1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ጦርነት፣ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ጥቅምት 26 2016

(IISS) እንዳስታወቀዉ የእስራኤል ጦር 169 ሺህ 500 መደበኛ፣465ሺሕ ተጠባባቂ ሠራዊት አለዉ።ጦሩ፣ 2200 ዘመናይ ታንኮች፣ 530 መድፎች፣ ከF-16 እስከ F-35፣እስከ ሐፓቺ ሔሊኮብተር የሚደርሱ 339 የአየር ተዋጊዎች፣ 5 ባሕር ሰርጓች መርከቦች፣49 ቃኚና ተዋጊ ጀልባዎች፣ አይረን ዶም ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬልና ሌላም ታጥቋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን ከረብ አቻዎቻቸዉ ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል
የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና የአረብ ሐገራት አቻዎቻቸዉ ስብሰባ-አማን ምስል JONATHAN ERNST/AFP

የጋዛ ዉድመት፣የአሜሪካኖች ዲፕሎማሲ ክሽፈት

This browser does not support the audio element.

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለዘመናት እንደኖሩበት አሁንም ይዝቱ-ይፎክራሉ።ድል አድራጊ ነኝ እያሉ።የቴል አቪቭ አደባባይ ሰልፈኞ ግን ታጋች-ዘመድ ወዳጆቻቸዉ ባለመለቀቃቸዉ መሪዎቻቸዉን ይቃወማሉ።የኔታንያሁዋ እስራኤል ዋና ደጋፊ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን በአራት ሳምንታት ዉስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ከቴል-አቪቭ አማን፣ከረመላሕ፣ አንካራ ይባትላሉ፤ ከየአስተናጋቾቻቸዉ ቅሬታ፣ ከየሐገሬዉ ሕዝብ ዉግዘት ይፈራረቅባቸዋል።ጋዛዛሬምም ትነፍራለች።እስራኤል ትሸማቀቃለች።አምስተኛ ሳምንት።የጋዛ እልቂት፣ የቴል አቪቭ-ዋሽግተን መሪዎች እንቢተኝነት፣ የአረብ መሪዎች መፍረክረክና የሕዝብ ቁጣ  ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

የቀድሞዉ የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ሊቀመንበር ያሲር አረፋት ባንድ ወቅት  የሚወዱት ፊልም የትኛዉ ነዉ ተብለዉ ተጠየቁ አሉ-ጉዳዩን የሚያዉቁ።«ቶም ኤንድ ጄሪ» መለሱ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ።ጠያቂዉ «ለምን?» ቢላቸዉ «ትልቆች ብዙ ጉዳት ቢያደርሱም ሁል ጊዜ እንደማያሸነፉ ስለሚያሳይ» አሉ ሰዉዬዉ-ከምፀት ፈገግታ ጋር። 
                     

የእስራኤል ኃይል 

በቆዳ ስፋት ከዓለም ትናንሽ ሐገራት አንዷ የሆነችዉ እስራኤል በምጣኔ ሐብት አቅም፣ በቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ ከሁሉም በላይ በጦር ኃይል ጉልበት ከዓለም አንደኞች-አንዷ ናት።በዚሕ ላይ ከዓለም ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር ከዩናይትድ ስቴትስ በገፍና ለዘላለም የሚንቆረቆርላት ዙሪያ መለስ ድጋፍ የመካከለኛዉ ምሥራቅ «የማትበገር» አድርጓታል።
ዩናይትድ ስቴትስ በዓመት 3.8 ቢሊዮን ዶላር የምትቆርጥለት የእስራኤል ጦር በመደኛና በተጠባባቂ የሰዉ ኃይሉ ብዛት፣ በስልጠናዉ ብስለት፣ በታጠቀዉ ጦር መሳሪያ ዓይነት፣ ጥራት፣ ዘመናይነትና በቴክኖሎጂዉ ምጥቀት ከጥቂት ሐገራት በስተቀር ከዓለም ተወዳዳሪ የለዉም።

የእስራኤል እግረኛ ጦር በታንክ ታጅቦምስል Jack Guez/AFP/Getty Images

የስልታዊ ጥናት ዓለም አቀፍ ተቋም (IISS) እንዳስታወቀዉ የእስራኤል ጦር 169 ሺህ 500 መደበኛ፣465ሺሕ ተጠባባቂ ጦር ሠራዊት አላት።ጦሩ 2200 ዘመናይ ታንኮች፣ 530 መድፎች፣ ከF-16 እስከ F-35፣እስከ ሐፓቺ ሔሊኮብተር የሚደርሱ 339 የአየር ተዋጊዎች፣ 5 ባሕር ሰርጓች መርከቦች፣49 ቃኚና ተዋጊ ጀልባዎች፣ አይረን ዶም ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬልና ሌላም ታጥቋል።

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የሚወነጅሉት ሐማስባንጻሩ ባለፈዉ መስከረም በደቡባዊ እስራኤል ላይ ያደረሰዉን ጥቃት ለመበቀል እስራኤል 360 ሺሕ በላይ ወታደሮች ወደ ጋዛ ሰርጥናና አካባቢዉ ማዝመቷን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አስታዉቋል።
ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚገመተዉ ሐማስ ትልቁ መሳሪያዉ እስከ 75 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚወነጨፈዉ ፈጂር 5 የተባለዉ ሚሳዬል ነዉ።ሌሎቹ መሳሪዎቹ WS-1 E፣ ቃሳም ና  ካቱሻ የተባሉት ሚሳዬሎችና ጓዳ ሰራሽ ሮኬቶች ናቸዉ።

የጋዛ ዉድመትና የቀጣይ ጥቃት ዛቻ

ከሕንፃ ፍርግርግ ወደ ጉርጉድ፣ ከምድር ምሽግ ወደ ዋሻ የሚሽሎኮሎኩትን የሐማስ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ የዘመተዉ የእስራኤል ጦር ጋዛ ሰርጥ ላይ በትንሽ ግምት ከ6 ሺሕ ቶን በላይ ቦምብ አዝንቧል።የሚሳዬል፣ መድፍ፣ አዳፍኔዉን ብዛት በትክክል የዘገበዉ፣ በግልፅ የተናገረዉም የለም።የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሐጋሪ በቀደም እንዳሉት ጦራቸዉ ጦርነት የገጠመዉ ከጋዛ ሰላማዊ ሰዎች ጋር ዓይደለም።
«የኛ ጦርነት ከሐማስ ጋር ነዉ።ከሰላማዊ ሰዎች ጋር ዓይደለም።ሐማስ የአሸባሪ መዋቅራቸዉን ለመደበቅ ሆስፒታሎችን እንዲጠቀም አንፈቅድም።»

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሐጋሪምስል Gil Cohen-Magen/AFP

የእስራኤል መሪዎች «ሰብአዊ አዉሬ« ያሏቸዉን ኃይላት ለማጥፋት በከፈቱት ጥቃት የተገደሉት ሰላማዊ ፍልስጤማዉያን ቁጥር ግን ወደ 10 ሺሕ ደርሷል።4 ሺሕ የሚጠጉት ሕፃናት፤ ከተቀሩት አብዛኞቹ ሴቶች ናቸዉ።ከ35ቱ የጋዛ ሆስፒታሎች 16ቱ አንድም በእስራኤል ጦር ተመትተዋል፣ ወይም ከአገልግሎት ዉጪ ናቸዉ።ትምሕርት ቤቶች፣ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች፣መኖሪያ ቤቶች፣ የዉኃ ማጠራቀሚያዎች፣ አምቡላንሶች---ብቻ ጋዛ በርግጥ ወድማለች።

ሐማስ ግን አሁንም ሮኬቱን ወደ እስራኤል ያወነጨፍል፤ እስራኤሎችን ያሸማቅቃል።ያገታቸዉን ሰዎችም አለቀቀም።አምስተኛ ሳምንቱ።ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያሚን ኔታንያሁም ይዝታሉ።
«ድላችን ቁርጥና ግልፅ ነዉ።ለጠላቶቻችን መልዕክት ያስተላልፋል።ለትዉልዶች የሚያስተጋባ መልዕክት።የጠላቶቻችን ዓላማ መንግስተ-እስራኤልን ማጥፋት ነዉ።እና እነግራችኋለሁ።ለነሱም እናገራለሁ ጠላቶቻችን ይወድቃሉ፤ ይሸነፋሉ።»

እነማን? መቼና እንዴት? ጠቅላይ ሚንስትሩ በግልፅ አልተናገሩም።ኔታንያሁ ባለፈዉ ቅዳሜ የዩናይትድ ስቴትሱን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለማነጋገር ኪሪያ የተባለዉ የቴል አቪቭ የእስራኤል ጦር ኃይል ጠቅላይ ዕዝ ዉስጥ መቀበል ነበረባቸዉ።ኔታንያሁ ከብሊንከን ጋር ሲነጋገሩ የቴል አቪቭ አደባባዮች ሐማስ ያገታቸዉ እስራኤላዉያን እንዲለቀቁ በሚጠይቁ ሰልፈኞች ተሞልተዉ ነበር። ኔታንያሁ እንዳሉት መንግስታቸዉ ከድል በመለስ ተኩስ አቁም ብሎ ነገር አይቀበልም።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ንግግር ሲያደርጉምስል Abir Sultan via REUTERS

«የታጋቾቻችንን መለቀቅ የማያካትት የጊዚያዊ ተኩስ አቁም (ጥያቄን) እስራኤል አትቀበልም።እስራኤል ወደ ጋዛ ነዳጅ ዘይት መግባቱንና ገንዘብ መላኩን አትቀበልም።»
 

የዲፕሎማሲዉ ክሽፈትና ተቃዉሞ 

የአሜሪካዉ ዲፕሎማት በኔታንያሁ ዛቻ፣ በአደባባይ ሰልፈኞች ጩኸት፣ በሐማስ ሚሳዬል፤ በሚሳዬል ማስጠንቀቂያ ደወል፣ በአይረን ዶም ተኩስ የተደበላለቀችዉን ቴል አቪቭን ጥለዉ አማን ሲገቡም ያደባባይ  ዉግዘትና የአዳራሽ ዉስጥ ተቃዉሞ ነዉ የገጠማቸዉ።ብሊንከን ከተለያዩ የአረብ ሐገራት አቻዎቻቸዉን ጋር አዳራሽ ዉስጥ ሲነጋገሩ የአማንን አዉራ ጎዳኖችን ያጥለቀለቀዉ ሰልፈኛ እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስን ከማዉገዝ አልፎ የራሱን የዮርዳኖስ መሪዎችን ጭምር አጥብቆ ተቃዉሟል።

«የዮርዳኖስ ምክር ቤት ጋዛን ለመርዳት ምንም ያደረገዉ ነገር የለም።የዮርዳኖስ ሕዝብ ምንም አላደረገም።ምሁራኑ ምንም አላደረጉም።የኛ ሕዝብ በኑክሌር ቦምብ መመታት ይገባዋል።አያሳፍርም? ሁለት ቢሊዮን አረብና ሚስሊሞች የራፋሕ መተላለፊያን እንኳን መክፈት ሲያቅታቸዉ-ይሕ አሳፋሪ አይደለም።»
ከዮርዳኖስ ሰልፈኞች አንዷ።የአረብ ሚኒስትሮችም እንደከዚሕ ቀደሙ የህዝባቸዉን ቁጣ ለመሸፋፈን አልቻሉም።ቁጣዉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2011 እንደሆነዉ ከየሥልጣን መንበራቸዉ ጠራርጎ እንደሚወስዳቸዉ ከተረዱት አንዱ የዮርዳኖሱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አይማን ሳፋንዲ የእስራኤልን ጥቃት «የጦር ወንጀል» በማለት በግልፅ አወገዙ።
«እኛ ዮርዳኖሳዉያንና የአረብ ሐገራት በሙሉ ይሕን እንደ ጦር ወንጀል ነዉ የምንቆጥረዉ።ባለን አቅም ሁሉ ማስቆም አለብን።የአረብ ሐገራት፣ የአረብ ዓለም ይሕ ጦርነት፣ የንፁሐን መገደልና ጥፋቱን የሚያቆም አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ይጠይቃል።»
የግብፁ አቻቸዉ መልዕክትም ተመሳሳይ ነዉ።የአሜሪካዉ ትልቅ ዲፕሎማት አንተኒ ብሊከን ግን የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቴል አቪቭ ላይ ያሉትን አማን ላይ ደገሙት።ተኩስ አቁም አይደረግም።
«በኛ አመለካከት አሁን ተኩስ አቁም ቢደረግ ሐማስ ዳግም እንዲደራጅና መስከረም 26 ያደረሰዉን እንዲገም ይረዳዋል።» 
የሐማስ ታጣቂዎች ባለፈዉ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤልን ወርረዉ 1400 ሰዎች ገድለዋል።ከ200 በላይ አግተዋል።የሐማስን ጥቃት አብዛኛዉ ዓለም አዉዟል።ይሁንና አብዛኛዉ ዓለም እስራኤል በከፈተችዉ የብቀላ ጥቃት የጋዛን ሰላማዊ ሕዝብ መፈጅቷ መቆም አለበት ባይ ነዉ።የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ትናንት ረመላሕ ደርሰዉ አንካራ ሲገቡም ከቱርክ ሕዝብና ባለስልጣናት ጠንካራ ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል።

ጋዛ ትወድማለችምስል Bashar Taleb/APA Images via ZUMA Press/picture alliance

ብሊንከን በተቃዉሞ ታጅበዉ ካንዱ የመካከለኛዉ ምስራቅ ርዕሰ ከተማ ወደ ሌላዉ ሲባትሉ በአሜሪካኖች ወረራ ከወደመችበት በቅጡ ያላንሰራራችዉ የኢራቅ ርዕሰ ከተማ ባግዳድ የአሜሪካ ቀንደኛ ጠላት የኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሂም ራሲን ታስተናግድ ነበር።በአመሜሪካ የሚደገፈዉ የኢራቅ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሺያ አል ሱዳኒ ከኢራኑ እንግዳቸዉ ጋር ሆነዉ በሰጡት መግለጫ አሜሪካን በተዘዋዋሪ እስራኤል በቀጥታ አዉግጠዋል።

«ግጭቱ ባለበት እንዲቆይና በአካባቢዉ በመላ እንዳይሰራጭ የሚፈልጉ ወገኖች ፅዮናይዊዉ ሥርዓት የወታደራዊ ወረራዉን እና ሆን ብሎ ሰዎችን መግደሉን እንዲያቆም ግፊት ሊያደርጉበት ይገባል።» 
                               

የባይደን አስተዳደርና የመንግስታት ተቃዉሞ

ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ እዚያዉ ዋሽግተን ዋይት ሐዉስ አጠገብ ሳይቀር በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ አሜሪካዉያን የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር ለጋዛ ሕዝብ ርዳታ እንዳይደርስ መከልከሉንና እስራኤል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የምትፈፅመዉን ግድያ መደገፉን አጥብቀዉ ተቃዉመዋል።ጥናቶች እንደጠቆሙት ለወትሮዉ ዴሞክራቶችን የሚደግፉት አረብና ሙስሊም አሜሪካዉያን ለባይደን መስተዳድር የሚሰጡት ድጋፍ ወደ 17 ከመቶ አሽቆልቁላል።

የጋዛ ሰርጥ ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ ዋሽግተን ከተደረገዉ ሰልፍ በከፍልምስል Stefani Reynolds/AFP

በጋዛ ላይ የሚደርሰዉን እልቂት በመቃወም እስራኤል የሚገኙ አምባሰደሯን በመጥራት ደቡብ አፍሪቃ እስካሁን የመጨረሻዋ ሐገር ሆናለች።ከዚሕ ቀደም ቮሊቪያ ከእስራኤል ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣለች።ኮሎምቢያ፣ ቺሌ፣ ዮርዳኖስና ቱርክ አምባሳደሮቻቸዉን ወደየሐገራቸዉ ጠርተዋል።

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር ለመንግስታቱም ሆነ ለሕዝቡ ጥያቄና ጥሪ የሰጠዉ መልስ ግን ተጨማሪ ጦር ኃይል ወደ መካከለኛዉ ምስራቅ ማዝመት ነዉ። የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስ ሁለት የጦር አዉሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቦች፣ በመቶ የሚቆጠሩ ተዋጊ ጄቶችና በሺሕ የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮች አዝምታለች።ትናንት ደግሞ የኑክሌር ሚሳዬል ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ልካለች።ለሰላማዊ ጥሪ የዋሽግተኖች አፀፋ።ቸር ያሰማን።
 

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW