የግንቦት 14 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 14 2015ዘንድሮ አይበገሬነቱን ያስመሰከረው ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን መውሰዱን አረጋግጧል ። ከሻምፒዮንስ ሊግ እና የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታዎችም ሁለት ዋንጫዎችን ለመሰብሰብ የመጨረሻ የፍጻሜ ግጥሚያዎች ብቻ ይቀሩታል ። ሊቨርፑል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የመግባት እድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ። ጭላንጭል እድሉ ለኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ በደረሰው ማንቸስተር ዩናይትድ ሁለት ጨዋታዎች ይወሰናል ። በማንቸስተር ሲቲ ከሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የተሰናበተው ሪያል ማድሪድ ትናንት በቫለንሺያ ዳግም ሽንፈት ገጥሞታል ። ብራዚሊያዊው የሪያል ማድሪድ አጥቂ ቪንሺየስ ጁኒየር በቆዳ ቀለሙ ለደረሰበት የዘረኝነት ስድብ ላሊጋ እና ስፔን ዘረኞች ሲል ምላሽ ሰጥቷል ። ትናንት ስታየም ውስጥ ተመልካቾች ከጥግ እስከ ጥግ የዘረኝነት ስድብ ሲያስተጋቡበት ነበር ። በጨዋታው መገባደጃ አንገቱን ክርኑ ውስጥ አስገብቶ ሲጎትተው የነበረውን ተጨዋች አንገቱ ላይ በማመናጨቅ በመሰንዘሩ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
አትሌቲክስ
ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው እና በርካታ ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተገኙበት 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በትናንትናው እለት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተጠናቋል ። ይህ አንጋፋ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ1963 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል ። የዘንድሮው ፉክክር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከግንቦት 8-13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት መካሄዱ ተገልጧል ። በዘንድሮው ውድድር ከ11 ክልሎችና የከተማ አስተዳዳሮች ከ30 ቡድኖች እና ተቋማት የተውጣጡ 1,270 አትሌቶች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘግቧል ።
ለስድስት ቀናት የተከናወነው ውድድር ሦስት ዓላማዎችን ያነገበ እንደነበር ፌዴሬሽኑ ገልጧል ። ከሦስቱ ዓላማዎቹም 1ኛው፦ ከሦስት ወራት በኋላ ከነሐሴ 13 እስከ ነሐሴ 21 ቀን፣ ድረስ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች አቋማቸውን እንዲለኩ እድል ለመፍጠር ነው ። ለመሆኑ ለአንድ ሳምንት ከተካሄደው ውድድር እንደተባለው ለቡዳፔስቱ ፉክክር ተስፋ የሚጣልባቸው ምን ያህል አትሌቶች ተገኙ?
በክልሎች፣ በከተማ አስተዳድሮች፣ በቡድኖችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል መፍጠር፤ እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ሌሎቹ የውድድሩ ዓላማዎች ነበሩ ። ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ረገድስ ምን አይነት እመርታ ታይቷል? በኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮ ስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ምሥጋናው ታደሰ ውድድሮቹን በአጠቃላይ ተከታትሏል ። ለቡዳፔስት ፉክክር በወንድም በሴትም አዳዲስ ተስፋ የተጣለባቸው አትሌቶች ብቅ ማለታቸውን ገልጧል ።
ፕሬሚየር ሊግ
ኤቲሀድ ስታዲየም ትናንት በሰማያዊ እና ነጭ ቀለማት አሸብርቆ የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎችን ሲያስፈነድቅ አምሽቷል ። ምክንያት? ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የዘንድሮ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን መውሰዱ ። ማንቸስተር ሲቲ በዘንድሮ የዓመቱ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሦስት ዋንጫዎችን ለመውሰድ ጫፍ ደርሷል ። የአንዱ ጉዳይ ተፈጽሟል ። የቀሩት ሁለት ዋንጫዎች ጉዳይ የቅዳሜ ሳምንት በኤፍ ኤካፕ ከማንቸስተር ዩናይትድ፤ ከዚያ በሳምንቱ ደግሞ በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ከኢንተር ሚላን ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ይወሰናሉ ።
በትናንቱ ግጥሚያ ጁሊያን አልቫሬዝ በ12ኛው ደቂቃ ቸልሲ ላይ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ማንቸስተር ሲቲ የዘንድሮ ዋንጫን መውሰዱን ያረጋገጠባት ነበረች ። ማንቸስተር ሲቲ ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታዎቹ ከብራይተን እና ከብሬንትፎርድ ጋር ነው ። 7ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ብራይተን ግጥሚያው የሞት ሽረት ነው ። ከሊቨርፑል የአውሮጳ ሊግ ቦታን ለመቀማት ግን ማንቸስተር ሲቲንም ሆነ አስቶን ቪላን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ።
በአንጻሩ ሊቨርፑል ከሳውዝሀምፕተን ጋር ያለውን ቀሪ የመጨረሻ ጨዋታ ካሸነፈ የአውሮጳ ሊግ ቦታውን የሚቀማው የለም ። ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያልፈው ግን ማንቸስተር ዩናይትድ ከቸልሲ እና ከፉልሃም ጋር የሚያደርጋቸውን ቀሪ ጨዋታዎች ከተሸነፈ ነው ። ይህ የመሆን እድሉ ደግሞ እጅግ ጠባብ ነው ። በዚህም መሠረት ማንቸስተር ሲቲ አንደኛ፤ አርሰናል ሁለተኛ እንዲሁም ዛሬ ማታ ሁለተኛ ተስተካካይ ጨዋታውን ከላይስተር ሲቲ ጋር የሚያደርገው ኒውካስል ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሳውዝሀምፕተን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረዱን አረጋግጧል ። ከኤቨርተን፤ ሊድስ ዩናይትድ እና ላይስተር ሲቲ ሁለቱ በቀጣይ ጨዋታቸው ውጤት መሠረት ከፕሬሚየር ሊጉ መሰናበታቸው አይቀርም ።
በእንግሊዝ የሴቶች ሱፐር ሊግ የእግር ኳስ ፍጻሜ ፉክክር ግን ማንቸስተር ዩናይትድ የከተማው ተፎካካሪው ቡድን ማንቸስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፎ ዋንጫ ወስዷል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ዘንድሮ ዋንጫውን ማን ይወስዳል? መሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወይንስ ለበርካታ ጊዜያት ዋንጫዎችን የሰበሰበው ባየርን ሙይንሽን? የፊታችን ቅዳሜ ይለይለታል ። 70 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ማይንትስን ይገጥማል ። ዘንድሮ በቡንደስሊጋው የባየርን ሙይንሽን የመጨረሻ ተጋጣሚ ኮሎኝ ነው ። የቅዳሜ ውጤቶች 9ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙት ማይንትስም ሆነ ኮሎኝ ደረጃቸውን ከፍ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም ። ለቀጣይ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፤ ባየርን ሙይንሽን፤ ላይፕትሲሽ ማለፋቸው አረጋግጠዋል ። ተመሳሳይ 59 ነጥብ ያላቸው ዑኒዮን ቤርሊን እና ፍራይቡርግ 4ኛ ደረጃ የሻምፒዮስ ሊግ ቦታን ይዞ ለመጨረሽ የሞት ሽረት ግጥሚያ ያደርጋሉ ። ከሁለት አንዱ ነጥብ የጣለ ቡድን በቀጣይ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጀርመንን በአውሮጳ ሊግ የሚወክል ይሆናል ።
በስፔን ላሊጋ ትናንት በቫሌንሺያ የተሸነፈው ሪያል ማድሪድ ብራዚሊያዊ አጥቂ ቪንሺየስ ጁኒዬር የዘረኝነት ስድብ ሰለባ ሆኗል። 70ኛው ደቂቃ ላይ ስታዲየም ውስጥ ጥቁር በመሆኑ ከጥግ እስከ ጥግ ባስተጋባ መልኩ በደረሰበት የዘረንነት ስድብ አንገቱን እንደማያቀረቅር ተናግሯል ። ይልቁንስ፦ «በአንድ ወቅት የእነ ሮናልዲንሆ፤ ሮናልዶ፤ ክርስቲያኖ እና ሜሲ የነበረው የስፔን ላሊጋ ፉክክር ዛሬ የዘረኞች ሆኗል» ሲል ኢንስታግራም ገጹ ላይ በብርቱ ተችቷል ። ስፔን ተቀብላው በማስተናገዷ «ውብ ሀገር» ቢላትም ስፔናውያን እና ላሊጋ ግን ዘረኞች ናቸው በማለት ነቅፏል ። የ22 ዓመቱ ብራዚሊያዊ አጥቂ ከስድቡ ባሻገር ጨዋታው ወደ መገባደዱ ሲል በነበረው የተጨዋቾች አለመግባባትና ግርግር የቫለንሺያው ተጨዋች ሑጎ ዱሮ አንገቱን በክርኑ ስር አስገብቶ ሲጎትተው ይታያል ። ቪንሺየስ ጁኒየርም እጁን አመናጭቆ የሑጎን አንገት አይበሉባው ቸብ ያደርጋል ። ሑጎም መሬት ላይ ይንፈራፈራል ። ዳኛው በቴሌቪዥን በዝግታ ክስተቱን አይተው ቢጫ ካርዱን ወደ ቀይ ቀይረው ከሜዳ አሰናብተውታል ። የስፔን ላሊጋ በእርግጥም በተደጋጋሚ የዘረኝነት ችግሮች ሲንጸባረቁበት ይስተዋላል። ቪንሺየስ ጁኒየር ስለ ስፔን ሲናገር፦ «በሀሳቤ ለማይስማሙ ስፔናውያን ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ግን ዛሬ ስፔን ብራዚል ውስጥ የምትታወቀው እንደ ዘረኛ ሀገር ነው» ብሏል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ