1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግብፅ አስገዳጅ የውኃ ክፍፍል ውል ጥያቄ "የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያሻው ነው" - ባለሙያ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2018

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ግብፅ በናይል ውኃ ላይ አለኝ የምትለው መብት በአስገዳጅ የውል ስምምነት እንዲታሰር ተሰምቷል። ኢትዮጵያ በአንፃሩ ይህ ጉዳይ በናይል ተፋሰስ ሀገራት ማዕቀፍ ውስጥ መታየት ያለበትና ከሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ያለፈ ሀሳብ መሆኑን በመጥቀስ ፍትሐዊ ክፍፍል መደረግ አለበት በሚል የግብፅን አቋም ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

ሕዳሴ ግድብ
ሕዳሴ ግድብ ምስል፦ Luis Tato/AFP

የግብፅ አስገዳጅ የውኃ ክፍፍል ውል ጥያቄ "የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያሻው ነው" - ባለሙያ

This browser does not support the audio element.

 

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ግብፅ በናይል ውኃ ላይ አለኝ የምትለው መብት በአስገዳጅ የውል ስምምነት እንዲታሰር ቅዳሜ ዕለት ደግመው ማናገራቸው ተሰምቷል። ኢትዮጵያ በአንፃሩ ይህ ጉዳይ በናይል ተፋሰስ ሀገራት ማዕቀፍ ውስጥ መታየት ያለበት እና ከሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ያለፈ ሀሳብ መሆኑን በመጥቀስ ፍትሐዊ ክፍፍል መደረግ አለበት በሚል የግብፅን አቋም ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች። አልሲሲ ሀገራቸው "ለውይይት እና ለፖለቲካዊ መፍትሔዎች ቁርጠኛ መሆኗን" የገለፁ ቢሆንም ከሕዳሴ ግድብ ድርድር እና የውይይት ማዕቀፎች ከወጣች ቆይታለች። ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀድሞ ተደራዳሪዎች አንዱ ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን በሚመለከት የግብፅ መንግሥት እና ሕዝብ "ይህ ውኃ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት ነው የሚል የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለባቸው።" 

ግብፅፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሱሲ ሰሞኑን ካይሮ ውስጥ በተደረገ እና የአፍሪካ ሚኒስትሮች እና የልዑካን ቡድን መሪዎች በተገኙበት የሩሲያ-አፍሪቃ አጋርነት መድረክ ሁለተኛ ጉባኤ ላይ አደረጉት በተባለው ንግግር ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት "ብቸኛ አለመግባባት የናይል ውኃ መብቷን መጠበቅ እና በኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ላይ በሕጋዊ መንገድ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ" ስለመሆኑ ተጠቅሷል።

አልሲሲ ካይሮ "ለውይይት እና ለፖለቲካዊ መፍትሔዎች ቁርጠኛ መሆኗን አፅንዖት ሰጥተዋል" የተባለ ቢሆንም እስካሁን ስድስት የናይል ተፋሰስ ሀገራት የፈረሙትን የ2015ቱን የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የስምምነት ማዕቀፍ (CFA) አልፈረመችም። አለመግባባቶችን በውይይት መፍታትን በሚመለከት ኢትዮጵያ መወያየት ከተፈለገ ዝግጁ መሆኗን ደጋግማ ገልጻለች። የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ በቅርቡ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያም ይህንኑ አረጋግጠው ነበር።

ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን የቀድሞ አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ሰሞነኛው የግብፅ አቋም "አዲስ ነገር" እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። እንዴት? የሚለውን ሲመልሱም ግብፅ ድሮውንም "ውኃችንን አትንኩ" የሚል ወደ "አስገዳጅ የውል ስምምነት እንግባ" የሚል የአንድ ወገን ጥቅም ብቻ የሚያስከብር አቋም ስታራምድ ዓመታት መቆጠሩን በመግለጽ ነው።

የግብፁ ፕሬዚዳንት ኧብደል ፈታህ አልሲሲምስል፦ John Macdougall/AP Photo/picture alliance

"ውኃውን አትንኩብን ነው። ልማት አታልሙ ነው" እያሉ ያሉት።

አልሲሲ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አለመግባት መሆኑን መናገራቸው ተጠቅሷል። ይሁንና ግብፅ ኢትዮጵያን በማበጣበጥ፣ በውስጥ ጉዳይ ገብታ ታጣቂዎችን በመደገፍ እና በእጅ አዙር በማጥቃት ትጠረጠራለች። የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን የቀድሞ አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ እንደሚሉት ግብፅ የምትለውን ስምምነት መፈረም ማለት በቀጥታ "ባርነት ውስጥ መግባት ነው።"

 

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW