የጋዜጠኞች፣ የሞያው እና የተቋማቱ ደኅንነት በኢትዮጵያ
ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017
ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 43 ጋዜጠኞች ተይዘው ለእሥር እና ለአፈና መዳረጋቸውን በጋዜጠኞች ደኅንነት ላይ የሚሠራው የኢንተርናሽናል ሚዲያ ሳፖርት (IMS) ጥናት አመለከተ ። የዳሰሳ ጥናቱ ለአንድ ዓመት ያህል፦ ከታኅሣሥ 22 ቀን፣ 2016 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 22 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ማድረጉንም ዓለም አቀፍ ድርጅቱ ጠቅሷል ። ዋና መቀመጫው ዴንማርክ የሆነውና አዲስ አበባ ውስጥ ጽሕፈት ቤት ያለው ይህ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የቀጠሉ ግጭቶች ጋዜጠኞችን ከመንግሥትም፣ ከታጣቂዎችም ለሚቃጣ እሥር፣ እገታ፣ ማስፈራራት፣ ማዋከብ እና ጥቃት ተጋላጭ አድርጓቸዋል ብሏል ። ብሔራዊ ደህንነት እና ብሔራዊ ጥቅም ጋዜጠኞችን ከሥራቸው እንዲቆጠቡ፣ ግጭቶችንም ከመዘገብ ራሳቸውን እንዲያቅቡ እንደ ማስፈራሪያ እያገለጉሉ መሆኑንም ድርጅቱ ባሰራጨው የጥናት ውጤት ላይ አመልክቷል።
ኢንተርናሽናል ሚዲያ ሳፖርት (IMS) ሰሞኑን ያሰራጨውና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጋዜጠኞች ደህንነት የተመለከተው የአንድ ዓመት የጥናት ውጤት፤ ጋዜጠኞች በአሳሳቢ ኹኔታ ለአካላዊ፣ ለአዕምሯዊ እና የበይነ መረብ ጥቃቶች ሰለባዎች መሆናቸውን በጉልህ ያሳያል።
እንደ የጥናት ውጤቱ "በጋዜጠኞች ላይ በተደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የተፈጠረው የፍርሐት ስሜት" ብዙኃን መገናኛዎች "ግጭቶችን እንዳይዘግቡ አድርጓል"። ይህ [የጋዜጠኞች ግጭቶችን አለመዘገብ] በከፊልም ቢሆን የጋዜጠኞችን ተጋላጭነት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል። ይህ ማለት ግን በብዙኃን መገናኛዎች የይዘት ልዩነት እና የሕዝብ ድምጽ ላይ ዐሉታዊ ተጽዕኖ አላሳደረም ማለት እንዳልሆነ ተመላክቷል።
ይህ የጥናት ውጤት መሬት ላይ ካለው ዕውነታ ጋር ምን ያህል ይመጋገባል ወይም ተጨባጭ ሐቁን ያሳያል ስንል የጠየቅነው ጋዜጠኛ መርሻ ጥሩነህ ፦ «እንደ አንድ ጋዜጠኛ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ነገር ትንሽ አስፈሪም አስደንጋጭም ነገር ነው» ብሏል ።
በ2024 ብቻ 43 ጋዜጠኞች ተይዘው ታስረዋል፣ ታፍነዋል - IMS
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥናቱ በተደረገበት "በ2024 ምንም እንኳን የጋዜጠኞች ግድያ ባይኖርም 43 ጋዜጠኞች አንድም ተይዘው ታስረዋል አልፎም ታፍነዋል" ያለው የድርጅቱ የጥናት ውጤት "በግጭቶች ምክንያት የብዙኃን መገናኛዎች ነፃነት ወደ ኋላ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ" ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ "ዝቅተኛ ደረጃ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ተሰልፋለች" ሲል አመልክቷል።
እንደ IMS የጥናት ውጤት ያለፈው ዓመት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በተነሱ የትጥቅ ግጭቶች፣ በትግራይ ክልል ባለው የፖለቲካ ውጥረት፣ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ፣ በተለያዩ ክልሎች በተስተዋሉ ሕገ-ወጥ የማዕድን ቁፋሮዎች ምክንያቶች በተለይም በቤንሻንጉል፣ በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድሮች "በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን አባብሰውታል"። ጋዜጠኛ መርሻ ጥሩነህ ይህንን ድምዳሜ ይጋራዋል።
በጋዜጠኞች እና ብዙኃን መገናኛዎች ጥቃት ፈጻሚው ማን ነው?
የ2024 የኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ደኅንነትን በገለልተኛ አካል ማስጠናቱን ያስታወቀው IMS "በኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኞች እና በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩን ያሳያል" ሲል ገልጿል። በኢትዮጵያ ያሉ ጋዜጠኞች "ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች በተጨማሪ በፖለቲካ ሰዎች እና በነጋዴዎች ጭምር ስለ ፖለቲካ፣ ግጭት፣ ንግድ እና ፋይናንስ በመዘገባቸው ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል" ተብሏል።
የጥናት ግኝቱ በአብዛኛው ወረዳ እና በቀበሌ ያሉ ባለስልጣናት በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ያሳያል። ከእሥራት፣ አፈና፣ ጾታዊ ጥቃት በተጨማሪ የገንዘብ እና የሕግ ማስፈራሪያዎችን የመሰሉ የደህንነት ሥጋቶች በመድረሳቸው ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት ሥራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጫና ደርሶባቸዋል። የችግሩ አሳሳቢነት በጉልህ ማደጉን የገለፁት የኢንተርናሽናል ሚዲያ ሳፖርት (IMS) የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ነጋሽ ተቋማቸው መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እና በዘላቂነትም ለመፍታት ጥናቶችን እንደሚያደርጉ እና ከሚመለከታቸው ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባ ነግረውናል።
በጥናቱ የተመላከቱ ምክረ ሐሳቦች
ኢንተርናሽናል ሚዲያ ሳፖርት (IMS) የኢትዮጵያ መንግሥት በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን የዘፈቀደ እሥራት እና ማስፈራሪያ ማቆም እና ጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛ ተቋማት በኅብረተሰቡ ውስጥ ወሳኝ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከለላ ማድረግ አለበት ብሏል። የብሔራዊ የጸጥታ አካላት በጋዜጠኞች ላይ አካላዊ፣ የበይነ መረብ እና የሞባይል ስለላዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በጋዜጠኞች ላይ ለሚፈፀመው ወንጀል ያለመከሰስ እርምጃ ማቆም አለበትም ብሏል። የሕግ አስከባሪ ተቋማት በጋዜጠኞች ላይ የሚነሱ ጥቃቶችን በብቃት፣ በገለልተኝነት እና በነጻነት በመመርመር በጋዜጠኞች እና በብዙኃን መገናኛዎች ላይ ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ እና ውጤቱን በይፋ ለማስታወቅ አስፈላጊውን 'ርምጃ ሁሉ መውሰድ አለባቸው ሲልም አመልክቷል።
ተቋሙ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተፋላሚ ኅይሎች ጋዜጠኞችን ከመጥለፍ፣ ከማንገላታትና ከማስፈራራት በመቆጠብ የጋዜጠኞችን መብት በማክበር፣ ጋዜጠኞች በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ እንዲሰማሩ በማድረግ ዜጎችን የሚጠቅም መረጃ በነፃ እንዲዘዋወር ማድረግ አለባቸው የሚሉና ሌሎች ምክረ ሐሳቦችንም አቅርቧል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ