘንድሮ አልዘለቀም። ፍልስጤም-አይሁድ ቂም በቀሉን አይረሳም።ጋዛዎች የወደመ ቤት፥ መስሪያ ቤት፥ ሕንፃ፥ መጠለያቸዉን ጠግነዉ ሳያበቁ-ሌላ ጦርነት።የተጀመረበት ሰበብ-ምክንያት እንደሁሌዉ እንደየባለ ጉዳዩ ተቃራኒ ነዉ።

ብቻ ሕዳር አስራ-አራት፥-እስራኤል የሐማስን የጦር መሪ አሕመድ ጃቢሪንና ሌሎች ሰወስት ሰዎችን ገደለች።የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ሮኬቶች ከጋዛ ወደ ደቡባዊ እስራኤል ይወነጨፉ ያዙ።ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዛቱ።
                       
«ማንኛዉም ሐገር ከተሞቹና ሰላማዊ ሰዎቹ በሮኬት ሲጠቁ አይታገስም።እስራኤልም እንዲሕ አይነቱን ጥቃት አትታገስም።»

የጋዛዎች የእልቂት ስቃይ-ሰቆቃ እቶን ዳግም ተበረገደ። የአሽኬሎን፥ የቴል አቪቮች የሥጋት-መሸማቀቂያ በር እንደገና ተከፈተ።ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እስከ መሐመድ ሙርሲይ፥ ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን፥ እስከ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ፥ ከልዩ መልዕክተኛ ቶኒ ብሌር እስከ ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን ያሉ የዓለም መሪ-ዲፕሎማቶች ቀዳሚዎቻቸዉ በየጊዜዉ እንዳደረጉት፥ እነሱ በቅጡ እንለመዱት እንደገና ይባትሉ ገቡ።

አሰልቺ ልመና ተማፅኗቸዉን እንደገና ደገሙት።ፓን ጊ ሙን።የነገ-ሳምንት ማክሰኞ።
                
«መልዕክቴ ግልፅ ነዉ።ሁሉም ወገኖች ተኩስ ማቆም አለባቸዉ።ሁኔታዉን ማባባስ መላዉን አካባቢ ከአደጋ ይዶሏል።»

የዓለም ትልቁ ዲፕሎማት «አደጋ» ያሉትን በርግጥ አላብራሩትም።ሠላም ማለታቸዉ ከሆነ ግን ጥያቄ ይጭራል።እስራኤልና ፍልስጤሞች በርግጥ ሰላም ናቸዉ።ሶሪያ ሠላም ነች።ኢራቅ፥ ሊባኖስ፥ ኢራን፥ ሊቢያ---ሌሎቹስ? የሚል ጥያቄ።

ግን ሌሎች መሪ-ዲፕሎማቶችም ሌላ አላሉም።በአካባቢዉ ቀድመዉ ከደረሱት ዲፕሎማቶች አንዱ፥-የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለም ደገሙት።
             
«እስራኤል የራስዋን ዜጎችዋንና ሐገሯን የመከላከል ሙሉ መብት አላት።(አሁን) በጣም አስፈላጊዉ ነገር ግጭቱ እንዳይባባስ ማድረግ ነዉ።»

ጋዛዎች ሙቶቻቸዉን እየቀበሩ-ሲቆጥሩ፥ አንድ መቶ አምስት ሰላማዊ ሰዎች፥ ሐምሳ-አምስት ታጣቂዎች አሉ።የቆሰለ-ዘጠኝ መቶ ሰባ አንድ።ከእስራኤሎች አራት ተገደሉ፥ ሁለት መቶ አስራ ዘጠኝ ቆሰሉ።የተጠፋዉ ሐብት ንብረት መጠን እስካሁን በዉል አልተሰላም።

የጦርነቱ ዓላማ ግን የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር ኤሁድ ባራክ  እንዳሉት ሙሉ በሙሉ ግቡን መትቷል።
        
«ዓላማችን ሙሉ በሙሉ ግቡን መትቷል።ሐማስና እስላማዊ ጂሐድ ቆጥቋጭ ዱላ ቀምሰዋል። የሐማስ የጦር መሪ ጃብሪ እና ሌሎች በርካታ አሸባሪዎች፥ አዛዦችና ተባባሪዎች ተገድለዋል።ባጠቃላይ ከአንድ መቶ ሠላሳ በላይ ተገድለዋል።ከዘጠኝ መቶ በላይ ቆስለዋል።»

ስማቸዉን የሸሸጉት የሐማስ አባልም ጦርነቱ በድል ተጠናቀቀ አሉ።
                 
«ይሕ ጥሩ ነገር ነዉ።ፍልስጤሞች ድል አስመዝግበዋል።መጀመሪያ አይዶችን በደንብ ደብድበዋል።አሁን ደግሞ ተኩስ እንዲቆም አድርገዋል።»

እና አታካቹ፥ አሳዛኙ የእልቂት ፍጅት ዑደት አንድ ምዕራፍ ዘለለ። ከተለመደዉ፥ አሰልቺ ዲፕሎማሲ ልመና ተማፅኖ በሕዋላ የተለመደዉ ጦርነት፥ በተለመደዉ ተኩስ አቁም-መተካቱ ታወጀ። ሮብ።አሰልቺ፥ አስጊዉ ዉዝግብ ግን ቀጥሏል።ምናልባት እስከሚቀጥለዉ ጦርነት-እና እልቂት።ለዛሬዉ ይብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ቴል አቪቭ፤አዉቶቡስምምስል Reuters
ቴል አቪቭ መንገደኞች ተጎዱምስል dapd
ጋዛ፤ ነብስ አዳኞችም ተመቱምስል picture-alliance/dpa
ጋዛ-ሕፃኑም ተገደለምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ









 

 






 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW