1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 29 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 29 2014

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በ22ኛው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ሞሪሺየስ ገብቷል። ፖላንድ እና ሄንጌሎው ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በጦርነት የፈራረሰችው ዩክሬን እግር ኳስ ተጨዋቾች ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የነበራቸው ተስፋ በስተመጨረሻ ተጨናግፏል።

Frankreich | French Open: Rafael Nadal gewinnt gegen Casper Ruud
ምስል YVES HERMAN/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በ22ኛው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ሞሪሺየስ ገብቷል። ፖላንድ እና ሄንጌሎው ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በጦርነት የፈራረሰችው ዩክሬን እግር ኳስ ተጨዋቾች ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የነበራቸው ተስፋ በስተመጨረሻ ተጨናግፏል። በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ሁለተኛ ዙር የምድብ ግጥሚያዎች ቀጥለዋል። ለዛሬ ቀጠሮ ከተያዘላቸው ስድስት ግጥሚያዎች እስራኤል ከሩስያ ጋር ታደርግ የነበረው ተሰርዟል። ውድድሮቹ ነገ እና ከነገ በስትያም ይቀጥላሉ። በሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ውድድር የ36 ዓመቱ ስፔናዊ ተጨዋች ራፋኤል ናዳል አሸናፊ ኾኗል።  ዐርባዎቹን የተጠጋው ስፔናዊ የሜዳ ቴኒስ ዕውቅ ወደፊት በቀጣይ ውድድሮች ይሳተፍ አለያም የቴኒስ መሠረቢያውን ይስቀል የሚታወቅ ነገር የለም።

አትሌቲክስ

በ22ኛው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ሞሪሸስ መግባቱ ታውቋል። ሞሪሺየስ ውስጥ የሚከናወነው ውድድር ረቡዕ ሰኔ 1 ቀን፣ ጀምሮ እሁድ ሰኔ 5 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።  ኢትዮጵያን ጨምሮም የአፍሪቃ ምርጥ አትሌቶች በኮት ዲዖር ብሔራዊ የመወዳደሪያ ማእከል ላይ ይፋለማሉ። ውድድሮቹም፦ የከፍታ ዝላይ፤ የርዝመት ዝላይ፤ የመሰናከል ሩጫ፤ የ3000 ሜትር የመሰናከል ሩጫ፤ የ100 ሜትር፣ የ400 ሜትር፤ የ800 ሜትር የ1500 ሜትር፤ የ5,000 ሜትር እንዲሁም የ10,000 ሜትር ሩጫ ውድድሮች ይኖራሉ። 4 በ400 የዱላ ቅብብል እና የአሎሎ ውርወራም ከውድድሮቹ መካከል ይገኙበታል።

ምስል picture-alliance/sampics/S. Matzke

ሞሪሺየስ ከዚህ ቀደም ሁለት የአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድሮችን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1992 እና 2006 አዘጋጅታ ነበር። ከ54ቱ የአፍሪቃ ሃገራት 42ቱ በውድድሩ እንደሚካፈሉ ከወዲሁ ዐሳውቀዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የልዑካን ቡድን እሁድ ግንቦት 28 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ በተካሄደ መርኃ ግብር በአራራት ሆቴል ሽንት ተደርጎለታል።

ኔዘርላንድስ ሄንግሎ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የ10,000 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቲች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከታትለው በመግባት ደማቅ ድል አስመዘገቡ። የኦሎምፒክ ባለድሉ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በውድድሩ 26.44.72 በመሮጥ አንደኛ ደረጃን ይዞ አሸንፏል። በውድድሩ ድል ያስመዘገቡት አራቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የገቡበት ሰአት ከ26,50 በታች መሆኑም በልዩ ኹኔታ ታሪካዊ ክስተት ተብሎ ተመዝግቧል። እንደ ሰለሞን ሁሉ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ምርጥ ሰአት አስመዝግበዋል። ታደሰ ወርቁ የራሱን ምርጥ ሰአት ባስመዘገበበት 26.45.91 በመሮጥ 2ኛ ወጥቷል። ብርሃኑ አረጋዊ 26.46.13 በመሮጥ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ዮሚፍ ቀጀልቻ 26.49.39 በመሮጥ የ4ኛ ደረጃን ሲይዝ ሁሉም የገቡበት ሰአት ፈጣን ተብሏል።

ትናንት ማታ ፖላንድ ውስጥ በተከናወነ ሌላ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ የራሷን ምርጥ ሰአት ባስመዘገበችበት ፍጥነት 1ኛ በመውጣት አሸንፋለች። በኦሎምፒክ አራተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው የብሪታንያ እና ሰሜን አይርላንዷ ጄማ ሪኪ በመጨረሻዎቹ ዙሮች አፈትልካ ለመውጣት ብትጥርም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ግን ድሉን ሳታስቀማ በ1ኛነት አጠናቃለች። ያሸነፈችውም 1:58.28 በመሮጥ ነው። ድርቤ ወልተጂን ከ16 ሰከንድ በኋላ ተከትላ የገባችው ጄማ ሪኪ የሁለተኛ ደረጃ ስትይዝ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ሰአቷ ተብሎላታል። የሦስተኛውን ደረጃ ደግሞ ፖላንዳዊቷ ሶፊያ እናዎዪ 1:58.98 በመሮጥ ይዛለች።

ምስል REBECCA NADEN/REUTERS

እግር ኳስ

የዓለም ዋንጫ የመጨረሺያ የማጣሪያ ግጥሚያ

በጦርነት የተዳቀቀችው ዩክሬን እግር ኳስ ተጨዋቾች ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀረ። በዌልሱ የካርዲፍ ስታዲየም ውስጥ ትናንት በተከናወነው ግጥሚያ የዌልስ ቡድን በኳስ ይዞታ ጉልኅ ብልጫ ዐሳይቷል። 34ኛው ደቂቃ ላይም የዌልሱ አምበል ጋሬት ቤል ያገኛት የቅጣት ምት ዌልስን ለድል ዩክሬንን ለሽንፈት ዳርጋለች። የቅጣት ምቱን ለማጨናገፍ የጣረው ዌስት ሀም ዩናይትድ ውስጥ የሚጫወተው የዩክሬኑ አማካኝ አንድሬ ያርሞሌንኮ አሳዛኝ ድርጊት ፈጽሟል። አንድሬ የገዛ ግቡ ላይ በጭንቅላት ገጭቶ በማስቆጠሩ ጨዋታው በዌልስ አሸናፊነት 1 ለ0 ተጠናቋል። 74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የዌልሱ ብሬናን ጆንሰን የመታት ኳስ ማእዘኑን በመግጨት ለጥቂት ግብ ከመኾን ተርፋለች። ከዚያ በኋላ 10 ደቂቃ ቆይቶ ደግሞ ቪታሊ ሚኮሌንኮ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የዌልሱ ግብ ጠባቂ አጨናግፏል። በዚህም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2006 ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ጫፍ ደርሶ የነበረው የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ዕድል ተጨናግፏል።

ምስል Mike Egerton/empics/picture alliance

የዌልስ ቡድን ካታር ውስጥ ከኅዳር 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም እስከ ታኅሣስ 9 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ተሰላፊ መሆናቸውን ካረጋገጡ የአውሮጳ ሃገራት መካከል የመጨረሻው ቡድን ኾኗል። ዩክሬን ውስጥ ባለው ጦርነት የተነሳ የሁለቱ ቡድኖች ውድድር መጀመሪያ ላይ ወደ መጋቢት ከዚያም ሰኔ ወር ተዛውሮ ነበር። የዩክሬን ቡድን በግማሽ ፍጻሜው ስኮትላንድን በሜዳው ግላስኮው ውስጥ አስደማሚ በኾነ መልኩ 3 ለ1 አሸንፎ ነበር ለፍጻሜ የደረሰው። ለዌልስ ግን እጅ ሰጥቷል። ያም በመኾኑ አሸናፊው የዌልስ ቡድን ከ1958 ወዲህ ታሪካዊ በሆነ መልኩ ለሁለተኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል። በካታር ምድር የዓለም ዋንጫ የመክፈቻው ስርዓት እስኪጀምርም 167 ቀናትን ይጠብቃል።

የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ

የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ዙር ቀጥሏል። ፖርቹጋል ሊዛቦን ከተማ ኤስታዲዮ ኾዜ አልቫላዴ ውስጥ ትናንት ስዊትዘርላንድን 4 ለ 0 ድባቅ በመታችበት የኔሽንስ ሊግ ግጥሚያ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 2 ግቦችን አስቆጥሯል። ስፔን በቼክ ሪፐብሊክ 2 ለ1 ከመሸነፍ የዳነችው ባለቀ ሰአት በኢንጎ ማርቲኔዝ በተገኘ ግብ ነው። ጀርመን ቦሩስያ ዶርትሙንድ ውስጥ የሚጫወተው የኖርዌዩ አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ ደግሞ ስዊድንን ባሸነፉበት የ2 ለ1 ግጥሚያ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ አሳርፏል። ኖርዌይ ከምድቧ በ6 ነጥብ አንደኛ ናት። ከምድቡ መጨረሺያ ላይ የምትገኘው ስሎቬንያ ሐሙስ ማታ ኖርዌይን ታስተናግዳለች። በምድቡ 2ኛ ደረጃ የያዘው እና ስሎቬኒያን 4 ለ1 ያሸነፈው ሠርቢያ ወደ ስዊድን ያቀናል። ስዊድን በምድቡ 3 ነጥብ ይዛ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ምስል Alberto Lingria/REUTERS

ትናንት በተከናወኑ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ጆርጂያ ቡልጋሪያን 5 ለ2 ድል ሲያደርግ፤ ሰሜን መቄዶንያ ጂብራልታርን 2 ለ0 አሸንፏል። ማልታ ሳን ማሪኖን 2 ለ0 ባሸነፈበት ምሽት፤ ሰሜን አየርላንድ እና ሲፕረስ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት ጀርመን እና ጣሊያን ተጋጥመው አንድ እኩል ተለያይተዋል። እንግሊዝ በሐንጋሪ የ1 ለ0 ሽንፈት ደርሶባታል። ዐርብ ዕለት ደግሞ ዴንማርክ ፈረንሳይን 2 ለ1 ስታሸንፍ፤ ቤልጂየም በኔዘርላንድ የ4 ለ1 ብርቱ ሽንፈት ገጥሟታል።

ለዛሬ ቀጠሮ ከተያዘላቸው ግጥሚያዎች መካከል የሩስያ እና እስራኤል ከመሰረዙ በስተቀር ቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ምሽቱን ይከናወናሉ። እነሱም፦ ቤላሩስ ከአዘርባጃን፣ ፈረንሳይ ከክሮሺያ፣ ካዛክስታን ከስሎቫኪያ፣ ኦስትሪያ ከዴንማርክ፣ አንዶራ ከሞልዶቫ፣ እንዲሁም አልባንያ ከአይስላንድ ናቸው። የጀርመን ከእንግሊዝ እንዲሁም ጣሊያን ከሐንጋሪን ጨምሮ ነገ ስድስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ጨዋታዎቹ ሳምንቱን ሙሉ ይቀጥላሉ።  

ምስል Sportphoto24/EPhotopress/picture alliance

በሌላ የእግር ኳስ ግጥሚያ፦ ሊዮኔል ሜሲ ባለፈው ረቡዕ ኤስቶኒያ ላይ አምስት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ በአንድ ጨዋታ ብዙ ግቦችን በማስቆጠር አራተኛ ደረጃን አግኝቷል።  ስፔን ውስጥ በተደረገው የወዳጅነት ግጥሚያ በሊዮኔል ሜሲ ግቦች የንበሸበሸችው አርጀንቲና ኤስቶኒያን በማንኮታኮት የአውሮፓ ጉዞዋን አጠናቃለች።

የሜዳ ቴኒስ

ስር በሰደደ የእግር ኅመም የሚሰቃየው ራፋኤል ናዳል 14ኛውን የፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ አሸነፈ። የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ራፋኤል ምንም እንኳን ዘንድሮ መቶ በመቶ ብቃቱ ላይ ባይገኝም ለድል በቅቷል። ፓሪስ ከተማ ውስጥ በኮር ፊሊፕ ሻርቲዬ በተከናወነው የፍጻሜ ውድድር ራፋኤል ናዳል ያሸነፈው የኖርዌዩ ተጨዋች ካስፐር ሩዉድን ነው። ራፋኤል በትናንቱ ፍጻሜ የደረሰው፦ ታዋቂዎቹን ኖቫክ ጄኮቪችን እና አሌክዛንደር ዝቬሬቭን በማሸነፍ ነው። ራፋኤል ናዳል ለ14ኛ ጊዜ የፈረንሳይ የፍጻሜ ውድድርን ትናንት ያሸነፈው ሁለት ጊዜ 6-3 እና  6-0 በሆነ ውጤት ነው።  36ኛ ዓመቱን በሞላ በ2ኛ ቀኑ የፍጻሜ ውድድሩን ትናንት ያሸነፈው ራፋኤል ናዳል በፈረንሳይ የፍጻሜ ውድድር ታሪክ በዕድሜ ትልቁ አሸናፊ ኾኗል። የመጀመሪያ ድሉንም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2005 ያሸነፈው በ19 ዓመቱ ነበር። እሁድ በነበረው የፍጻሜ ውድድር በራፋኤል ናዳል የተሸነፈው የ23 ዓመቱ ወጣት ስፔናዊውን የዓለማችን ምርጥ ተጨዋች እንደ ምሳሌ ዕያየ ያደገ ነው። የእሁዱ ድል ለራፋኤል ናዳል በፍጻሜ ውድድሮች 22ኛው ኾኖ ተመዝግቦለታል።  ራፋኤል ናዳል ከ36ኛ ዓመቱ በኋላ የቴኒስ መጫወቺያውን ይስቀል ወይንስ በቀጣይ ውድድሮች ተሳታፊ ይሁን የሚታወቅ ነገር የለም። በተደጋጋሚ ማሸነፍ እጅግ ያስደስተኛል ያለው ራፋኤል ምናልባትም ከ21 ቀናት በኋላ በሚከናወነው የዌምብልደን ውድድር ተካፋይ ሊኾንም ይችላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW