1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች ሥደት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ጥሪ

ሰለሞን ሙጬ
እሑድ፣ መስከረም 12 2017

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች እየገጠማቸው ነው ያለው ወከባ፣ እሥር፣ እንግልትና ማስፈራሪያ እየጨመረ መምጣት ​"በእጅጉ" እንዳሳሰበው አስታወቀ። የኢትዮ ኒውስ እና አልፋ ሚዲያ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛዎች መሥራቾች በላይ ማናዬ እና በቃሉ አላምረው ከኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ገልጸዋል

ከኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ያሳወቁት በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ
ከኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ያሳወቁት በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የፌድራል ምርመራ ቢሮ በኋላም በአፋር ክልል በሚገኘው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ታስረው ነበር። ምስል privat

የጋዜጠኞች ሥደት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ጥሪ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጋዜጠኞችን ጨምሮ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች እየገጠማቸው ነው ያለው ወከባ፣ እሥር፣ እንግልት፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እየጨመረ መምጣት ​"በእጅጉ" እንዳሳሰበው አስታወቀ። የመብት ተሟጋቹ ድርጅት በኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ እየተባባሰ መሆኑን የገለፀው ቀደም ሲል በተለያዩ መደበኛ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሲሰሩ የነበሩትና ኢትዮ ኒውስ እና አልፋ ሚዲያ የተባሉ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛዎችን አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ የቆዩት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን መግለፃቸውን ተከትሎ ነው።

ኢንተርኔትን መሠረት በማድረግ ሀገራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ በማቅረብ እና ትንታኔዎችን በማሰጠት ሲሠሩ የነበሩት የኢትዮ ኒውስ እና የአልፋ ሚዲያ መስራቾች ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ባለፈው ዓመት አፋር በሚገኘው አዋሽ አርባ ለረጅም ጊዜ ታስረው ነበር።

ጋዜጠኞቹ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ሰኔ ወር ላይ ከእሥር ከተለቀቁ በኋላ ግን ወደ ቀደመ ሥራቸው መመለስ እንዳልቻሉ ሰሞኑን ገልፀዋል። ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ሀገር ጥሎ ለመሰደድ ያስገደደው ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ጠይቀነዋል።

"የሕይወቴም ምኞት የነበረው በሀገሬ ሆኜ ሙያየን ተጠቅሜ ማገልገል ነበር። ይሄ በተደጋጋሚ ታግሼው የቆየሁት ቢሆንም አሁን ግን በተለየ መልኩ አንደኛ ለሕይወቴ አደጋ በሚሆን መልኩ የተሰጠኝ ማስጠንቀቂያ፣ ክትትል እና ዛቻ እንዲሁም ከሙያየ አፈንግጬ ለመሥራት እና ለመታዘዝ ዝግጁ አለመሆኔ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከሙያየ መውጣት አልፈልግም ስለዚህ በጋዜጠኝነቴ ለመቀጠል አካላዊ ነፃነት ማግኘት አለብኝ- ሙያየን ለማስቀጠል ነው"

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከጋዜጠኞች ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ ቀረበ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በሙያቸው ምክንያት "በተደጋጋሚ ለእሥር እና እንግልት የተዳረጉት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እና በቃል አላምረው ከእሥር ከተለቀቁም በኋላ በደረሰባቸው ጫና፣ ዛቻና ማስፈራሪያ የተነሳ በያዝነው ሳምንት ከሀገር መሰደዳቸውን ለድርጅታችን አሳውቀዋል" ሲል መስከረም ዘጠኝ ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ሲይዙ የመሻሻል አዝማሚያ አሳየ ተብሎ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን እና የጋዜጠኞች ነጻነት ባለፉት ዓመታት አሽቆልቁሏል። ምስል United Nations FAO 2024

ድርጅቱ "የዘፈቀደ እሥራት፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ እና ​እራስን ​ሳንሱርን ለማድረግ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን ጨምሮ እየተባባሰ የመጣው በጋዜጠኞች ላይ ሚደርስ ጫና ገሚሶቹን ሥራቸውን ትተው እንዲቀመጡ ያደረገ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እያስገደዳቸው መሆኑን ያሳያል" በማለት ያለውን ሁኔታ አመላክቷል።

ይህ ሁኔታ "በሀገሪቱ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ምህዳር የሚያጠብ፣ ሐሳብን ​በ​ነፃነት የመግለጽ መብትን፣ የሐሳብ ብዝሃነትን ​እና​ የማህበረሰቡን መረጃ የማግኘት መብትን የሚገድብ መሆኑን" በአፅንኦት መግለጽ ይወዳል ሲልም በመግለጫው አስታውቋል።

ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በመጀመርያ ለእሥር የዳረገው ምን እንደሆነ፣ ከእሥር ከወጣ በኋላ ወደ ሥራው ለመመለስ የገጠመው ችግር ምን እንደነበር ጠይቀነዋል።

የሚዲያ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጥሪ

"ጋዜጠኞችን እንደ ጠላት፣ ማንነታቸውን ሙያቸውንም የተለያየ ምክንያት እየተፈለገ እንደ ጠላት እና ለሥልጣን አስጊ እንደሆኑ፣ እኔ እበይንላችኋለሁ የሚል አካሄድ ነው የተከተለው [መንግሥት] እና ይሄ አጠቃላይ የፕሬስ ነፃነትን ፣ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን እያቀጨጨ መምጣቱን የሚያሳይ ነው"

ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ከ2012 ዓ.ም ወዲህ ሁለት ጊዜ ታሥራ ተፈቷል። አሁን ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት እንደ ሥጋት የሚታዩበት ሁኔታ የመፈጠሩ እውነታ እጅግ አሳዛኝ መሆኑንም ጋዜጠኛው ይናገራል።

ኢትዮጵያ ከስድስት ዓመታት በፊት - በ2018 እንደ ጎርገረሲያን አንድም ጋዜጠኛ ያልታሠረባት ሀገር በሚል የተሻለ የመገናኛ ብዙኃን ሥራ ዐውድ ያለባት ሀገር በሚል ተወድሳ ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW