የግንቦት 2 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 2 2013ዓለም በአጓጊነቱ የሚጠብቀው የቶኮዮ ኦሎምፒክ ውድድር በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዱላ ቀረሽ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። ውዝግቡ ተካሮ፦ «በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን በነጭ ባንዲራ አትሌቶችን ይዘን እንቀርባለን» የሚሉ ማስጠንቀቂያዎችም እየተሰሙ ነው። ሁለቱ የስፖርት ተቋማት በጋራ ተስማምተው ለመሥራት ያስችላቸው ዘንድ በነገው ዕለት ስብሰባ እንዲያደርጉ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት አሳስበዋል። ከነገው ስብሰባ ምን ይጠበቃል? ጉዳዮን በቅርበት የተከታተለ የስፖርት ጋዜጠኛ አነጋግረናል። በሳምንቱ መጨረሻ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ድንቅ ብቃቷን አስመዝግባ ለድል በቅታለች። የአውሮጳ ዋና ዋና የእግር ኳስ ውድድሮች ሊጠናቀቁ ጫፍ ደርሰዋል።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋው ሊጠናቀቅ ሁለት ዙር ግጥሚያዎች ይቀራሉ። ኃያሉ ባየርን ሙይንሽን ዋንጫውን ለ31ና ጊዜ መስወሰዱን ቀደም ሲል አረጋግጧል። ማሸነፉንም ቀጥሎበታል። በተለይ አጥቂው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል። በቀጣይ ሁለት ሳምንታት በወራጅ ቀጣናው ውስጥ እና ግርጌ የሚገኙ ቡድኖች የሞት ሽረት ግጥሚያዎች ለእግር ኳስ አፍቃሪያን እጅግ የሚያጓጉ ናቸው።
ከ18 የጀርመን ቡንደስሊጋ ቡድኖች በ13 ነጥብ የተወሰነው ሻልከ መሰናበቱን ካረጋገጠ ቆይቷል። ቀጣይ ሁለት ግጥሚያዎቹን እንኳን ቢያሸንፍ 17ኛ ደረጃ ላይ ያለው ኮሎኝ ላይ አይደርስበትም። ኮሎኝ እስካሁን በሰበሰበው 29 ነጥብ፤ ምንም እንኳን ከግርጌ አንድ ከፍ ብሎ ቢገኝም ከወራጅ ቀጣናው የመውጣት ዕድል ግን አለው። ወራጅ ቀጣናው ጠርዝ ላይ የየተንጠለጠለው አርሜኒያ ቢሌፌልድ ዘንድሮ በመጣበት እግሩ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላለመመለስ ቀጣይ ጨዋታዎቹ ላይ መሟሟት ይጠበቅበታል። ከበላዩ የሚገኙት ብሬመን እና ሔርታ ቤርሊንም እንደ ኮሎኝ 31 ነጥብ ሰብስበዋል። 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አውግስቡርግ ሳይቀር የመውረድ እጣ ሊገጥመው ይችላል። ምክንያቱም ነጥቡ 33 ነው። 31 ነጥብ ያለው ቢሌፌልድ ሁለቱን ጨዋታዎች ቢያሸንፍ እና አውግስቡርግ በሁለቱም ቢረታ ቦታቸውን ይቀያየራሉ። በአጠቃላይ ከታች ከ17ኛ እስከ 13ኛ ደረጃ ድረስ ያሉት ቡድኖች የመውረድ ስጋትም በቡንደስሊጋው የመቆየት ተስፋም አላቸው።
ፍራንክፉርት ለአውሮጳ ሊግ የዙር ውድድር ለማለፍ ዕእድል አለው። ባየርን ሙይንሽን፣ ኤርቤ ላይፕትሲሽ፣ ቮልፍስቡርግ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ተደርድረዋል። አሁን ያላቸውን ውጤት ማስጠበቅ ከቻሉ በሚቀጥለው ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ጀርመንን የሚወክሉ ቡድን ይሆናሉ። ተሰናባቹ ሻልከ ተስተካካይ ግጥሚያውን ዛሬ ማታ ከሔርታ ቤርሊን ጋር ያከናውናል። የዛሬው ውድድርም ሆነ ቀጣይ ውድድሮች ለሻልከ የሚያመጡት ለውጥ የለም። ለሔርታ ቤርሊን ግን እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ሔርታ የዛሬ ማታውን ግጥሚያ ካሸነፈ በ34 ነጥቡ ከአውግስቡርግ የ13ኛ ደረጃውን ይረከባል። አውግስቡርግ በበኩሉ ቦታውን ላለማስነጠቅ እና ከመውረድ ስጋት ለመራቅ ወሳን የሆነውን ግጥሚያውን ቅዳሜ ዕለት ከቬርደር ብሬመን ጋር ያከናውናል።
17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ቀጣይ ግጥሚያውን ቅዳሜ ዕለት የሚያከናውነው ከሔርታ ቤርሊን ጋር ነው። በተለይ የሁለቱ ጨዋታ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ አካል በመሆኑ እጅግ አጓጊ ነው። 16ኛ ደረጃ የያዘው አርሜኒያ ቢሌፌልድ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ላለመግባት ከሆፈንሃይም ጋር ቅዳሜ ይጋጠማል። 39 ነጥብ ላለው ሆፈንሃይም የቅዳሜውም ሆነ 34ኛው ዙር ግጥሚያ ውጤቱ የሚቀይረው አንዳችም ነገር የለም።
ከዚያ በተረፈ ከመከረኛው ሻልከ ጋር የሚጋጠመው አይንትራህት ፍራንክፉርት በቦሩስያ ዶርትሙንድ የተነጠቀውን የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ለማስመለስ ቅዳሜ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። አይንትራህት ፍራንክፉርትን በአንድ ነጥብ ብቻ በልጦ በ58 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ግጥሚያው ምንም የሚቀይርበት ነገር ከሌለው ማይንትስ ጋር ይጫወታል። 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማይንትስ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ቢሸነፍ እና ወራጅ ቀጣናው ጠርዝ ላይ የሚገኘው አርሜኒያ ቤሌፌልድ ሁለት ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ ሁለቱ ቡድኖች እኩል ነጥብ ይኖራቸዋል። የግብ እዳቸው ግን ከፍተኛ ልዩነት አለው። ማይንትስ 16፤ አርሜኒያ ቢሌፌልድ 28 የግብ እዳ አለባቸው። ያ ማለት ቢሌፌልድ የማይንትስን ቦታ ለመረከብ አሸንፎም ከእንግዲህ ከ12 ግብ በላይ ማስቆጠር ይጠበቅበታል ማለት ነው። ያ ደግሞ ከተጋጣሚዎቹ ብርታት አንጻር ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ሌላው የሳምንቱ መጨረሻ አጓጊ ግጥሚያዎች በ64 ነጥቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ላይፕትሲሽ እና በ60 ነጥቡ ሦስተኛነት በተቆናጠጠው ቮልፍስቡርግ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ነው። ዶርትሙንድም ከማይንትስ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ በሁለቱም በኩል እጅግ ወሳኝ ነው። ለዶርትሙንድ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ተሳታፊነቱን ለማስጠበቅ፤ ለማይንትስ ከመውረድ ስጋት ለመውጣት የሚያደርጉት ግብግብ።
በቡንደስሊጋው ድንቅ ብቃቱን ያስመሰከረው የባየርን ሙይንሽኑ አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የጌርድ ሙይለር በአንድ የጨዋታ ዘመን 40 ግቦችን የማስቆጠር ክብረወሰን ለመስበር ተቃርቧል። በሳምንቱ መጨረሻ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 6ለ0 ባንኮታኮቱበት ግጥሚያ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። አየር ላይ ተንሳፎ በመቀልበስ ያስቆጠራትን ውብ ግብ ጨምሮ እስካሁን 39 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በቀጣይ ሳምንት ከፍራይቡርግ ከዚያም በ34ኛ እና የመጨረሻ ዙር ግጥሚያ አውግስቡርግ ላይ ሁለት ግብ ብቻ ማግባት ይጠበቅበታል። ያኔም ፖላንዳዊው አጥቂ 49 ዓመታት የቆየውን ክብረወሰን ይሰብራል።
ፕሬሚየር ሊግ
የእንግሊዝም ፕሬሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። ፉልሃም፣ ዌስት ብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ በወራጅ ቀጣናው ከ18ኛ እስከ 20ኛ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል። የዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ባለድል ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በቀጣይ ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል። ቸልሲ፣ ላይስተር ሲቲ፣ ዌስትሀም፣ ሊቨርፑል፣ ቶትንሃም ሆትስፐር እና ኤቨርተን ከሦስተኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ስድስቱም ቡድኖች በቀጣይ ዙር ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት እድል አላቸው። በተለይ ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ሊቨርፑል እና ኤቨርተን እድል አላቸው። ሊቨርፑል ተስተካካይ ጨዋታውን ከዌስት ብሮሚች፣ ኤቨርተን ከቪላሪያል ጋር ያደርጋሉ። ሁለቱም ካሸነፉ ሊቨርፑል በ60 ነጥብ የአምስተኛ ደረጃውን ከዌስት ብሮሚች ተረክቦ በላይስተር በ3 ነጥብ ብቻ ይበለጣል። ኤቨርተን ነጥቡን 58 አድርሶ የሊቨርፑልን ቦታ ይረከባል። ሁለቱም ካሸነፉ ቀጣይ ቀሪ የፕሬሚየር ሊጉ ግጥሚያዎች ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግባቸው አጓጊ ጨዋታዎች ይሆናሉ።
ኢትዮጵያዊቷ ድንቅ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ፖርቹጋል ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው የ10,000 ሜትር ውድድር በታሪክ አምስተኛውን ፈጣን ሰአት አስመዝግባለች። ማያ ውስጥ በጎልድ ጋላ ፌርናንዳ ሪቤይሮ በተካኼደው ፉክክር 29 ደቂቃ ከ39,42 ሰከንድ በመግባት ነበር ፈጣኑን ሰአት ያስመዘገበችው። ቀደም ሲልም የዓለምን ክብረወሰን ሰብራ ለድል በቅታለች። ከሦስት ወራት በፊት ሊቪ ፈረንሳይ ውስጥ በተከናወነው የ1,500 ሜርትር የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ጉዳፍ 3:53.09 በመሮጥ በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ድንቅ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን መስበሯ ይታወሳል።
ከኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ ታደለ አሰፋ ጋር የተደረገው ቃለ መጠይቅ ዘገባው ውስጥ ይገኛል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ