የግእዝ ቋንቋን የማስመዝገብ ጥረት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2015
የግእዝ ቋንቋና የአፃፃፍ ስርዓቱን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየጣሩ መሆናቸዉን ዉጪ የሚኖሩ ምሁራን አስታወቁ።ጥንታዊዉን ቋንቋ በቅርስነት ለማስዝገብ ዘመቻ መጀመራቸዉን ያስታወቁት ምሁራን እንደሚሉት፣ግዕዝን በዓለም ቅርስነት ሊያስመዘግበው የሚያስችለው ታሪክና አስፈላጊ ማስረጃዎች አሉት።የግዕዝ ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት የኢትዮጵያ የባህል ቅርሶች ዋነኛ ክፍል ነው የሚሉት ምሁራኑ፣ እውቅና እና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል የሚል እምነት አላቸው።
ይህን ዘመቻ የሚያስተባብሩት ዶክተር አበበ ከበደ፣ግዕዝና የአፃፃፍ ስርዓቱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ምሁራኑ ለምን እንደተነሳሱ ከዶይቸ ቨለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ እንደሚከተለው ገልጸዋል።"ግዕዝ የኢትዮጵያ ንብረት ነው። ስለዚህ ብዙ ነገር አስመዝግበናል። ኢትዮጵያውያን ብዙ ነገር አስመዝግበናል።ገዳ ስርዓት ተመዝግቧል፣ጨምባላላ ተመዝግቧል፣ጥምቀት ተመዝግቧል፣እና ይሄኛውም መመዝገብ አለበት።እንደ ዓለም ቅርስ ግዕዝ የዓለም ታሪክ ጠባቂ ተብሎ በቋንቋም ሆነ በጽሑፍ መመዝገብ አለበት በሚል ነው የተነሳነው።"
ግዕዝ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ሃይማኖትና ማኀበረሰብና ሥልጣኔ ጋር ለረጅም ዘመናት በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑንም ዶክተር ከበደ አመልክተዋል።"ግዕዝ ይህን ሁሉ ታሪክ ይዞ ከ380 ጀምሮ ከእዛም በፊት፣ ጸሎት የሚደረግበት ማለት ነው። ከንግስተ ሳባ ጀምሮ የፊደሉን የቋንቋውን ዕድገት ስንመለከት፣ከሳባ ጀምሮ ነው መታየት ያለበት።ከሳባ ጀምሮ የንግድ፣ የስነጽሁፍ፣ሙዚቃ ሲያገለግል የቆየ ቋንቋ ነው። አሁንም እያገለገለ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ጸሎትን ይዟል።ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ ትልልቆቹን መጻህፍት በመዝገቡ ይዞ ቁጭ ብሏል።ስለዚህ ግዕዝ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ውለታ ነው።"
ግዕዝን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ የተጀመረ ሲሆን፣በዚሁ እንቅስቃሴ ከሚሳተፉት መኻከል አቶ መኮንን እሸቴ ይገኙበታል።"ከሁሉ በላይ እኔ ያሳሰበኝ እና ወደዚህ ነገር እንድመጣ ያደረገኝ፣ኢትዮጵያ ለብዙ ሺ ዓመታት ኖረች ሃገር ነች እና በቋንቋም ይሁን በባህል የተለያዩ ታሪኮች ውስጥ በዓለም ታውቃለች።እና ለዚህ ሁሉ ቀደምት የሆነ ነገር ለአንድ ሃገር ዕድገት ከኢኮኖሚ፣ከሳይንሱ ከሁሉ በላይ ቋንቋ ነው፤መግባቢያ ቋንቋ ነው።"ከታሪክና ከሃይማኖት እስከ ስነጽሁፍና ኪነጥበብ ድረስ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ያካተቱ የመጽሐፍት ጥራዞች በግዕዝ ተጽፈው እንደሚገኙ ተመልክቷል።
የግዕዝ አፃፃፍ ስርዓት ልዩ ከመሆኑ በላይ፣ በዓለም ለሚገኝ ማንኛውም የቋንቋ አፃፃፍ የሚያገለግል የተራቀቁ የአጻጻፍ ስርአት እንዲፈጠር ማድረጉ ተመልክቷል።ምሁራኑ እንዳሉት፣ይህ ሥርዓት፣ ለዓለም ባህላዊ ቅርሶች ወሳኝ አስተዋጽኦ ነውና እውቅና ሊሰጠው ይገባል።
ግዕዝ በዓለም ቅርስ ሆኖ መካተቱ፣ የባህል ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመጭው ትውልድ ለማቆየት እንደሚረዳም ጭምር።ዮኔስኮም ምሁራኑ የሚያቀርቡትን አቤቱታ ተመልክቶ፣የግዕዝ ቋንቋና የግዕዝ አፃፃፍ ስርዓትን፣የዓለም ቅርስ አድርጎ እንዲያውቅ የሚጠይቁት ምሁራኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጀመሩት የፊርማ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ፣በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዚሁ ዘመቻ ቀጣይ ሂደት ምን እንደሚሆን የጠየቅናቸው ዶክተር አበበ የሚከተለውን ብለዋል።"ይህ ፊርማ፣ማናቸውም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ነው። ይህ ነገር ቢፈረም ጥሩ ነው ብለው ሰዎች እንዲፈርሙ ነው የመጀመሪያው እሱ ነው።ምንድነው የሰዉ ስሜት ነው ይኼ።አሁን ረቂቁ በሚዘጋጅበት ጊዜ፣እኛ በኮሚቴያችን የሚያደርጉት ነገሮች ከተጻፉ በኇላ ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ መጠናከሩ ከታየ በኋላ፣የሕብረተሰቡ ፍላጎት መሆኑን ካሳየን በኋላ፣የሚሆነው ነገር ይህ እንግዲህ እንደውጭ የሚኖሩ ዜጎች እንቅስቀሴ ተደረጎ ሊቆጠር ይችላል።"በሂደትም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስታት አካላት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ዶክተር አበበ አብራርተውልናል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ