የግብፅ ወቅታዊ ሁኔታና ዓለም አቀፍ አስተያየት፣
ሐሙስ፣ ነሐሴ 9 2005ማስታወቂያ
በግብፅ ፣ የሽግግሩ መስተዳድር ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ፣ ከሥልጣን የተወገዱት ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ደጋፊዎች ፣ ካይሮ ውስጥ በከተማይቱ አንዳንድ አደባባዮች ከመሸጉባቸው ጣቢያዎች እንዲለቁ ለማስገደድ በወሰዱት እርምጃ የብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እንደታወቀ፤ የአፍሪቃ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽን፤ ያቋቋመውን አጥኚ ቡድን ፤ በአፋጣኝ ልኳል። የግብፅን ወቅታዊ ይዞታ በተመለከተ፣ በዚያው በአፍሪቃ ኅብረት ምክክር መደረጉም ታውቋል።
ትናንት ፣ የግብፅ ፖሊስና ወታደር 12 ሰዓት ያህል በወሰደው የኃይል እርምጃ እንደ ሙስሊም ወንድማማች ማኅበር መግለጫ ከሆነ ከ 2,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሺ የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል።የሽግግሩ መንግሥት በበኩሉ፤ 43 ፖሊሶች እንደተገደሉበት ያስታወቀ ሲሆን፤ ገለልተኛ የዜና አውታሮች፣ ቢያንስ ከ 250 በላይ ተገድለዋል ይላሉ። ባሁኑ ወቅትም፣ በካይሮና በሌሎች 11 ከተሞች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣ ሲሆን የሰዓት እላፊ ገደብም ተጥሏል። ከአካባቢው የሚገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሁኔታው አስፈሪና አሳሳቢ ነው።
ጌታቸው ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ/ገበያው ንጉሤ
ተክሌ የኋላ
ሂሩት መለሰ