1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግብጽ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደት

ቅዳሜ፣ መስከረም 26 2016

ከተቃዋሚው ከታንታዊ የምርጫ ዘመቻ አባላት ቢያንስ 73ቱ ከአሸባሪ ቡድን ጋር አብራችኋል፤የሀሰት ዜና አሰራጭታችኃል፤ እንዲሁም ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን አለአግባብ ተጠቅማችኋል ተብለው መያዛቸው ተረጋግጧል። ስለጉዳዩ የተጠየቀው የግብጽ ብሔራዊ የምርጫ ባለሥልጣን ፣ በሰዎቹ ላይ ደረሰ የተባለውን በሙሉ «መሠረተ ቢስና የሀሰት ክስ» ሲል አጣጥሏል።

እስከሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ በሚካሄደው የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እስካሁን የ68 ዓመቱ ፕሬዝዳንት አልሲሲ እና 7 እጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል። ታዛቢዎች አል ሲሲ ማሸነፋቸው አያጠራጥርም እያሉ ነው።
በታዋቂ ጎዳናዎች ላይ ይሰቀሉ የነበሩ የንግድ ማስታወቂያዎች በደጋፊዎቻቸው አማካይነት የግብጹን ፕሬዝዳንት የአብደል ፈታህ አልሲሲን ምስሎች በያዙ ፖስተሮች መቀየር ጀምረዋል።ምስል፦ Amr Nabil/AP Photo/picture alliance

የግብጽ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደት

This browser does not support the audio element.

የግብጽ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 10 እስከ ታኅሳስ 12 ቀን 2023 ዓም እንደሚካሄድ ይፋ ከተደረገበት ወዲህ ሀገሪቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ምርጫ ድባብ ገብታለች። በታዋቂ ጎዳናዎች ላይ ይሰቀሉ የነበሩ የንግድ ማስታወቂያዎች በደጋፊዎቻቸው አማካይነት የግብጹን ፕሬዝዳንት የአብደል ፈታህ አልሲሲን ምስሎች በያዙ ፖስተሮች መቀየር ጀምረዋል። የዶቼቬለዎቹ ጀነፊር ሆሌይስ እና መሐመድ ሁሴን እንደዘገቡት እስከሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ በሚካሄደው የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እስካሁን የ68 ዓመቱ ፕሬዝዳንት አልሲሲ እና 7 እጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል። ታዛቢዎች አል ሲሲ ማሸነፋቸው አያጠራጥርም እያሉ ነው። መቀመጫውን ዋሽንግተን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው « ለመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ የታህሪር ተቋም» ምክትል ሃላፊ ቲሞቲ ኢ ካልዳስ ይህንኑ ያጠናክራሉ። 
«እርግጥ ነው እጩዎቹ ምርጫውን የማሸነፍ እድል የላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ የሚፎካከሩበት እድል አልተሰጣቸውም።በግልጽ ለመናገር ፉክክር ያለበት ምርጫ ቢሆን ሲሲ ከመጠን በላይ ተጋላጭ ይሆኑ ነበር።  ነጻ እና ትክክለኛ የምርጫ ድባብ ቢኖር ኖሮ ግብጽ የሚገኙ ምንም ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎች እርሳቸውን የመገዳደር በቂ እድል ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ።»
በምርጫው ተስፋ አላቸው የተባሉት አልካራማ የተባለው የግራው ፓርቲ የቀድሞ መሪ አህመድ ታንታዊ እና የነጻው ዶስቱር ወይም «ሕገ መንግሥት» የተባለው ፓርቲ ሊቀ መንበር ጋማልያ ኢስማኤል ደጋፊዎቻቸው ወከባ እንደሚደርስባቸው እና በባለስልጣናት እንደሚመረመሩ ተናግረዋል። መቀመጫውን ካይሮ ያደረገው የግብጾች የግል መብቶች ተነሳሽነት ድርጅት በምህፃሩ EIPR ከታንታዊ የምርጫ ዘመቻ አባላት መካከል ቢያንስ 73ቱ ከአሸባሪ ቡድን ጋር አብራችኋል፤የሀሰት ዜና አሰራጭታችኃል፤ እንዲሁም ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን አለአግባብ ተጠቅማችኋል ተብለው መያዛቸውን አረጋግጧል። ስለጉዳዩ የተጠየቀው የግብጽ ብሔራዊ የምርጫ ባለሥልጣን ፣ በሰዎቹ ላይ ደረሰ የተባለውን በሙሉ መሠረተ ቢስና የሀሰት ክስ ሲል አጣጥሏል። ይህ በየግብጽ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንዲህ እንዳለ ማዳር ማረስ የተባለው ብቸኛው በመንግሥት ስር ያልሆነው መገናኛ ብዙሀን ደግሞ የታንታዊ ስልክ ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ጊዜያት መጠለፉን ዘግቧል።አነጋጋሪው መጪው የግብፅ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ
አል ሲሲ የተቆናጠጡት ሥልጣን 
መቀመጫው ለንደን የሆነው «አዙር» ስትራቴጂ የተባለው የጂኦ ፖለቲካና የፀጥታ አማካሪ ድርጅት ሃላፊ አሊስ ጎወር የዘንድሮው ምርጫ ከዛሬ 5 ዓመቱ ይለያል ብለው አያምኑም ።አል ሲሲ፣ በጎጎሮሳውያኑ 2011 ዓመተ ምኅረቱ የአረቡ ዓለም አብዮት ወቅት በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የያዙትን «የሙስሊም ወንድማማቾች» ፓርቲውን ሞሐመድ ሙርሲን በመፈንቅለ መንግሥት ካስወገዱበት ከጎርጎሮሳዊው 2013 አንስቶ ሥልጣን ላይ ናቸው። ከዚያን ወዲህ በጎርጎሮሳዊው 2014 እና በ2018 በግብጽ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ታዛቢዎች እንደሚሉት ሁለቱም ምርጫዎች ትክክለኛነት ይጎድላቸዋል። አል ሲሲ በ2019 ፣አንድ ፕሬዝዳንት ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር እንዲችል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ ሥልጣናቸውን አጠናክረዋል። በማሻሻያው የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመን ከአራት ወደ ስድስት ዓመት አድጓል ። በዚሁ መሠረት አል ሲሲ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ካሸነፉ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 ሥልጣን ላይ ይቆያሉ ማለት ነው። አል ሲሲ በሀገራቸው ምክር ቤት ግብጻውያን ዴሞክራሲያዊ ያሉትን መድረክ እንዲያዩ እና ለቦታው ትክክለኛውን ሰው እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል። የታኅሳሱን ምርጫ ቲያትር ያሉት ካላዳስ ሀገሪቱ በተዘፈቀችባቸው ችግሮች የተማረረው ህዝቡ ከአል ሲሲ የተለየ ፕሬዝዳንት እንዲመረጥ ይፈልጋል ብለዋል።
«እርግጥ ነው በአንዳንድ ሁኔታዎች አካሄድ ፣ በተለይ የኤኮኖሚው እና የአብዛኛዎቹ ግብጻውያን የኑሮ ደረጃ ማሽቆልቆል፣ በአመራሩ ላይ ህዝባዊ ቅሬታዎች እያስነሳ ነው። የግብጻውያን የመግዛት አቅም ሲሽመድመድ ያዩ ግብጽ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የተለየ ፕሬዝዳንት ቢያስቡ አይገርምም። »
የግብጽ ወቅታዊ የፋይናንስ ሁኔታ 
ግብጽ ለዓመታት በኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ደግሞ ስንዴ ከውጭ በምታስገባው በግብጽ ላይ የፋይናንሱን ቀውስ አባብሶታል።በሀገሪቱ ባለፈው ዓመት የምግብ ዋጋ በ72 በመቶ አሻቅቦ ነበር። የዓለም የገንዘብ ድርጅት የግብጽ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት አጠቃላይ ገቢ እድገት በጎርጎሮሳዊው 2023 ፣ 3.7 በመቶ ብቻ ይሆናል ሲል ተንብየዋል። በ2022 ግን 6.7 በመቶ ነበር።ሀገሪቱ 39 በመቶ ከደረሰው የዋጋ ግሽበትም ጋር እየታገለች ነው። የግብጽ ገንዘብ ፣የመግዛት አቅም ደግሞ ከየካቲት 2022 አንስቶ  ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ መቀነሱን የግብጽ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ድርጅት አስታውቋል።

ሀገሪቱ 39 በመቶ ከደረሰው የዋጋ ግሽበትም ጋር እየታገለች ነው። የግብጽ ገንዘብ ፣የመግዛት አቅም ደግሞ ከየካቲት 2022 አንስቶ  ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ መቀነሱን የግብጽ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ድርጅት አስታውቋል።ምስል፦ Amr Abdallah Dalsh/REUTERS
አል ሲሲ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ካሸነፉ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 ሥልጣን ላይ ይቆያሉ ማለት ነው። አል ሲሲ በሀገራቸው ምክር ቤት ግብጻውያን ዴሞክራሲያዊ ያሉትን መድረክ እንዲያዩ እና ለቦታው ትክክለኛውን ሰው እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል። ምስል፦ Amr Abdallah Dalsh/REUTERS


ግብጽ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር ባለፈው ሐምሌ 2022 ዓም የ3 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ብትፈራረምም ፣ እስካሁን ያገኘችው ብድር 347 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ምክንያት የተባለው ሀገሪቱ የሚጠበቅባትን የወጪ ቅነሳ እና ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አለማድረጓ ነው ።ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀገሪቱ  የውጭ ምንዛሬ ክምችት ሙሉ በሙሉ ተሟጧል እየተባለ ነውል። በዚህ መሀል አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት በምርጫ ዘመቻ ላይ የሰጡት ከሰጡት እንግዳ አስተያየት ውስጥ  «ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና የሚከፈለው ዋጋ ረሀብና ጥማት ከሆነ ፣ አንብላ አንጠጣ »  ማለታቸው ብዙዎችን አበሳጭቷል። ተቃዋሚው ታንታዊ ለዚህ የአል ሲሲ አባባል በሰጡት መልስ ግብጻውያን የተራቡት በአስተዳደርዎ ምክንያት በርስዎ አመራር ወቅት ነው ብለዋቸዋል። የግብጽ ዓለም አቀፍ አጋሮችም ከቀድሞ በበለጠ መንግሥትን መተቸትና ጥሪዎችን ማቅረብ መጀመራቸውን ካልዳስ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።.የግብጽ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ
«በግልጽ ለመናገር በርካታ የግብጽ አጋሮች በተለይ የግብጽ አጋር የሆኑ የባህረ ሰላጤው አገራት ለምሳሌ ሀገሪቱ በምትመራበት መንገድ እንዳልረኩ በይፋም ይሁን በግል ግልጽ አድርገዋል።የግብጽ ምዕራባውያን አጋሮች መንግሥት በጫም እየተቹ ነው። በርግጥ ያም በቂ የሚባል አይደለም። እውነታው በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎች የግብጽን አመራር አይመለከቱም ለማጽደቅም ዝግጁ አይደሉም።»
የግብጽ የሰብዓዊ መብት አያያዝ 
 ግብጽ የምትፈተነው በኤኮኖሚ ብቻ አይደለም ፤ በደካማ የሰብዓዊ መብቶች አያያዟ ጭምር እንጂ። በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግምት፣ ቁጥራቸው ከ65 ሺህ እስከ 70 ሺህ ይደርሳል የተባሉ የፖለቲካ እስረኞች፣ ለፍርድ ያልቀረቡ ሰዎች በሚያዙባቸው እስር ቤቶች ውስጥ ናቸው፤ ወይም በኢፍትሀዊ ፍርድ በግብጽ እስር ቤቶች ይገኛሉ። የማዳር ማርስ መገናና ብዙሀን ዋና አዘጋጅ ሊና አታላህ
«የምንናገረው ስለ ክሶች ነው። የምንናገረው ከፍርድ በፊት ስለመታሰር ነው።የምንናገረው ከሕግ ውጭ ስለተፈጠረ እሥርና ስለመሳሰሉት ነው። ብዙውን ጊዜ ደግሞ የሚቀርቡባቸው ክሶች በጣም ተመሳሳይ ናቸው። ይኽውም «ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ አሸባሪዎችን መደገፍ ፣የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት ፣የሚሉ ናቸው። የመረጃ ፍሰትን ከማስተካከል ይቅል ፣ የተሳሳተ መረጃን፣ የመጨቆኛ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ነው የሚካሄደው። አፈናው በሌሎች የተለያዩ መንገዶችም ይከናወናል።የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ስራዎች በመገደብ፣ ፈቃድ መስጠትንና ፣ መደራጀትን በጣም በጣም አስቸጋሪ በማድረግ ጭምር። እነዚህ አሰራሮች ባለፉት አሥር ዓመታት የፖለቲካ ምኅዳሩን በእጅጉ ሸርሽረውታል።»
ምርጫ ሲቀርብ ደግሞ እርምጃው እንደገና ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሪድሬስ የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅትና የግብጽ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳሉት ደግሞ የግብጽ ባለሥልጣናት ሰዎችን ቁም ስቅል ማሳየት ተስፋፍቷል። ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር የሚስተካከል ነው ሲሉ በጋራ ባወጡት ሕጋዊ ትንታኔ በያዘ ዘገባ አስታውቀዋል። ይኽው ዘገባ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 14 እና 15 የግብጽን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለሚገመግመው የተመድ ፀረ-ቁም ስቅል ኮሚቴ ቀርቧል። ማዳ ማርስ የተባለው መገናና ብዙሀን ዋና አዘጋጅ አታላህ እንዳሉት በግብጽ አፈናና እስር በተለይ በተቃዋሚዎች ላይ ተደጋግሞ ይፈጸማል።
«ባለፉት አሥር ዓመታት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንዳይናገሩ ማፈን በተለያየ መንገድ ሲፈጸም ቆይቷል።ከሁሉ የሚጎላው የፖለቲካ አራማጆች ወይም ጋዜጠኞች አለያም የቀድሞ የፓርላማ አባላት ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች የሚበየንባቸው እሥር ነው። 

አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት በምርጫ ዘመቻ ላይ የሰጡት ከሰጡት እንግዳ አስተያየት ውስጥ  «ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና የሚከፈለው ዋጋ ረሀብና ጥማት ከሆነ ፣ አንብላ አንጠጣ »  ማለታቸው ብዙዎችን አበሳጭቷል። ምስል፦ AFP


ጀነፊር ሆሌይስ/መሐመድ ሁሴን

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW