የግብፅ ብጥብጥ፤ የአካባቢዉ ሀገራትና አዉሮጳ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2005ማስታወቂያ
የአዉሮጳ ሕብረት በግብፅ ጦር ሐይል በተመሠረተዉ ጊዚያዊ መንግሥት ላይ ሥለሚወስደዉ እርምጃ የአባል ሐገራት ባለሥልጣናት እየተነጋገሩ ነዉ።የግብፅ ጦር ሐይል ካለፈዉ ሮብ ጀምሮ ተቃዋሚ ሠልፈኞችን መግደሉን ሕብረቱና የሕብረቱ አባል ሐገራት አዉግዘዋል።
በተያያዘ ዜና፤በግብፅ ጦር ሐይል የተመሠረተዉ ጊዚያዊ መንግሥትና ጦሩ ያደረገዉን መፈንቅለ መንግሥት በሚቃወመዉ በሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበረሰብ መካካል የሚካሔደዉ ደም አፋሳሽ ግጭት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ። የግብፅ ፀጥታ አስከባሪዎች የሙስሊም ወንድማማቾች መሪ መሐመድ ባዲን አስረዋቸዋል። ማሕበሩ እስካሁን ምክትል መሪዉ የነበሩትን መሐመድ ኢሳት የመሪነቱን ሥልጣን እንዲይዙ መወሰኑን አስታዉቋል። ማሕበሩ ዛሬ ባወጣዉ መግለጫዉ እንዳስታወቀዉ ጦር ሐይሉ በሚወስደዉ የማሠርና የሐይል እርምጃም ትግሉ አይቋረጥም።መፈንቅለ መንግሥቱን ከሚደግፉት የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ ሐገራት አንዷ የሆነችዉ ኩዌት ደግሞ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር አባላት ያለቻቸዉን ግብፃዉያንን አባራራች።ቱርክ በበኩሏ በግብፁ መፈንቅለ መንግሥት የእስራኤል ዕጅ አለበት በማለት ወንጅላለች።
ነብዩ ሲራክ/ ገበያዉ ንጉሴ
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ