1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግንቦት 4 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017

ሪያል ማድሪድ ትናንት ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ በባርሴሎና ሽንፈት ገጥሞታል ። በኮፓ ደ ሬይ ዋንጫ የወሰደው ባርሴሎና ለላሊጋው ዋንጫም እየገሰገሰ ነው ። የባዬርን ሙይንሽን የረዥም ዘመን ተጨዋች ቶማስ ሙይለር ከቡድኑ ስንብት ተደርጎለታል ። አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ከባዬር ሌቨርኩሰን መለየቱን ይፋ አድርጓል፤ ሪያል ማድሪድ ይጠብቀዋል ።

በኮፓ ደ ሬይ ዋንጫ የወሰደው ባርሴሎና ለላሊጋው ዋንጫም እየገሰገሰ ነው
በዘንድሮ የኮፓ ደ ሬይ የፍጻሜ ግጥሚያ ሪያል ማድሪድን አሸንፎ ዋንጫ የወሰደው ባርሴሎና ለላሊጋው ዋንጫም እየገሰገሰ ነው ምስል፦ Borja Suarez/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ሪያል ማድሪድ ትናንት ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ በባርሴሎና ሽንፈት ገጥሞታል ። ባርሴሎና ዋንጫ የማንሳት እድሉን እጅግ ከፍ አድርጓል ። የባዬርን ሙይንሽን የረዥም ዘመን ተጨዋች ቶማስ ሙይለር ከቡድኑ ስንብት ተደርጎለታል ።  አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ከባዬር ሌቨርኩሰን መለየቱን ይፋ አድርጓል፤ ሪያል ማድሪድ ይጠብቀዋል ። 

54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቅቋል

ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲከናወን የቆየው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቅቋል ። በወንድ እና ሴት የፍጻሜ ውድድር ከተካሄደባቸው መካከል፦ የ5000፤ የ1500 እንዲሁም የ100 ሜትር በአራት የዱላ ቅብብል ይገኝበታል ።

በአጠቃላይ ውድድሩ 1,379 አትሌቶች፣ 31 ቡድኖች እና ተቋማት እንዲሁም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሳተፋቸው ተገልጧል ። ለአንድ ሳምንት ግድም በተከናወነው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በድምር ውጤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 279 ነጥብ በማምጣት በአንደኛነት አሸንፏል ። መቻል 242 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ ሸገር ሲቲ በ143 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።

በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድበ ባርሴሎና ዳግም ጉድ ሆነ

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ትናንት ሪያል ማድሪድን 4 ለ3 በመርታት የደረጃ መሪነቱን ይበልጥ አጠናክሯል ። በትናንቱ ግጥሚያ ቀዳሚውን ግብ በተገኘ ፍጹም ቅጣት ምት 5ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ኪሊያን እምባፔ ነበር ።  ከጥቂት ቆይታ በኋላ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ይኸው ግብ አዳኝ ኪሊያን እምባፔ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር ባርሴሎናን በገዛ ሜዳው እና በደጋፊው ፊት አስደንግጦ ነበር ። ሁለተኛው ግብ እንድትቆጠር ቪንሰንት ጁኒዬር በድንቅ ሁኔታ ከተከላካዮች እግር ፊት አስቀድሞ ኳሷን ለኬሊያን እምባፔ በመላክ ብቃቱን ዐሳይቷል ።

ኬሊያን እምባፔ እንደለመደው ሦስት ግቦችን ለሪያል ማድሪድ በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷልምስል፦ Manu Fernandez/AP Photo/picture alliance

በ19ኛው ደቂቃ ባርሴሎና ያገኘውን የማእዘን ምት ኤሪክ ጋርሺያ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል ። በገዛ ሜዳቸው ግራ ተጋብተው የነበሩት የባርሴሎና ደጋፊዎችን እፎይ ያስባለች እና ያነቃቃች ግብ ። ከተከላካዮች ዕይታ ውጪ ከግቡ በስተግራ ቆሞ አጋጣሚውን ሲጠብቅ የነበረው ላሚን ያማል 32ኛው ደቂቃ ላይ ባርሴሎናን አቻ ያደረገውን ግብ ተረጋግቶ አስቆጥሯል ። ሰባት የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተደርድረው ሌሎች ተጨዋቾች ላይ ትኩረት ባደረጉበት ቅጽበት ለብቻው ነጠል ብሎ የነበረው ላሚን ጉድ አድርጓቸዋል ። የሚያዝያ 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ጨዋታው ተጋግሎ 34ኛ ደቂቃ ላይ ራፊና ዲያስ 3ኛውን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ባርሴሎናን ቀደሚ አድርጓል ። ይኸው ራፊና 41ኛው ደቂቃ ላይም የተሻማ ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ በማለፍ ግብ ሳይሆን ቀርቷል ።  በፈጣን እንቅስቃሴው የሪያል ማድሪድ ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ የቆየው ራፊና 45ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተሳክቶለት ለራሱ ሁለተኛ ለባርሴሎና የማሸነፊያዋን አራተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል ።

የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ፍጥጫ አሁንም ቀጥሏል

መደበኛው 45 ደቂቃ ተጠናቅቆ በጭማሪው 8ኛ ደቂቃ ላይ እምባፔ ለሪያል ማድሪድ ቢያስቆጥርም ግቡ ከጨዋታ ውጪ ተብሏል ። ወዲያውም ባርሴሎና 4 ለ2 እየመራ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቅቆ ረፍት አድርገዋል ። ከረፍት መልስ 52ኛው ደቂቃ ላይ ላሚን ያማል ሪያል ማድሪድን ያስደነገጠ ግብ ቢያስቆጥርም ለጥቂት ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮበታል ።  70ኛ ደቂቃ ላይ ቪንሰንት ጁኒዬር በድንቅ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ኪሊያን እምባፔ 3ኛ ግብ ለሪያል ማድሪድ በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል ።  ኪሊያን እምባፔ በ27 ከመረብ ያረፉ ኳሶች የላሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ ነው ። የባርሴሎናው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ25 ግብ ይከተለዋል ። 

በኮፓ ደ ሬይ ዋንጫውን ያነሳው ባርሴሎና በላሊጋውም ሪያል ማድሪድን 4 ለ3 በማሸነፍ ለዋንጫ ግስጋሴውን ቀጥሏልምስል፦ Borja Suarez/REUTERS

ባርሴሎና በትናንቱ ግጥሚያ 94ኛ ደቂቃ ላይ በሎፔዝ አምስተኛ ግብ ቢያስቆጥርም ኳሷን ቀደም ብሎ በእጁ በመንካቱ ግቡ ተሽሯል ። ብርቱ ፍልሚያ የታየበት የሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ፦ በ97ኛው ደቂቃ ላይ በባርሴሎና የ4 ለ3 ድል ተጠናቅቋል ። ከ2 ለ0 ተነስቶ በማሸነፍ 82 ነጥብ የሰበሰበው ባርሴሎና እና ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዲተር ሐንስ ፍሊክ ፈንጥዘዋል ። በ75 ነጥቡ የተወሰነው ሪያል ማድሪድ እና አሰልጣኙ ካርሎ አንቼሎቲም አንገታቸውን ደፍተዋል ።  20 ቡድኖች ያሉት የስፔን ላሊጋ ሊጠናቀቅ ሦስት ዙር ጨዋታዎች ይቀሩታል ። የሚያዝያ 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የፊታችን ሐሙስ ማታ ቀጣይ 36ኛ ጨዋታውን ከኢስፓኞል ጋር የሚያደርገው ባርሴሎና ካሸነፈ ዋንጫውን መውሰዱን ያረጋግጣል ። በላሊጋው 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢስፓኞል ጨዋታውን ቢያሸንፍ በቀጣይ የአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግ ማጣሪያ ተሳታፊ ለመሆን ጭላንጭል ዕድል ይኖረዋል ። ሆኖም በማጣሪያው ተሳታፊ ለመሆን ባርሴሎናን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። የሐሙሱ ጨዋታ ለኤስፓኞል ብርቱ ፈተና ሲሆን ለባርሴሎና ዋንጫውን መውሰዱን የሚያረጋግጥበት ወሳኝ ግጥሚያ ። 

አርሰናል ከኋላ ተነስቶ በሊቨርፑል ከመሸነፍ ተርፏል

አርሰናል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ አስቀድሞ መውሰዱን ያረጋገጠው ሊቨርፑልን አንፊልድ ውስጥ ትናንት ገጥሞ ከ2 ለ0 በመነሳት አቻ ተለያይቷል ። 83  ነጥብ ላለው ሊቨርፑል የትናንቱ ግጥሚያ ምንም የሚፈይደው ነገር ባይኖርም 68 ነጥብ ላለው አርሰናል ግን ወሳኝ ነበር ። በሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ባፓሪ ሳንጃርሞ የተሰናበተው አርሰናል የትናንቱን የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ አሸንፎ ቢሆን ኑሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን መቶ በመቶ ያረጋግጥ ነበር ። በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሰባተኛ ላይ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት እንኳን በ62 ነጥቡ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድል አለውና ። 

የአርሰናሉ ቡካዮ ሳካ በሻምፒዮንስ ሊግ ከፒኤስጂ ጋር ተጫውተው በተሸነፉበት ወሳኝ ግጥሚያ ወቅትምስል፦ Neal Simpson/Imago Images

ለአውሮጳ ሊግ የምድብ ጨዋታ የማለፍ ዕድል ይዞ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላ ነጥቡ 63 ነው ። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 69 ያደርሳል ። ያም በመሆኑ 68 ነጥብ ያለው አርሰናል የሻምፒዮስ ሊግ ተሳታፊነቱን የሌሎች ቡድኖችን ውጤት ሳይጠብቅ ለማረጋገጥ ከቀጣይ ጨዋታዎቹ ቢያንስ አንዱን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። በርካታ የግብ ክፍያ ስላለውም አንድ ጨዋታ አቻ ቢወጣም ያዋጣዋል ።

ኢፒስዊች ታወን፣ ላይስተር ሲቲ እና ሳወዝሀምፕተን ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ወራጆች ናቸው ። በእነሱ ምትክ ባለፈው ሳምንት የሁለተኛ ዲቪዚዮን ዋንጫውን የወሰደው ሊድስ ዩናይትድ ወደ ዋናው ፕሬሚየር ሊግ ማለፉን አረጋግጧል ። ሌላኛው ማለፉን ያረጋገጠ ቡድን በርንሌይ ሲሆን፦ ለቀሪ ሦስተኛ ቦታ ደግሞ ሼፊልድ ዩናይትድ፣ ሰንደርላንድ፣ ኮንቬንትሪ እና ብሪስቶል ሲቲ ይጋጠማሉ ።

ሐምቡርግ ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ አለፈ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረዳቸው የተረጋገጠ ቡድኖች ናቸው ። በእነሱ ምትክ ሐምቡርግ ወደ ዋናው ቡንደስሊጋ ማለፉን አረጋግጧል ። አንድ ጨዋታ እየቀረ ሁለተኛ ሆኖ የሚጨርስ ቡድን ማንነት ገና ዐልታወቀም ። በዋናው ቡንደስሊጋ 29 ነጥብ ሰብስቦ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሐይደንሀይም ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ቡድን ጋር በደርሶ መልስ ይጋጠማል ። ከሁለቱ የአሸነፈ ቡድን የቀጣይ ቡንደስሊጋ ተሳታፊ ቦታ መያዙን ያረጋግጣል ። የመጋቢት 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡንደስሊጋ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያሉት ቡድኖች የሰበሰቡት ነጥብ በቀጥታ ወደ ቡንደስሊጋው ለማለፍ ዕድል ይሰጣቸዋል ። አንድ ዙር ቀሪ ጨዋታ እየቀረ ሐምቡርግ በ59 ነጥብ ይመራል ።  ኮሎኝ በ58 ይከተላል ። ኤልቨርስበርግ እና ፓዴርቦን 55 ነጥብ አላቸው ።  ዱይስልዶርፍ እና ካይዘርስላውተርንም በ53 ነጥባቸው ገና የማለፍ ዕድላቸው አልመከነም።

አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ በጀርመን ቡንደስሊጋ ምሥጢር ሁኖ የቆየውን  ከባዬርን ሌቨርኩሰን የመለየቱን ጉዳይ አረጋግጧልምስል፦ Harry Langer/dpa/picture alliance

ዣቪ አሎንሶ ከባዬርን ሌቨርኩሰን መለየቱን ይፋ አድርጓል 

አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ በጀርመን ቡንደስሊጋ ምሥጢር ሁኖ የቆየውን  ከባዬርን ሌቨርኩሰን የመለየቱን ጉዳይ አረጋግጧል ። ባዬርን ሌቨርኩሰንን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደረሰው ዣቪ አሎንሶን ሪያል ማድሪድ በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን መጠናቀቂያ ይጠብቀዋል ። ዣቪ አሎንሶ ባለፈው ሳምንት ዐርብ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የባዬርን ሌቨርኩሰን ውሉ ለመጠናቀቁ ገና አንድ ዓመት ይቀረው እንደነበረም ገልጧል ።

በሌላ ዜና፦ ለባየርን ሙይንሽን የረዥም ዘመን ተጫዋች በመሆን ክብረ ወሰን የሰበረው አጥቂ የ35 ዓመቱ ቶማስ ሙይለር ከቡድኑ ስንብት ተደረገለት ። በአሊያንትስ አሬና ቅዳሜ ዕለት የተሰናበተው በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ0 ካሸነፉ በኋላ ነው ።  ቶማስ ሙይለር ለባየርን ሙይንሽን  750 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል ። የዘንድሮውን ጨምሮ 13 የቡንደስሊጋ ዋንጫዎችን ቡድኑ ሲያሸንፍ አብሮ ነበር ። ለሁለት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም በጀርመን ብሔራዊ ቡድኑ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫዎችንም ማንሳት ችሏል ። ቶማስ ሙይለር በባየር ሙይንሽን ታሪክ ከጌርድ ሙይለር (570) እና ሮቤርት ሌቫንዶብስኪ  (344) ቀጥሎ 248 ግቦችንን በማስቆጠር ሦስተኛ ግብ አግቢ ነው ።  222 ግብ ሊሆኑ የሚችሌ ኳሶችንም በማመቻቸት ይታወቃል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW