የግዕዝ ቋንቋ እና ፋይዳዉ
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2018
የግዕዝ ቋንቋ እና ፋይዳዉ
የግዕዝ ቋንቋን በትምህርት ስርዓት ዉስጥ ማካተት ጉዳቱ ምኑ ላይ ነዉ? አንዳንድ ምሁራን የግዕዝ ቋንቋ የመግባብያ ቋንቋ ባለመሆኑ እየሞተ ያለ፤ አልያም የሞተ ቋንቋ ነዉ ሲሉ፤ አስተያየት ይሰጣሉ። ይሁንና ግዕዝ አልሞተም፤ በርካታ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ፍልስፍናን የያዘ ቋንቋ ነዉ ሲሉ የሚከራከሩም አሉ። ከአንድ ወር ገደማ በፊት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን በ1ኛ እና በመካከለኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ መወሰኑን ተከትሎ ፤ ግዕዝን ማስተማር ሃይማኖትን እና ባህልን ለማስረፅ እየተደረገ ያለ እርምጃ ነዉ ሲሉ ለተቃዉሞ የወጡ እንደነበሩ ተመልክቷል። የግዕዝ ቋንቋን መማር ሃይማኖት እና ባህልን መማር / ማስተማር ነዉ ብለዉ ያምናሉ?
ግዕዝ እንደ ማንኛዉም ቋንቋ ነዉ። ኢትዮጵያ የራሴ የምትለዉ ቋንቋ ፊደል ቁጥር አለኝ ብላ የምትኩራራበት ግዕዝ ነዉ። በትምህርት ቤት መሰጠት መጀመሩ ጥሩ ጅማሬ ነዉ፤ ይበል ያሰኛል። ግዕዝ እምነት ነዉ ብለዉ ለሚቃወሙ፤ የግብፅ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ኦርቶዶክሶች፤ ለቅዳሴ እና ስብከት የሚገለገሉበት ቋንቋ አረብኛ ነዉ። ስለዚህ በእነሱ አባባል አረብኛ ቋንቋም የእስልምና እምነት ሊባል ነዉ? ሲሉ አቡ ሃበሻ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያን የግዕዝ ቋንቋ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ንቅናቄ ከጀመሩ አስር ሽህ ኢትዮጵያዉያን መካከል ፕሮፊሰር አበበ ከበደ ቀዳሚ አስተባባሪ ናቸዉ። ፕሮፊሰር አበበ ከበደ በኖርዝ ካሮላይና ዉስጥ በሚገኘዉ ኖርዝ ካሮላይና የግብርና ቴክኒካል ዩንቨርስቲ መምህርም ናቸዉ።
ፕሮፊሰር አበበ ከበደ ፤ አቶ አበበ ተብለዉ መጠራትን እንደሚፈልጉ ነግረዉናል። የግዕዝ ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋ አይደለም፤ በመሆኑም አንዳንድ ምሁራን የግዕዝ ቋንቋ የሞተ ቋንቋ ነዉ ነዉ ሲሉ አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል፤ እርሶ በዚህ ይስማማሉ ስንል አቶ አበበ ከበደን ጠይቀናቸዋል።
በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በብዙ ጥበብ የተሞሉ መጻሕፍትን ለማወቅና ለመመርመር ቋንቋዉን ማወቁ ትልቅ ጥቅም አለዉ ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ሊቃዉንቶች ይናገራሉ። የግዕዝ ቋንቋን ማወቅ ስለ ኢትዮጵያ ምንነት ማወቅ መሆኑን፤ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳዩ ብዙ መጻሕፍትን ለመረዳትም ጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ። የግዕዝ ቋንቋ በስራ ላይ የነበረበት ዘመን የኢትጵያ ከፍታ ዘመን እንደነበር የቋንቋዉ ሊቃዉንቶች ይናገራሉ። በእርግጥ የግዕዝ ቋንቋ ሞቷልን፤ ስንል በወሎ ዩንቨርስቲ የግዕዝ ቋንቋ እና ስነ-ጽሑፍ መምህር የሆኑትን ይባል የፈቀደን ጠይቀናቸዋል።
ከሩብ ምዕተ-ዓመት በፊት እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 1982 ዓመት ትውልደ-ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ሳይንቲስት ዶ/ር አበራ ሞላ የግእዝ ፊደላትን በኮምፒዩተር በተንቀሳቃሽ ስልኮች በመሳሰሉ ስነ-ቴክኒክ ዘርፍ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲጻፍ በማስቻላቸው በሚኖሩበት ዩናይትድ ስቴትስ አምስት የፈጠራ መብት ባለቤትነት ዕውቅናን ከኢትዮጵያ ሦስት የባለቤትነት እዉቅናን ተቀብለዋል። ዶ/ር አበራ ግዕዝ ቋንቋ ሞትዋል የሚባለዉ አስተሳሰብ ትክክለኛ ያልሆነ ሲሉ ገልፀዉታል።
ዶ/ር አበራ በግዕዝ ቋንቋ ያልተተረጎሙ ከ 50 ሺህ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍት እንዳሉ ተናግረዋል። የሴማዊ ቋንቋዎች አባል የሆነዉ የግዕዝ ቋንቋ፤ የጥንት የሰዉ ልጅ ታሪክን የያዙ መሆናቸዉ ይነገራል። በዚህም ጀርመንን ጨምሮ በርካታ የአዉሮጳ ሃገራት በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ ጥንታዊ መጻሕፍትን በማገላበጥ ማጥናት ከጀመሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል። ጀርመናዉያን በአፍሪቃ ቀንድ በኢትዮጵያና በኤርትራ ከጥንት ጀምሮ ሲያገለግል ስለቆየዉ ስለ ግዕዝ ቋንቋ በጥልቀት ማጥናት ከጀመሩ እጅግ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በጀርመን ሃምቡርግ ከተማ በላይፕዚግ ከተማ እና በበርሊን ከተማ በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ዉስጥ የግዕዝ ቋንቋ ጥናት እና መማር ማስተማር ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። የኢትዮጵያ ባህል ቋንቋ ጥናት በአዉሮጳ እንዲጀመር ያደረገችዉ የመጀመርያዋ አዉሮጳዊት ሀገር ጀርመን መሆንዋም ይታወቃል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የግዕዝ ቋንቋን በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል የሚከተለዉ በጥቂቱ እንዲህ ይደመጣል።
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ