1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ እልቂት፣ የምዕራባዉያን ድምፀት መለወጥ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2016

ጉተሬሽም እንደ ኡታንት ሁሉ በርግጥ ታንክ የላቸዉም። ጉተሬሽ ከወር በፊት ያሉትን የብዙ ሐገራት እንደራሴዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች በየመገናኛ ዘዴ-ጉባኤ-ስብሰባዉ የኃይማኖት መሪዎች በየፀሎት፣ ሶላታቸዉ ወቅት፣ከሳንቲያጎ ደ ቼሌ እስከ ኦታዋ፣ ከሲድኒ እስከ ሰነዓ የሚገኘዉ ሕዝብ በየአደባባይ ሰልፉና በዕለቱ ብሉታል።

እስራኤልና ፍልስጤማዉያን ሴቶች በጋራ ለሰላም ተሰልፈዉ
የእስራኤልና የፍልስጤም ሴቶች በጋራ ሰላም ሲማፀኑምስል Yahel Gazit/Middle East Images//abaca/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ እልቂት፣ የምዕራባዉያን የድምፀት ለዉጥ

This browser does not support the audio element.

ጋዛ፣ በደም በሰዉ ደም ማዓልት ወሌት እየጨቀየች፣ ቦምብ-ሚሳዬል እየተዘራባት አስከሬን ይመረት፣ፍርስራሽ ይከመርባታል።ከሰዎች መኖሪያነት ወደ ሰዉ አካል መንጨርጨሪያነት ከተለወጠች ሁለት ወር ከሁለተኛ ሳምንቷ።የዚያች ትንሽ፣ ጠባብ፣ ደሐ ሰርጥ ጎስቋሎች ሕፃን-ካዋቂ፣ ወንድ ከሴት ሳይለይ የሚፈጀዉ የቦምብ-ሚሳዬል ወዠቦ  እንዲቆም፣ ፖለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች፤ ቀሳዉስት፣  መሻኢኾች ተማፅነዋል።ሕዝብ በየአደባባዩ ሰልፍ ጠይቋል።ምግብ፣ ወሐ፣ ሕክምና፣ የተነፈገዉየጋዛ ሕዝብ እልቂት ሊቆም ቀርቶ አልቀነሰም።ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ከዋሽግተን፣ለንደን፣ፓሪስ የሰማነዉ አንድም የሶቮየት ሕብረቱን የቀድሞ መሪ አለያም የአሜሪካዊዉን እዉቅ ፅንፈኛ ፖለቲከኛ አባባል ከማረጋገጥ ጋር ምናልባት ከቦምብ ሚሳዬል ለተረፉት ጋዛዎች ተስፋ ይኖሮዉ ይሆን?የሚል ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም።የጋዛ እልቂት መነሻ፣ ብሒል ተስፋዉ ማጣቃሻ የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አቶኒዮ ጉተሬሽ ከወር በፊት ብለዉታል።«ክቡራትና ክቡራን ጋዜጠኞች።ጋዛ የህፃናት የመቃብር ሥፍራ ሆናለች።በዘገቦች መሰረት በመቶ የሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ወንዶች ልጆች በየቀኑ ይገደላሉ።»

ከጥፋት ከተረፉ ጥቂት ሆስፒታሎች አንዱ ቁስለኛ ሲቀበል-ራፋሕምስል Fatima Shbair/AP/picture alliance

 

ጉተሬሽን ያሉትን በማለታቸዉ ከእስራኤል ባለስልጣናት የተሰነዘረባቸዉ ወቀሳ፣ተቃዉሞና ዉግዘት ሥልጣን እንዲለቁ እስከመጠየቅ ደርሶ ነበር።የቀድሞዉ የሶቭየት ሕብረት መሪ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ በ1960ዎቹ ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከያኔዉ የግብፅ አቻቸዉ ገማል አብድናስር ጋር ሲወያዩ «ኡታንት አንድም ታንክ የለዉም ብለዉ ነበር» አሉ የሰሙ።ሲትሁ ኡታንታ የዛሬዋ ምያንማር ተወላጅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሶስተኛዉ ዋና ፀሐፊ ነበሩ።

ብሬዥኔቭ እንደሚያምኑት ዓለም የምትመራዉ በሕግ ሥርዓት ሳይሆን በታንክ ኃይል ነዉ።የዓለምን ሰላም እንዲጠብቅ፣ ሕግና ሥርዓት እንዲያስከብር ባለታንኮች የመሰረቱት ድርጅት መሪ ጉተሬሽም እንደ ኡታንት ሁሉ በርግጥ  ታንክ የላቸዉም። ጉተሬሽ ከወር በፊት ያሉትን የብዙ ሐገራት እንደራሴዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች በየመገናኛ ዘዴ-ጉባኤ-ስብሰባዉ የኃይማኖት መሪዎች በየፀሎት፣ ሶላታቸዉ ወቅት፣ከሳንቲያጎ ደ ቼሌ እስከ ኦታዋ፣ ከሲድኒ እስከ ሰነዓ የሚገኘዉ ሕዝብ በየአደባባይ ሰልፉና በዕለቱ ብሉታል።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ትናንት ደገሙት።

የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና የብሪታንያዉ አቻቸዉ ዴቪድ ካሜሩንምስል Odd Andersen/AFP/Getty Images | Dan Kitwood/POOL/AFP/Getty Images

 

«ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች በቦምብና በጥይት ይደበደባሉ።ይሕ እርምጃ ከቤተሰቦች፣ ከሕፃናት፣ ከሕሙማን፣ከአካል ጉዳተኞችና ከመነኮሳት በስተቀር እሸባሪ በሌለበት፣በቅዱስ ቤተሰቦች መኖሪያ ቅጥር ግቢ እንኳን ይፈፀማል።»

ሁሉንም ሰማን።በዚያ ጉደኛ ምድር ከእልቂት በስተቀር የተለወጠ ግን የለም።የዩናይትድ ስቴትስ አክራሪ ቀኝ ፖለቲከኛና ዲፕሎማት ጆን ቦልተን በ1994 «የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብሎ ነገር የለም፣ ያለዉ በምድራችን ላይ ባለችዉ ብቸኛ እዉነኛ ኃያል ሐገር ሊመራ የሚችል ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ነዉ።ያቺ ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ ነች» ቀጠሉ በእዉቅ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ሕግ ያጠኑት ፖለቲከኛ «የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅሕፈት ቤት 38 ፎቆች አሉት።ዛሬ 10ሩ ቢናድ ምንም ለዉጥ አያመጣም» ብለዉ።

ከቦምብ-ሚሳዬል ለተረፈዉ ለጋዛ ሕዝብ የምግብ፣የወሐና የመድሐኒት እርዳታ ያገኝ ዘንድ እስራኤል ተኩስ እንድታቆም የሚጠይቅ የዉሳኔ ረቂቅ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቀርቦ ነበር።ቦልተን ከ30 ዓመት በፊት «የለም» ያሉት ድርጅት እንዳይወስን «ዓለም ሊከተላት ይገባል» ያሏት ሐገራቸዉ በተደጋጋሚ ዉድቅ አደረገችዉ።የአብዛቸዉ ዓለም መንግስታትም እንደደነገጠ ቀንድ አዉጣ ወደየመደበቂያዉ ተኮራመተ።ቦልተን ተሳስተዉ ይሆን?
እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤል ላይ ያደረሰዉን ጥቃት ለመበቀል እስራኤል ጋዛ ሰርጥ ላይ የከፈተችዉን አፀፋ ጥቃት፣ በሕዝብ ላይ የጣለችዉን የምግብ፣ የዉሐ፣የመብራትና የሕክምና እቀባ ያልደገፈ፣ ድጋፉን ለመግለፅ እስራኤልን ያልጎበኘ የምዕራብ አዉሮጳና የሰሜን አሜሪካ መሪና ሚንስትር ካለ በርግጥ በግልፅ አልተናገረም።

ከዩናይትድ ስቴትስ በገፍ የሚጋዘዉ ቦምብ፣ሚሳዬል፣አረር፣ ቴክሎጂ ከ20 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዉያን አርግፏል።ከ15 ሺሕ የሚበልጡት፣ ሕጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ናቸዉ።በየሕንፃ ፍርስራሹ፣ በየጉድባ ቦዩ «የተደፋዉን» ፍልስጤማዊ ቤቱ ይቁጠረዉ።ወደ አርባ ሺሕ የሚጠጋ ቆስሏል።የዩናይትድ ስቴትስሱ የፀጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በቀድም እንዳሉት ግን በጣም ያሳዘናቸዉ ሶስት የእስራኤል ታጋቾች በእስራል ወታደሮች መገደላቸዉ ነዉ።
«ልብ የሚሰብር ነዉ።ይሕ ዛሬ ከጋዛ የመጣዉ ዜና በጣም አሳዛኝ ነዉ።አንድ ቤተሰብ ሊሰማዉ የሚችለዉ በጣም መጥፎ ዜና በመሆኑ ከሟቾች ቤተሰቦች ጋር ሐዘኑን እንጋራለን።»
እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮቻቸዉ የቀድሞዉ አድሚራል እንዳሉት በጣም አዝነዋል።የእኒያ ከየፍርስራሽ፣ ዉዳቂዉ ክምር አስከሬናቸዉ እንደ ቁሻሻ እቃ የተለቀመዉ ሕፃናት፣ሽማግሌዎች፣ ሴቶች ወላጅ፣ዉላጅ፣ ቤተሰቦችስ?

ፕሬዝደንት ጆርጅ ቦሽና ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር በ2003 እንዳደረጉት ሁሉ የባይደን አስተዳደርም  የፍልስጤሞችን እልቂት፣ የዓለም ሕዝብን ጩኸት፣የኃይማኖት መሪዎችን ተማፅኖ፣ የፖለቲከኛ ዲፕሎማቶችን ጥያቄ ከቁብ አልቆጠረዉም ነበር።ሰሞኑን ግን ዋሽግተኖች ለእስራኤል የሚሰጡትን ጭፍን ድጋፍ ማስተንተን የጀመሩ መስለዋል።ምክንያቱ ብዙዎች እንደሚሉት ብዙ ነዉ።
ባይደን በገዛ ሕዝባቸዉ ዘንድ ያላቸዉ ድጋፍ አለቅጥ በማሽቆልቆሉ-አንድ፣ዩናይትድ ስቴትስ ከምርጫ ዘመቻ ዓመት መግቢያዋ ስለሆነ-ሁለት፣ ኔታንያሁና ባይደን መጀመሪያ ላይ እንደፎከሩት ሐማስን ባጭር ጊዜ ማጥፋት አለመቻለቸዉ ሲረጋገጥ-ሶስት፣ምናልባት እንደ ሊባኖሱ ሒዝቡላሕ ሁሉ የየመን ሁቲዎች ፍልስጤሞችን ደግፈዉ ቀይ ባሕርን አቋርጠዉ ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን በማጥቃቸዉ አራት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ምክንያቶችን የሚጠቅሱ አሉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደደንት ጆ ባይደንምስል Stephanie Scarbrough/AP Photo/picture alliance

እነዚሕና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረዉ ባይደን ባለፈዉ ሳምንት «እስራኤል አለም አቀፍ ድጋፍ ልታጣ ትችላለች» አሉ።ወዲያዉ የፀጥታ አማካሪያቸዉን ጃክ ሱሊቫንን ወደ እስራኤል ላኩ።የፀጥታ አማካሪዉ ዋና መልዕክት ቃል አቀባያቸዉ ጆን ኪርቢ እንዳሉት የእስራኤል መሪዎች ጋዛን ማዉደም ማጥፋቸዉን ቀነስ እንድታደርጉ በዲፕሎማቶች አገላለፅ «መምከር» ነዉ።
«ደሕና፣ ጃክ ራሱ እንዳለዉ እስራኤሎች ማድረግ ያለባቸዉን እኛ መመሪያ አንሰጣቸዉም።በጣም ከፍተኛ (ድብደባ) ከሆነዉ ወታደራዊ ዘመቻ፣ እኛ አነስተኛ መጠን ወዳለዉ ጥቃት መቀነስ አለበት የሚለዉን ሐሳብችንን እነሱ እንዴት እንደሚያዩት ተነጋግረናል።ይሕ ግጭት ለወራት ሊቀጥል ይችላል።ይሁንና ጃክ ከነሱ ጋር የተነጋገረዉ ዘመቻዉ ወደተለየ ምዕራፍ የሚሸጋገርበትን ጉዳይ እንዲያስቡት ነዉ።ይሕ ማለት ዘመቻዉ በስፋትና በደረጃዉ ይበልጥ ኢላማ ላይ ያተኮረ፣ ያነጣጠረ፣ ነጣይ እንዲሆን ነዉ።»

ዋሽግተኖች ቢያንስ በቃላት ደረጃ አቋማቸዉን የመለወጣቸዉ ዜና በቅጡ ተተንትኖ ሳያበቃ የለንደን፣ በርሊን ፓሪስ ተከታዮቻቸዉ ተመሳሳይ ዜማ ያንጎራጉሩ ገቡ።የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩንና የጀርመኗ አቻቸዉ አናሌና ቤርቦክ በጋራ ፃፉት የተባለ መጣጥፋቸዉን ሳንዴይ ታይምስ በተባለዉ የብሪታንያ ጋዜጣ ላይ ትናንት አትመዋል።
ፅሁፉ የለንደንና የበርሊን መንግስታት ለእስራኤል የሚሰጡትን ድጋፍ አስረግጦ ጋዛን የሚያጠፋዉ ጦርነት «በዘላቂነት እንዲቆም» ይጠይቃል።ቤርቦክ ለወትሮዉ ለወዳጅነታቸዉ ደረጃ «ልክ የለዉም» የሚባሉት ፓሪስ አቻቸዉን ጥለዉ ከለንደኖች ጋር የተወዳጁበት ምክንያት በርግጥ በፅሁፉ አልተጠቀሰም። 

ይሁንና የዋሽግተኖች የአቋም ለዉጥ (ከቃላት ባያልፍም) መግለጫ ቀድሞ፣ የለንደን-በርሊኖች መጣጥፍ ተከትሎ ሲነበብ፣ ፓሪሶችም አሰለሱ።የፈረንሳይዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የካተሪን ኮሎና መግለጫ ከዋሽግተን፣ ለንደን፣ በርሊኖችም ጠንከር፣ጠጠር ያለና ምክንያታዊም ይመስላል።                                   

«ሆን ተብሎ የሚደረገዉ የቦምብ ድብደባ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ነዉ።እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ በተደነገገዉ መሰረት የሰላማዊ ሰዎችን ደሕንነት መጠበቅ አለባት።ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚረዳ ተኩስ አቁም ማድረግ አለባት።እርዳታ እንዲገባና በተሻለ መጠን እንዲሰራጭ መፍቀድም አለባት።»
በሁለት ወር ከሁለተኛ ሳምንታቸዉ አሜሪካ የድብደባዉ መጠን ይቀንስ አለች።አዉሮጳም ተከተለች።ብቻ ብሩዥኔቭ እንዳሉት የጋዛ ሕዝብን የሚፈጀዉ ቦምብ-ሚሳዬል በጠቅላይ ሚንስትር ቤንኒያሚን ኔታንያሁ እጅ ነዉ።እሳቸዉ ደግሞ «እስከ መጨረሻዉ» እንዋጋለንእያሉ ነዉ።

«አላማዎቻችንን በሙሉ ከግብ እናደርሳለን፣ ሐማስን ማጥፋት፣ታጋቾቻችንን በሙሉ ማስለቀቅ እና ጋዛ ዳግም የሽብር፣በእስራእል መንግስት ላይ የሚሰነዘር የጥላቻና የጥቃት  ማዕከል እንዳትሆን የተገባዉን ቃል መጠበቅ።ለተሰዉትና እዚሕ እስራኤል ምድር ለመኖር ለሕልዉናችን ስንል እስከ መጨረሻዉ እንዋጋለን።»

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የፀጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ቴል አቪቭምስል GPO/Anadolu/picture alliance

ታዛቢዎች እንደፃፉት እስራኤል ባጭር ጊዜ ምናልባት በሁለት ሳምንት ዉስጥ የጋዛ ድብደባዋን ሥልት እንድትቀይር የባይደን አስተዳደር ጠይቋል።ኔታንያሁ ግን የዋሽግተኖችን ጥያቄና ማበበያ የተቀበሉት አይመስሉም።ቦልተን ተሳተዉ ይሆን ወይስ ረስተዉ «የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የለም ነዉ-ያሉት።ዩናይትድ ስቴትስ እንጂ።«እስራኤልም» የሚል ሐረግ ይጨመርበት ይሆን?  ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW