1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የጋዛ እልቂት፣ የታጋቾች ተስፋና ዲፕሎማሲ

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2016

ማሕሙድ አባስ የጋዛ ሕዝብ ሞት፣ስቃይ ሰቆቃ እንዲቆም ባይደንን ተማፀኑ።ቅዳሜ።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የዚያኑ ዕለት እንዳሉት ግን ጦርነቱን ማቆም አይደለም ፍልስጤሞችን የሚገዛዉን ወገን የምትመርጠዉ እስራኤል እንጂ ፍልስጤሞች ወይም የአባስ ድርጅት ሊሆን አይችልም።

የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዬ ከአረብ-ሙስሊም ሐገራት አቻዎቻቸዉ ጋር
የአረብ፣ ሙስሊምና የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች-ቤጂንግምስል Pedro Pardo/AFP/Getty Images


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪቃ ሕብረት፣ቻይና የዓረብ-ሙስሊምና   የተቀሩት ሐገራት መንግስታት፣ የአብዛኛዉ ዓለም ሕዝብም የጋዛ ሕዝብ እልቂት፣ሥቃይ-ዕመቃ እንዲቆም ይጠይቃሉ።እስራኤል «እንቢኝ» እንዳለች ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የጋዛ ሕዝብን ለፈጀና ለሚፈጀዉ ቦምብ ሚሳዬል «በጎደለ ለመሙላት» ለእስራኤል 14 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት እየመከረች ነዉ።ደግሞ በተቃራኒዉ እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ ሊያጠፉት ከዘመቱበት ቡድን ጋር መስማማታቸዉ ተወርቷል።የጋዛ ዉድመት፣ የእስራኤል አሜሪካኖች-ሐማስ ስምምነትና ዲፕሎማሲዉ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

የፍልስጤም ራስ-ገዝ ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ 88ኛ ዓመታቸዉን ባለፈዉ ሮብ ደፈኑ።የዘመድ-ወዳጅ-ወገኖቻቸዉን አስከሬን ሲቆጥሩ፣ስደተኛ ሲያሰሉ፣ ጉልበተኞችን ሲማፀኑ አድገዉ ላረጁት ፖለቲከኛ የዘንድሮ ልደታቸዉም በእልቂት-ጥፋት ሐዘን የጨለመ፣ኃለኞችን በመለመን ቀቢፀ ተስፋ- የደበዘዘ ነዉ።
                                       
«ፕሬዝደንት ባይደን! በየዋሕ ሕዝባችን ላይ የሚፈፀመዉን ይሕን ሰብአዊ ጥፋት፣ ይሕን ዘር ማጥፋት፣ይሕን ታሪክ ማንንም ነፃ የማያደርገዉን (እልቂት) ባለዎት ሥልጣንና ሰብአዊ አቅም ሁሉ እንዲያስቆሙና ጋዛ ለሚኖረዉ ህዝባችን ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ አማፀናለሁ።ይሕ ጦርነት ባስቸኳይ መቆም አለበት።በእዉነቱ እነዚሕ ቅጣት የሚገባቸዉ የጦር ወንጀሎች ናቸዉ።»

የፍልስጤም ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስምስል Saudi Press Agency/Newscom/picture alliance

አባስን በሰባት ዓመት የሚያንሱት የአሜሪካዉፕሬዝደንት ጆ ባይደን የፍልስጤሞቹን መሪ የሰቆቃ ጩኸት አልሰሙም ማለት አይቻልም።የሰጡት መልስ ግን በርግጥ የለም።
ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ዋዜማ እስከ ጆ ባይደን ድረስ 7 የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞችን ለፕሬዝደንትነት አብቅታለች።በሩዘቬልት ብልሐት፣ በትሩማን ድፍረት፣በኬኔዲ ጥበብ፣ በክሊንተን ትዕግስት፣ በኦባማ ተግባቢነት ከኪሳራ መዉጣትን፣ የጦርነት ድል አድራጊነትን፤ የዲፕሎማሲ ትዕግስትን፣ የፖለቲካ ብልጠትን፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪነትን፣ ከሁሉም ጋር ኃያል፣ሐብታም መሆንን፣ ተወዳጅነትንም አትርፋለች።

ጆ ባይደን የዩናይትድ ስቴትስን የዴሞክራቲክ ፓርቲን  የተቀየጡት በፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ  ዘመነ-ሥልጣን ነበር።እግአ በ1962 ግድም። በ29 ዓመታቸዉ።ባይደን የፖለቲካ መርሕ የሚጋሯቸዉን ቀዳሚዎቻቸዉን መሆን አለመሆናቸዉ በርግጥ ብዙ ያነጋግራል።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ምስል Kent Nishimura/Getty Images

 

የፕሬደንትነቱን ሥልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ግን አፍቃኒስታንን ለታሊባኖች አስረክበዋል።የሩሲያዉን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን «ገዳይ» እና «ዋጋ ይከፍላታል» በማለት ለጠብ መዘጋጀታቸዉን በይፋ ያስታወቁት ሥልጣን በያዙ በሁለተኛ ወራቸዉ ነበር።መጋቢት 2020 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር)
 

«ፕሬዝደንት ፑቲን ገዳይ ናቸዉ ብለዉ ያስባሉ?----እሕ።አዎ አምናለሁ።ምን ዋጋ መክፈል አለባቸዉ? የሚከፍለዉን ዋጋ በርግጠኝነት ታያላችሁ።»
ፑቲንን ዋጋ ለማስከፈል ለኪየቭ ገዢዎች ዙሪያ መለስ ድጋፍ እየሰጡ ለዩክሬን ዉድመት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ፣ ሌሎችንም እያስደረጉ ነዉ።በምክትል ፕሬዝደትነት ዘመናቸዉ የተቀበሉትን ዉል እንኳ ማዳን ተስኗቸዉ ቀዳሚያቸዉ ዶናልድ ትራም ከኢራን ጋር የገጠሙትን  ዉዝግብ አንረዉታል።እስራኤል ጋዛን ያወደመችና የምታወድምበትን ቦምብ፣ ሚሳዬል ለመተካት 14 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጣት እየተከራከሩ ነዉ።

ጋዛ ዉስጥ የ13 ሺሕ ፍልስጤማዉያን አስከሬንን ያስቆጠሩት ማሕሙድ አባስ የጋዛ ሕዝብ ሞት፣ስቃይ ሰቆቃ እንዲቆም ባይደንን ተማፀኑ።ቅዳሜ።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የዚያኑ ዕለት እንዳሉት ግን ጦርነቱን ማቆም አይደለም ፍልስጤሞችን የሚገዛዉን ወገን የምትመርጠዉ እስራኤል እንጂ ፍልስጤሞች ወይም የአባስ ድርጅት ሊሆን አይችልም። 
«የፍልስጤም አስተዳደር አሁን ባለበት ቅርፁ ሊቆጣጠር አይችልም፤ ጋዛን ሊቆጣጠር አይችልም።ከተዋጋን በኋላ፣ ይሁን ሁሉ ካደረግን በኋላ ለነሱ አሳልፈን ልንሰጥ?»

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁምስል Xinhua/IMAGO

 

በሳልስቱ ዛሬ ፕሬዝደንት ባይደን 81ኛ ዓመት ልደታቸዉን አከበሩ።ያጋጣሚ ነገር ባይደን ከኔታንያሁ በ7 ዓመት ይበልጣሉ፤ ከአቡ ማዝን (አባስ) በ7 ዓመት ያንሳሉ።አዛዉንቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የአሜሪካኖችን የምስጋ ቀን ለመዘከረም እንደ ፕሬዝደንቶች ወግ ዛሬ ሁለት ዝዮች (ተርኪዎች) በምሕረት ለቅቀቁ።ለአሜሪካ አሞሮች ስለሚያዝኑ።

የአባስ ተማፅኖ፣ የኔታንያሁ እንቢታ እንዴትነት በሚያነጋግርበት፣ የባይደን ልደት በሚከበርበት ዛሬ የአረብና የሙስሊም ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ቤጂንግ ናቸዉ-ቻይና።ለወትሮዉ የዋሽግተን «የጡት ልጅ» የሚባሉት የሪያድ ገዢዎች ያደራጁት የሚንስትሮች ጓድ የጋዛንዉድመት ለማቆም ከዋሽግተን ይልቅ የዋሽግተንን ቀንደኛ ተፎካካሪ ቤጂንግን የመረጡ ወይም ያስቀደሙበት ምክንያት የባይደን አስተዳደርን አቋም በግልፅ የመረዳታቸዉ አብነት መሆኑ በርግጥ አያጠያይቅም።
ከዩናይትድ ስቴትስና ከእስራኤል ጋር ተባብራ የቴሕራን ገዢዎችን ስታሳጣ የነበረችዉ ሳዑዲ አረቢያ ከኢራን ጋር የታረቃቸዉ በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ሳይሆን በቻይና ሽምግልና መሆኑን ማጤኑም ጥሩ ነዉ።የአረብ-ሙስሊሞቹ ሐገራት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፈጣን ዉጤት ሊያመጣም-ላያመጣም ይችላል።የቻይና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ ሚንስትሮቹን ካነጋገሩ በኋላ የመስሪያ ቤታቸዉ ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ጋዛ ጦርነት መቆም አለበት።
                        
«ቻይይና ከዓረብና ሙስሊም ሐገራት ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ ነች።ጋዛ ዉስጥ በፍጥነት ግጭቱ እንዲቆም፣ ሰብአዊ ቀዉሱ እንዲቀንስ፣ ፍልስጤምና እስራኤል በሰላም ተቻችለዉ እንዲኖሩ ያለማሰለስ ትጥራለችም።በአካባቢዉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖርም አበክራ ትጥራለች።»

የአፍሪቃ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ዘግይት ብሎም ቢሆን የአዉሮጳ ሕብረትና ሌሎች መንግስታትም የጋዛ ሕዝብ እልቂት፣ስቃይና ሰቆቃ እንዲቆም ግፊት እያደረጉ ነዉ።ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት ከአማን እስከ ዋሽግተን አደባባይ የወጣና የሚወጣዉ ሕዝብም በጋዛ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመዉን የጭካኔ ግድያ አዉግዟል።

በጋዛ ላይ የሚፈፀመዉን ድብደባ በመዋቀም ከተደረጉ ሰልፎች አንዱምስል Henry Nicholls/AFP/Getty Images

በተማፅኖ፣ ፉከራ ንትርክ ዲፕሎማሲዉ መሐል እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ያጋታቸዉን እስራኤላዉን ለማስለቀቅ፣ እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት ከሚወነጅሉት ቡድን ጋር መስማማታቸዉ ተዘግቧል።ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ሽምግልና የያዘችዉ የቀጠር ጠቅላይ ሚንስትርና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ቢን አብዱልረሕማን አሳኒ ትንናት ስምምነቱ ባጭር ጊዜ ገቢር እንደሚሆን አስታዉቀዉ ነበር።
«በአሁኑ ደረጃ አጣብቂኝ ዉስጥ ያለዉ ከመሠረታዊዉ ሐሳብ ይልቅ ገቢራዊ የሚሆንበት መንገድና የሎጅስቲክ ጉዳይ ነዉ።ታጋቾቹን ወደየቤታቸዉ መመለስ ከሚያችል ስምምነት ላይ ለመድረስ በቃረባችንን በርግጠችነት መናገር እችላለሁ።»

የዜና ምንጮች በ6 ገፅ የተዘጋጀዉን ሰነድ ጠቅሰዉ እንደዘገቡት ሐማስ ካገታቸዉ ከ200 በላይ ሰዎች መካከል ሴቶችና ልጆችን ይለቃል።በምትኩ እስራኤል ለአምስት ቀናት ጋዛን መደብደቧን ታቆማለች።የእስራኤል ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሐማስ ደቡባዊ እስራኤልን ባለፈዉ መስከረም 26 ወርሮ 1200 ሰዎችን ገድሏል።ከ300 የሚበልጡት የእስራኤል ወታደሮች ናቸዉ።ከ220 በላይ አግቷል።
እስራኤል በከፈተችዉ የብቀላ ጥቃት የጋዛ ትምሕርት ቤቶችን፣ መኖሪያ ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ አምቡላንሶችን፤ ቤተ-እምነቶችን፣ የስደተኞች መጠለያ መንደሮችን፣ የዉኃ ማጠራቀሚያዎችን አዉድማለች። መገናኛ ዘዴዎችና የመብት ተሟጋቾች እንደ እንደገመቱት እስራኤል ባለፉት ስድስት ሳምንታት ጋዛ ሰርጥ ላይ ያዘነበችዉ ፈንጂ ወደ 30 ሺሕ ቶኖች ይደርሳል።
ጋዜጠኞች፣ ሐኪሞች፣ የአምቡላንስ ሰራተኞች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባልደረቦች በገፍ ተገድለዋል። የጋዛ ባለስልጣናት እንዳሉት በጥቅሉ ከ13 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከ30 ሺሕ በላይ ቆስሏል።
ያለጊዚያቸዉ የተወለዱ ሕፃናት፣የኩላሊት ታካሚዎች፤ የሌላ የድሜ ልክ በሽተኞች፣ አዛዉቶች፣ ቁስለኞች መታከሚያ ሆስፒታል፣ መዳኛ መድሐኒት፣ ዉኃም አያገኙም።ጋዛ።የዘመናችን የምድር ላይ ጀሐነብ።

አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ሳይቀር ከሆeፒታል ለመሰደድ ተገድደዋልምስል Rizek Abdeljawad/Xinhua/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW