1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች መብት እንዲከበር ማሳሰቢያ ተሰጠ

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2014

ለዜጎች መብት መከበር የሚሟገተው ጋዜጠኛ መብት ይከበር ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያዎች ማህበር አሳሰበ። ማህበሩ ትላንት ባውጣው መግለጫና ለDW በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ በጋዜጠኞች ላይ እየተፈጸመ ነው ያለው ከህግ ውጭ እስርና ወከባ መቆም አለበት ብሏል።

Illustration | Mikrofon in Ketten
ምስል Sorapop/Panthermedia/imago images

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማሕበር የጋዜጠኞች መብት እንዲከበር ተጠየቀ

This browser does not support the audio element.

160222
የጋዜጠኞች መብት ይከበር ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር አሳሰበ።

 

ለዜጎች መብት መከበር የሚሟገተው ጋዜጠኛ መብት ይከበር ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያዎች ማህበር አሳሰበ።
ማህበሩ ትላንት ባውጣው መግለጫና ለDW በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ በጋዜጠኞች ላይ እየተፈጸመ ነው ያለው ከህግ ውጭ እስርና ወከባ መቆም አለበት ብሏል።

የሪፖርተሩ ጋዜጠኛ ሲሳይ ሳህሉ በቅርቡ አማን አውለኝ ብሎ ከቤቱ ወደ ስራ በተሰማራበት ወቅት ያጋጠመው በተቃራኒው ነበር። የጋዜጠኝነ ተግባሩን ከአንድ የውጭ ጋዜጠኛ ጋ በሚያከናውንበት ሰአት ድንገት በመጡ የደንብ አስከባሪዎች በቁጥጥር ስር ዋለ። ደንብ አስከባሪዎቹ አሳልፈው ለፖሊስ ስጡት። ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ ታስሮ ከተመረመረ ቦኋላ ተለቀቀ። እንዲህ አይነት የጋዜጠኞች እስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጸው ጋዜጠኛ ሲሳይ ይህ በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስቧል።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ``የጋዜጠኞች ሲኦል`` እስከመባል ደርሳ ነበር። ባለፉት ጥቂት አመታት ባገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ጋዜጠኛ ያልታሰረበት አመት ተብሎ አለም አቀፍ የፕረስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ እስከ መከበር ተደርሶም ነበረ። ሁሉም ግን በነበር ለማስቀረት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ጋዜጠኞች ከስራ ገበታቸው ከስቱድዮ ጭምር ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚታሰሩበት፣ ታስረውም በቤተሰብና በጠበቆቻቸው ሳይጎበኙ ለወራት ባልታወቁ እስርቤቶች የሚማቅቁበት ሁኔታ ተፈጠረ። ይህ ድርጊት አሳስቦኛል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ትላንት ባወጣው መግለጫ ቅሬታውን ገልጿል። የማህበሩ ፕረዚደንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለDW በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያም ተስፋ የተጣለበት ለውጥ በጋዜጠኝነት ላይም እንዲሁ ጭላንጭል የታየበት ሁኔታ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ጋዜጠኞች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚታሰሩበት፣  የሚደበደቡበትና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለወራት ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸው ጋ ሳይገናኙ በእስር የሚማቅቁበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ገልጿል። ጋዜጠኞች ከስቱድዮ ጭምር ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ተወስደው ሲታሰሩ በአካል የታዘበው ጥበቡ እየጨመረ የመጣው የጋዜጠኞች እስር በሙያተኛው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሆነ ይገልጻል።

በወንጀል የተጠረጠረ ጋዜጠኛ በህግ አግባብ አይጠየቅ የሚል አቋም እንደሌለው የጠቀሰው የማህበሩ መግለጫ ከህግ አግባብ ውጭ የሚከናወኑ እስሮች መቆም አለባቸው፣ እስካሁን ያልተለቀቁትም በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው ብሏል። የማህበሩ ፕረዚደንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠም በጋዜኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው እስር ወከባ ሙያውን የሚያቀጭጭና የተጀመረው የተስፋ ጭላንጭል ይሚያጠፋ በመሆኑ ሊታረም ይገባል ሲል አክሏል።

ለሌሎች መብት መከበር የሚታገለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ በማህበር ተደራጅቶ ለመብቱ በመታገል ረገድ ብዙ እንደሚቀረው ትችቶች ይቀርቡበታል። በጋዜጠኞች የሚደርስ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚደመጠው በውጭ የሙያው መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ነው። ይህ መሆኑ እጅግ እንደሚያሳዝነው የማህበሩ ፕረዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ ተናግሯል።

የማህበሩ መግለጫ በመጨረም በአገሪቱ ጋዜጠኞች እየተሳደዱ የሚቀጥል ከሆነ አዲሱ ትውልድ የጋዜጠኝነት ሙያን እንደወንጀል እየቆጠረ ከሙያው እንዲሸሽ ያደርገዋል ሲል አጠቃሏል።

ምስል KHALED DESOUKI/AFP/Getty Images
ምስል Yohannes G. Egiziabher/DW

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

 

ሽዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW