የግንቦት 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 24 2012ለጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ በአደባባይ መገደል ተቃውሞው ከዩናይትድ ስቴትስም ተሻግሮ ወደ ቡንደስሊጋው አቅንቷል። ከሻልከ፣ እስከ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፤ ከባየር ሙይንሽን እስከ ዑኒየን ቤርሊን በቡንደስሊጋው የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዩናይትድ ስቴትስ ጸረ ዘረኝነት ተቃውሞን ተቀላልቅለዋል።
ከትዊተር ጽሑፍ አንስቶ ሜዳ ውስጥ እስከለበሱት የካናቴራ መልእክት በመታገዝም ተጨዋቾች ተቃውሞዋቸውን ሚሊዮኖች እንዲመለከቱ አስተጋብተዋል። በቡንደስሊጋው ባየር ሙይሽን እና ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በተመሳሳይ በግብ ተንበሽብሸዋል። በነጥብ ግን ባየር ሙይንሽን መሪነቱን አስጠብቋል። «ደህና ቆዪ ኢትዮጵያ» በሚል ከቤት ውስጥ ወይንም ካሉበት ቦታ በመኾን የሚከናወን የ5 ኪሜ የኢንተርኔት ላይ ሩጫ ዛሬ መጀመሩ ተዘግቧል።
የ46 ዓመቱ ጥቊር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ሰኞ እለት ነጩ ፖሊስ ዴሬክ ቻውቪን ጉሮሮው ላይ ለ11 ደቂቃ ያህል ተንበርክኮ ትንፋሽ በማሳጣት ሕይወቱ እንድታልፍ በማድረጉ የተቀጣጠለው ዓመጽ በተለያዩ ሃገራትም በስፖርቱም ከስፖርቱ ውጪም ተቃውሞን ወልዷል።
በአውሮጳ ከተሞች፦ ለንደን እና ቤርሊን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ለተቃውሞ ሰልፍ ወጥተዋል። ሰልፈኞቹ፦ «የጥቊር ሕይወት ይገዳል»፣ «ፍትኅ ለጆርጅ ፍሎይድ» እንዲሁም «ቀጣዩ ማን ነው?» የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል። የዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገን ውስጥም ለተቃውሞ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል።
የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኁ አጥቂ ማርኩስ ቱራም 2ኛውን ግብ ዑኒዮን ቤርሊን ላይ ሲያስቆጥር የጥቊር ሕይወት ትርጉም አለው በሚል የተጀመረውን የ(black lives matter) እንቅስቃሴ ደግፏል። የአሜሪካ ብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ (NFL) ዝነኛ ተጨዋች ኮሊን ኬይፐርኒከስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 በአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ወቅት በመንበርከክ የጀመረው የተቃውሞ ምልክትን ማርኩስ ቱራምም ተንበርክኮ ዐሳይቷል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ትናንት ዑኒዮን ቤርሊንን 4 ለ 1 አሸንፏል።
የዑኒየን ቤርሊኑ አንቶኒ ኡጃህም ትዊተር ላይ ተቃውሞውን ገልጧል። በትዊተር መልእክቱ ለኮሎኝ ይጫወት የነበረ ጊዜ ከ6 ዓመት በፊት በተነሳው ፎቶ ስታዲየም ውስጥ የለበሰውን መለያ ከፍ አድርጎ ካናቲራው ላይ ያለውን ጽሑፍ ያሳያል። ካናቲራው ላይ «መተንፈስ አልቻልኩም» እና «ፍትኅ» የሚሉ ጽሑፎች ይነበባሉ። ያኔ በወቅቱ ኒውዮርክ ውስጥ በፖሊሶች ታንቆ ስለሞተው የ6 ልጆች አባት ጥቁር አሜሪካዊ ኤሪክ ጋርነር ተቃውሞውን የገለጠበት ፎቶ ነው። እዚህ ፎቶ ላይ ጆርጅ ፍሎይድ የሚል ጽሑፍ በደማቁ ጽፎ በድጋሚ ትዊተር ላይ አስፍሯል። ኤሪክ ጋርነር እንደ ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ ትንፋሽ እንዲያጣ ተደርጎ ነበር የተገደለው።
የሻልከውም አማካይ ዌስተን ማክኬኒ ለጆርጅ ፍሎይድ መታሰቢያ ክርኑ ላይ «ፍትኅ ለጆርጅ» የሚል ጨርቅ አስሮ ሜዳ ውስጥ ገብቷል። ቅዳሜ ዕለት ሻልከ በብሬመን 1 ለ0 ተሸንፏል። የባየር ሙይንሽኑ ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግ በትዊተር ገጹ ላይ ተቃውሞን በጽሑፍ ገልጧል። በእንግሊዝኛ ያሰፈረው ጽሑፉ እንዲህ ይነበባል፦ «ስሙ ጆርጅ ፍሎይድ ይባል ነበር። ስሙን ጥሩት። ለቤተሰቡ ጸልዩ። ይኼ በድጋሚ መከሰቱን ማመን አልቻልኩም። ጭራሽ በጠራራ ጸሐይ፤ ለዚያውም እየተቀረጸ» ሲል ጽፏል። ከጽሑፉ ጋርም «የጥቁር ሕይወት ይገዳል» እና «ፍትኅ ለጆርጅ ፍሎይድ» የሚሉ መፈክሮችን አያይዟል።
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ፓዴርቦርንን 6 ለ 1 ድል ባደረገበት የትናንቱ ግጥሚያ ጄደን ሳንቾ ሔትትሪክ ሠርቷል። የመጀመሪያ ግቡን እንዳስቆጠረ መለያውን አውልቆ ለጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ፍትኅ የጠየቀበትን ጽሑፍ በካናቲራው ላይ ዐሳይቷል። አሽራፍ ሐኪሚም በተመሳሳይ ጸረ ዘረኝነት ንቅናቄውን ደግፏል።
አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬ ባለፈው ሳምንት ካሰለፏቸው ተጨዋቾች ኹለቱን ብቻ ቀይረው ነው ወደ ሜዳ የገቡት። ማሃሙድ ዳውድ በጉልበት ጉዳት በዚህ የጨዋታ ዘመን አይሰለፍም። ኧርሊንግ ሃላንድም በተመሳሳይ የጉልበት ጉዳት ትናንት አልተሰለፈም። የእሱን ቦታ አማካዩ ቶርጋን ሐዛርድ ሸፍኖ ውሏል። 54ኛው ደቂቃ ላይም የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሯል። 57ኛው፣ 74ኛው እና 91ኛው ደቂቃ ላይ ጄደን ሳንቾ ሲያስቆጥር፣ የቀሩትን ግቦች ከመረብ ያሳረፉት አሽራፍ ሐኪሚ በ85ኛው እንዲሁም ማርሴል ሽሜልትሰር 89ኛው ደቂቃ ላይ ናቸው። በተለይ ለተከላካዩ ማርሴል በዚህ የጨዋታ ዘመን ብቸኛዋ ግቡ ናት።
ማሪዮ ጎይትሰ ትናንትም ተቀያሪ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ ወደ ሜዳ ሳይገባ ቀርቷል። ባለፈው ሳምንት በባየር ሙይንሽን በተሸነፉበት ግጥሚያ ብቻ ለ10 ደቂቃ ተቀይሮ ገብቷል።
በአንጻሩ ትናንት ሙሉ ጨዋታ የተሰለፈው ጄደን ሳንቾ ባለፈው ሳምንት ዩሊያን ብራንድትን ቀይሮ የገባው 46ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ትናንት ግን ከዩሊያን ጋር ግራና ቀኝ የፊት አማካይ ቦታ ላይ ተሰልፏል።
ባለፈው ሳምንት በዚሁ ተመሳሳይ ጨዋታ 72ኛው ደቂቃ ላይ ኧርሊንግ ሃላንድን ተክቶ የተሰለፈው አማካዩ ጂዮቫኒ ሬይና ትናንት 80ኛው ደቂቃ ላይ ዩሊያን ብራንድትን ቀይሮ ገብቷል።
አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬ በያዙት የ3፣4፣3 አሰላለፍ ቀጥለው ስኬታማነታቸውን ዐሳይተዋል። ምናልባት ይኽን የአሰላለፍ ስልታቸውን በአንዲት ብቸኛ ግብም ቢኾን መስበር የቻለው የተከላካይ ክፍሉን በአራት ተጨዋቾች እያጠረ የሚሰለፈው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ነው።
ዐርብ ዕለት ባየር ሌቨርኩሰን ፍራይቡርግን 1 ለ 0 አሸንፎ በደረጃ ሰንጠረዡ ለጊዜውም ቢኾን ወደ 4ኛ ከፍ ብሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ዛሬ ማታ ከኮሎኝ ጋር ይጋጠማሉ። ካሸነፈ የሦስተኛ ደረጃውን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በኹለት ነጥብ በልጦ ይረከባል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ እና ባየር ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ 56 ነጥብ በግብ ክፍያ ተለያይተው ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃውን ይዘዋል።
ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ባየር ሙይንሽን ዱይስልዶርፍን 5 ለ0 አደባይቷል። ፍራንክፉርት ቮልፍስቡርግን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ሔርታ ቤርሊን አውግስቡርግን 2 ለ 0 ድል አድርጓል። ሆፈንሃይም ማይንትስን እንዲሁም ብሬመን ሻልከን በተመሳሳይ 1 ለ0 አሸንፈዋል።
ትናንት በተከናወኑ ኹለት ግጥሚያዎች ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ዑኒየን ቤርሊንን 4 ለ1 አሸንፏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወራጅ ቃጣና ግርጌ ላይ የተዘረጋው ፓዴርቦርንን 6 ለ1 አንኮታኩቷል። 60 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከመሪው ባየር ሙይንሽን በ7 ነጥብ ይበለጣል። ብሬመን ከፍራንክፉርት ጋር ረቡዕ ዕለት ተስተካካይ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። 25 ነጥብ ይዞ 17ኛ ደረጃ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ለሚገኘው ብሬመን የረቡዕ ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ዱይስልዶርፍ እና ማይንትስ 16ኛ እና 15ኛ ደረጃው ላይ የሚገኙት በ27 እና 28 ነጥብ ብቻ ነው።
የባየር ሙይንሽን ኃያልነት
ባየር ሙይንሽን በኮሮና ምክንያት ከተቋረጠ እና ዳግም ከጀመረ በኋላ ያሉትን አራቱንም የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች በድል አጠናቋል። በአንዱ ግጥሚያ ብቻ ግብ ተቆጥሮበታል። ከሦስት ሳምንት በፊት ዑኒዮን ቤርሊንን 2 ለ0፤ በሳምንቱ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 5 ለ2 አሸንፏል። ማክሰኞ ዕለት በወሳኝ የቡንደስሊጋው ግጥሚያ ቦሩስያ ዶርትሙንድን 1 ለ0 ሲረታ፤ ቅዳሜ ዕለት ዱይስልዶርፍን 5 ለ0 አሰናብቷል። በአጠቃላይ 2 ግብ ሲቆጠርበት 13 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።
ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት 5 ለ0 በግብ በተንበሸበሸበት ግጥሚያ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ43ኛው እና 50ኛው ደቂቃዎች ላይ ኹለት ግቦችን አስቆጥሯል። ሌቫንዶቭስኪ ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ግብ ሲያስቆጥር። በቅዳሜው ግብም ፖላንዳዊው አጥቂ፦ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በዘመኑ በቡንደስሊጋው ቡድኖች በአጠቃላይ ቢያንስ አንድ ግብ ማስቆጠር ተሳክቶለታል። እስካሁን 29 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በቡንደስሊጋው ግብ አዳኝነት ቀዳሚ ነው። የላይፕትሲሹ ቲሞ ቬርነር በ24 ግቦች ይከተለዋል። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ጄደን ሳንቾ በ17 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በቡንደስሊጋው ሦስተኛ ግብ አዳኝ ኾኗል።
ለባየር ሙይንሽን የመጀመሪያዋን ግብ 15ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ላይ ያስቆጠረው ማቲያስ ዮይርገንሰን ነው። ከመነሻው ጫና የፈጠረው ባየር ሙይንሽን በኪሚሽ በኩል ያሻገረውን ኳስ ቶማስ ሙይለር በድንቅ ኩኔታ ያሻገረው ለግናብሬ ነበር። ግናብሬ ለፓቫርድ ያሳለፈውን ኳስ ፓቫርድ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ማቲያስ በእግሩና በደረቱ ኳሱ ተጋጭቶ የገዛ መረቡ ላይ አርፏል። ኹለተኛውን ግብ ቤንጃሚን ፓቫርድ በ29ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። በ43ኛው እና 50ኛው ደቂቃ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ እንዲሁም 52ኛው ደቂቃ ላይ አልፎንሶ ዳቪስ ከመረብ አሳርፈዋል።
ከረዥም ጊዜ የጉልበት ጉዳት እና በኮሮና ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው የቀድሞው አትሌቲኮ ማድሪድ ተከላካይ ሉቃስ ሄርናንዴዝ ቅዳሜ ዕለት ከ11ዱ ቀዳሚ ተሰላፊዎች ተርታ ቢኖርም ከ45 ደቂቃ በኋላ ግን ተቀይሯል። አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ በ80 ሚሊዮን ዩሮ የተገዛውን ተከላካይ ለምን እደቀየሩት ተጠይቀው፦ «ከጉዳት ጋር በተያያዘ መቀየር ነበረብኝ» ብለዋል። «በቀላሉ ለአደጋ ተጋላጭነቱም ከፍተኛ ነበር» ሲሉም አክለዋል።
አትሌቲክስ
«ደህና ቆዪ ኢትዮጵያ» በሚል የ5ኪሜ በኢንተርኔት የታገዘ የሩጫ ውድድር ዛሬ ግንቦት 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም መጀመሩን የታላቊ ሩጫ በኢትዮጵያ በኢሜል የላከልን መልእክት ይጠቅሳል። የሩጫ ውድድሩ ለ7 ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ የተገለጠ ሲሆን የሚጠናቀቀውም እሁድ ግንቦት 30 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ነው ተብሏል። በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በሚጫን ስትራቫ (Strava) በተሰኘ የሩጫ ማስተናበሪያ በመታገዝ በሚደረገው ውድድር 500 ሰዎች ተሳታፊ እንደሚኾኑ ተጠቅሷል። በዛሬው የውድድሩ የመጀመሪያ ቀን 39 ተሳታፊዎች ሩጫውን ለማድረግ ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውንም የኢሜል መልእክቱ አክሎ ጠቅሷል።
በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ዳግም ሊጀምር ነው። ከበርካታ ወራት መቋረጥ በኋላ ሽቅድምድሙ ይጀምራል የተባለው የሐምሌ ወር ውስጥ ነው። ኦስትሪያ ውድድሩን ያለ ታዳሚ ታስጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል። ውድድሩ ሽፒልበርግ ውስጥ ሰኔ 28 ይጀምራል ተብሏል። ከዚያም በሳምንቱ ደግሞ የሬድ ቡል መወዳደሪያ ስፍራ ላይ ተጨማሪ ሽቅድምድም ሊኖር ይችላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ