የግል ባንኮች ቦንድ እንዲገዙ ያስገድድ የነበረው መመሪያ ምን አሳካ?
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 1 2012
ባለፈው ሳምንት አዋሽ ባንክ ለሚሰጠው ብድር የሚያስከፍለውን የወለድ ምጣኔ ከ0.5 በመቶ እስከ 4.5 በመቶ ዝቅ ማድረጉን አስታውቋል። የአዋሽ ባንክ የብድር ትንተና እና ፖርትፎሊዮ አስተዳደር ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቶሌራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር እና በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ባለወረቶች እና ኩባንያዎች ከባንኩ ሲበደሩ አነስተኛ ወለድ ከሚከፍሉት መካከል ይሆናሉ።
"በተለይ በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ላይ በመሠማራት፤ እሴት በመጨመር ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ በመላክ፤ የውጪ ምንዛሪ ለሚያስገኙ የኤኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛው የወለድ ቅናሽ ተደርጓል። ሁለተኛው በማምረቻው ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሐብቶች ወይንም ግለሰቦች ከፍተኛ የወለድ ቅናሽ የተደረገባቸው የኤኮኖሚ ዘርፎች ናቸው" ብለዋል።
«አዋሽ ትልቁ የግል ባንክ ነው። አዋሽ ከቀነሰ ሌሎቹ መከተላቸው አይቀርም» የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚገፋፋ ጥሩ ምልክት አድርገው ይቆጥሩታል።
አቶ ደሳለኝ ቶሌራ እንዳሉት አዋሽ ባንክ የብድር የወለድ ምጣኔውን ለመቀነስ ያበቁትን ሁለት ምክንያቶች አሉ። እርምጃው የኢትዮጵያን "የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል የራሱ የሆነ በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል" የሚል አመኔታ በባንኩ ዘንድ መኖሩ ለውሳኔው አንዱ ምክንያት ነው።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላለፉት ስምንት አመታት ሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ ማንሳቱ ነው። ይኸ መመሪያ ባለፈው ወር ሲሻር አዋሽን ጨምሮ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች እፎይታ ያገኙ ይመስላል። በመመሪያው መሠረት የግል ባንኮች ለደንበኞቻቸው ካበደሩት አጠቃላይ የገንዘብ መጠን በ27 በመቶው ከብሔራዊ ባንክ ቦንድ ሲገዙ ቆይተዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት በዚሁ መመሪያ ሳቢያ የግል ባንኮች መንግሥት ያዘዛቸዉን የ116 ቢሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል።
«በጣም ጥብቅ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ የዛሬ አራት እና አምስት አመታት አካባቢ የግል ባንኮችን የጥሬ ገንዘብ ክምችት እስከ ማውረድ ደርሷል። ሁለተኛው ተፅዕኖ ደግሞ ባንኮቹ የሚያበድሩት ገንዘብ ትንሽ ስለሆነ የወለድ መጠናቸውን ጨምረዋል። የግል ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የገዙት የ116 ቢሊዮን ብር ቦንድ ነው። 30 ቢሊዮን ብር ተመልሶላቸዋል፤ 86 ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ አልተመለሰም» ሲሉ መመሪያው ያሳደረውን ተፅዕኖ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
«የግል ባንኮች በመንግሥት ላይ የሚያቀርቡት ትልቁ የቅሬታ» ምንጭ ይኸው መመሪያ እንደነበረ የአዋሽ ባንክ የብድር ትንተና እና ፖርትፎሊዮ አስተዳደር ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቶሌራ አስታውሰዋል።
"የብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዢ ከመጣበት ከ2011 ዓ.ም. [በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር] ጀምሮ እስከ ባለፈው ወር [ጥቅምት] ድረስ አዋሽ ባንክ 17.1 ቢሊዮን ብር [ቦንድ] ገዝተናል። በየወሩ በምንሰጠው ብድር ላይ 27 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዢ እናውላለን። ከዚህ ውስጥ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ አምስት አመት የሞላቸውን ብሔራዊ ባንክ ሲከፍለን ነበረ። በዚህ መሰረት የተወሰነው ተከፍሎ ዛሬ 12.1 ቢሊዮን ብር በብሔራዊ ባንክ እጅ ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
ይኸ መመሪያ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ የግል ባንኮች ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ አቅርበው ነበር። የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር መመሪያው ተግባራዊ ከሆነ ከዘጠኝ ወራት ግድም በኋላ እንዲከለስ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ባለሙያዎች ያስታውሳሉ። መመሪያው በባንኮች ላይ ያሳደረውን ጫና ይተቹ ከነበሩ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አብዱልመናን ልማታዊ መንግሥትነትን የሚያቀነቅነው ሥርዓት ለባንኮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ለባለሙያዎች ውትወታ መልስ ሳይሰጥ መቆየቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ብዙ አቤቱታ ነበረ፤ ብዙ ተፅፏል። ከነ ዓለም ባንክ፤ የዓለም የገንዘብ ድርጅት፤ እኔ እና የባንክ ማኔጀሮችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ይኸን ጉዳይ አንስተውታል። መንግሥት ሊሰማ አልፈለገም» ብለዋል።
የቀድሞው የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚንስትር አቶ ሱፊያን አሕመድ እንዲሁም በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሹማምንት መንግሥታቸው የተከተለው መመሪያ የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት ለመቀየር ያቀደ ነው እያሉ ትችቶቹን ሲከላከሉ ቆይተዋል። ከግል ባንኮች በመመሪያው መሠረት በቦንድ ግዢ ወደ መንግሥት እጅ የሚገባው ገንዘብ የአገሪቱን የኢንዱስትሪ እና ትልልቅ የመንግስት ውጥኖችን ለመደጎም የታቀደ ነበር። በኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ መሠረት ለግዙፎቹ የልማት ውጥኖች የረዥም ጊዜ ብድር የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሲሆን የገንዘብ ፍላጎቱን በቦንድ ሽያጭ ለማሟላት ታስቧል።
«አንደኛው ጥያቄ ካልተመለሰው 86 ቢሊዮን ብር ልማት ባንክ ምን ያህል ደረሰው? ነው። ቢያንስ ሁለት ሶስተኛው በብሔራዊ ባንክ እጅ ነው። ወደ ልማት ባንክ አልተዘዋወረም። ለምን ልማት ባንክ ያን ያህል ገንዘብ ስለማይፈልግ። ልማት ባንክ ደግሞ ከደረሰው ራሱ ምን ያህሉን ለረዥም ጊዜ ብድር አውሎታል? የሚለው በጣም አጠያያቂ ነው። ምንአልባት ግማሽ ያህሉን ቢያውለው ነው» ሲሉ ይናገራሉ።
«ልማት ባንክ ከሰጣቸው የረዥም ጊዜ ብድሮች እስከ 40 በመቶው የተበላሸ ብድር ነው የሆነበት። ዝናብ ላይ ጥገኛ ለሆነ ግብርና የሰጠው ብድር የከፋ ችግር ያለበት ነው። የጋምቤላ የእርሻ ብድሮችም የከፋ ችግሮች ያለባቸው ናቸው። በአጠቃላይ ስናየው ከ86 ቢሊዮን ብር ግማሽ ያህሉ ነው ለብድር የዋለው። ልማት ባንክ ከተላከለት ገንዘብ መጠቀም ስላልቻለ ከመንግሥት የግምዣ ቤት ሰነድ ነው የገዛበት። ከሁለት በመቶ በታች ነው ወለድ የሚገኝበት። ልማት ባንክ ግን አሁን ባለው የወለድ ምጣኔ በቦንዱ 5 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ ይከፍላል። ብሔራዊ ባንክ ደግሞ አምስት በመቶ ለግል ባንኮቹ ይከፍላቸዋል» ሲሉ አቶ አብዱልመናን መንግሥት የተከተለው መንገድ የገባበትን ውጥንቅጥ ይገልጹታል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) መንግሥታቸው መመሪያውን በመሻር ከወሰደው እርምጃ በኋላ ባንኮች ለሚሰጡት ወለድ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን ዝቅ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
"ይኸን ማድረጋችን በባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሳይኖርባቸው ለግሉ ዘርፍ የተሻለ ብድር ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ፤ በሌላ በኩል በቅርቡ ለምንጀምረው የመንግሥት ግምጃ ቤት ገበያ (government treasury bill) [ግብይት] ባንኮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ ነው። ይኸ መመሪያ እንዲቀር መደረጉ የባንኮችን ለአመታት የቆየ ጥያቄ የሚፈታ በመሆኑ ባንኮች አሁን በሥራ ላይ ያለውን ወለዳቸውን ዝቅ እንደሚያደርጉ ወይም ደግሞ በተመጣጣኝ ወለድ አገልግሎት እንደሚያግዛቸው ስለምንረዳ ይኸንንው ታሳቢ በማድረግ ባንኮች ለብድር የሚያስከፍሉትን ወለድ ዝቅ እንዲያደርጉ ይጠበቃል"
አቶ አብዱልመናን የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ የተጀመሩ ምጣኔ ሐብታዊ ማሻሻያ አንድ አካል ነው የሚል ዕምነት አላቸው። «ይኸ የኤኮኖሚ ማሻሻያው አንድ አካል ነው። ኤኮኖሚውን ነፃ ማድረግ ካስፈለገ በባንኮች ላይ የተጫነው ጫና መነሳቱ የማይቀር ጉዳይ ነው» ብለዋል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ