የግዙፉ የገበያ ማዕከል - የመርካቶ የዛሬ ውሎ
ሰኞ፣ ኅዳር 9 2017በኢትዮጵያ ግዙፉ የንግድ ስፍራ መርካቶ ውስጥ ዛሬ ሰኞ ሕዳር 9 ቀን 2017 ዓ. ም አንዳንድ ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን ሸማቾችም ነጋዴዎችም ለዶቼ ቬለ ገለፁ። የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ በጉዳዩ ላይ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ግን "መርካቶ በመደበኛ ግብይት እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች" በማለት ከአራት ሰዓታት በፊት በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ጽፏል።
አንድ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ ለመግዛት ወደ ታወቀ የመርካቶ የንግድ ማዕከል ሄዳ የነበረች ሸማች አካባቢው "ተዘግቶ ነበር የዋለው" ስትል ገልፃለች። ሌሎች በመርካቱ ዙሪያ ዳር አካባቢ የሚሠሩ ነጋዴዎች ደግሞ ሱቆች አለመዘጋታቸውን እና እስከ አመሻሹ ድረስ ከፍተው እየሠሩ እንደሆነ ተናግረል።
መርካቶን በስልካችን
በአዲስ አበባ የሚገኘው ግዙፍ የገበያ ሥፍራ መርካቶ ውስጥ መንግሥት ለእያንዳንዱ ግብይት ደረሰኝ እንዲቀርብ ሰሞኑን ጥብቅ ክትትል ማድረግ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ውዥንብር እየተስተዋለ ነው። በዛሬው ዕለትም በገበያ ማዕከሉ በዛ ያሉ ሱቆች ይህንን በመቃወም ተዘግተው ስለመዋላቸው ተሰምቷል።
መርካቶ ውስጥ ወደ ሚታወቅ አንድ የሕንፃ የንግድ ሥፍራ ያመራች አንድ ሸማች "ዝግ ነበር" በማለት "ድባቡ ጥሩ ስላልነበር" ትታ መመለሷን እና የንግድ ሱቆች "ተዘጋግተው እንደነበር" ተናግራለች።
መርካቶ ሱቆች የተዘጉባቸው ስፍራዎች የመኖራቸውን ያህል፣ ክፍት ሆነው የዋሉባቸው እንደነበሩም ሌላ አስተያየት ሰጪ ለዶቼ ቬለ ተናግሯል።
ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንትም መሰል ሥራ የማቆም አድማ ስለመመታቱ በስፋት መነገሩን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ "በመርካቶ እየተከናወነ የሚገኘው ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል እየተሰራ ያለ ሥራ ሲሆን ለዚህም የንግዱ ማኅበረሰብ ተባባሪ ሊሆን ይገባል" ብሎ ነበር።
መርካቶ የተከሰተው ሌላኛው የእሳት አደጋ
"በመርካቶ አካባቢ አንዳንድ ነጋዴዎች ንብረት ሊወረስ ነው፤ ሱቃችን ሊዘጋ ነው የሚል መሰረት የሌለው ውዥንብር ውስጥ መግባታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተመልክተናል" ሲል ገልጾ የነበረው የከተማ አስተዳደሩ በደረሰኝ እንዲገበያዩ የሚጠበቅባቸው ነጋዴዎችን በመለየት በደረሰኝ ግብይት እንዲፈጽሙ የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ጊዜያት ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱም ገልጾ ነበር። ዛሬ ስለተፈጠረው ክስተት ግን እስከ ምሽት 12:00 ድረስ ያለው ነገር የለም።
መርካቶ የሚገኝበት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ግን "መርካቶ በመደበኛ ግብይት እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች" ሲል በክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን በኩል ገልጿል። አንድ ከመርካቶ ተማሮ የንግድ ሱቁን ዘግቶ የወጣ ነጋዴ የችግሩ መነሻ ያለውን ምክንያት ገልጾልናል። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የጠየቅናቸው በዛ ያሉ ነጋዴዎች ለደህንነታቸው ከመስጋት በመነሳት ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ