1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እስር በኢትዮጵያ

እሑድ፣ ግንቦት 28 2014

እስከ ግንቦት 21 ቀን 2014 በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ከታሰሩ 19 ጋዜጠኞች የተፈታችው አንድ ብቻ ነች። ፍርድ ቤት የቀረቡ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመጠየቁ በእስር እንዲቆዩ ሆኗል። የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንዲፈቱ የቀረቡ ጥሪዎችም እስካሁን ፍሬ አላፈሩም። ይኸ ውይይት በእስሩ እና አንድምታው ላይ ያተኩራል

Symbolbild | Gefängnis
ምስል Ritzau Scanpix/imago images

እንወያይ፦ የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እስር በኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መረጃ መሠረት እስከ ግንቦት 21 ቀን 2014 ድረስ 19 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ከእነዚህ መካከል ሰለሞን ሹምዬ፣ መዓዛ መሐመድ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ እና መስከረም አበራ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። የቀረቡባቸው ፍርድ ቤቶች ፖሊስ በጠየቀው መሠረት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅደዋል። ከታሰሩ መካከል አንዷ ማለትም የፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ ባልደረባ የሆነችው ሰቦንቱ አሕመድ ግንቦት 22 ቀን 2014 በመታወቂያ ዋስትና ተለቃለች።

ይኸ የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እስር ከጋዜጠኞች፣ ከሙያ ማኅበራት እና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። በቁጥጥር ሥር የዋሉ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንዲፈቱ የቀረቡ ጥሪዎችም እስካሁን ይኸ ነው የሚባል ፍሬ አላፈሩም።

የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ በሥራው ምክንያት የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም ሲሉ ለጋዜጠኞች መብት ለሚሟገተው ሲፒጄ ተናግረዋል። ኃላፊው ከሲፒጄ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የታሰሩት ፖሊስ ወንጀል ለመፈጸማቸው ማስረጃ በማግኘቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ የእንወያይ መሰናዶ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር አብዲ ጅብሪል፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፍ ብርሀነ እንዲሁም ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ ተካፍለዋል።

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ተወካዮች በውይይቱ በመሳተፍ በጉዳዩ ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ በ-ኢሜይል እና በተደጋጋሚ በቀጥታ ስልክ በመደወል ሙከራ ቢደረግም ምላሽ አልተገኘም።

ሙሉ ውይይቱን የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW