1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግጭት ተጋላጭነት ምክንያቶችና የሰላም ሚኒስቴር ማብራሪያ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ "ሥር የሰደዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ" ምክንያቶች ለግጭት ተጋላጭነት መነሻ ኾነዋል ሲል የሰላም ሚኒስቴር ገለፀ። "ብሔር " አንዱ የሀብት መሰብሰቢያ መንገድ ስለሆነ "ለብሔርተኝነት መስፋፋት" መነሻ ሆኗል ሲሉ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ የተቋሙን ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባ ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የግጭት ተጋላጭነት ምክንያቶችና የሰላም ሚኒስቴር ማብራሪያ

This browser does not support the audio element.

የግጭት ተጋላጭነት ምክንያቶችና የሰላም ሚኒስቴር ማብራሪያ 

ኢትዮጵያ ውስጥ "ሥር የሰደዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ" ምክንያቶች ለግጭት ተጋላጭነት መነሻ ኾነዋል ሲል የሰላም ሚኒስቴር ገለፀ። "ብሔር " አንዱ የሀብት መሰብሰቢያ መንገድ ስለሆነ "ለብሔርተኝነት መስፋፋት" መነሻ ሆኗል ሲሉ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ የተቋሙን ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ ገልፀዋል። የሀገሪቱ ዋና ዋና የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ተጠሪነታቸው ለሚኒስቴሩ በነበሩበት ወቅት በሕዝብ ዘንድ ስለ ሰላም የተያዘው አመለካከት እንዳለ ነው ያለው ሚኒስቴሩ ተቋሙ አሁን ያለው አደረጃጀት መከለሱ በዚህ ረገድ አንድ ችግር መሆኑ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው "የፀጥታ መደፍረስ" ከፍተኛ መሆኑንና ይህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ገጠሙኝ ካላቸው ዋነኛ የሰላም ችግሮች አንዱ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገልጿል። 

ሚኒስቴሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ "የአስተዳደር ወሰን" ግጭቶች፣ ኢ-መደበኛ የተባሉ ታጣቂዎች እንቅስቃሴዎች እና የብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶች በዘላቂነት እንዴት ሊፈቱ ይገባል? ሚኒስቴሩስ ምን እየሠራ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበውለታል። ለዚህ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ድዔታ ቸሩጌታ ገነነ "ሥሩ የሰደዱ" ያሏቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል። 

"አንዱ የግጭት ተጋላጭነት ምክንያት ሥር የሰደዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ናቸው ስንል አለመግባባቶች አሉ፣ ድህነት አለ፣ ድህነት ዋናው ምክንያት ነው"። የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ "በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ" ብቻ የሚፈታ መሆኑን የገለፁት ባለሥልጣኑ ችግሮቹ መዋቅራዊ በመሆናቸው በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ለመፍታት  እንዳልተቻለ ገልፀዋል። 

"የማሕበረሰብ ዓላማ አስፈጽማለሁ ብሎ ይነሳል፣ በመሰረታዊነት ኢኮኖሚያዊ ይሆናል"። 

ዋና ዋና የሚባሉት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ተጠሪነታቸው በሥሩ ሆነው የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ተቋሙ ከተፈጠረ ጀምሮ በኢትዮጵያ "ሰላም ርቋል" የሚል ብርቱ ትችት እየቀረበበት ቆይቷል። ሕልውናው ላይም ጥያቄ ሲነሳበት ነበር። ዛሬ ሰኞ የዘጠኝ ወራት ሥርራውን ለውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ግን ይህ ወቀሳ "የተሳሳተ አመለካከት" ስለመሆኑ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ አደረጃጀቱ ከነበረው ተሻሽሎ የተስተካከለ ቢሆንም አሁንም ስለ ሚኒስቴር የተያዘው አተያይ ግን አንድ መሠረታዊ ችግር እንደሆነባቸው ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ ኢድሪስ ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ

የኢትዮጵያ ፌደሬሽን ምክር ቤት ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የሰላም ሚኒስትር ድዔታ ቸሩጌታ ገነነ እንዳሉት በዚህ ሀገር የተፈናቃይ ዜጎች ጉዳይ ከሰብአዊ ጉዳይነት እየወጣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መልክ መላበሱንም አብራርተዋል። 

"ተፈናቃዮችን መመለስ የሚባለው ጉዳይ ሰብአዊ ከሆነው ነገር አንዳንዴ እየወጣ ነው አስቸጋሪ ያደረገው"። 

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ ኢድሪስ መሠረታዊ የሀገሪቱ የፀጥታ ችግሮችን የሰላም ምኒስቴር ብቻ እንዲፈታ መጠበቅ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ትርክቶችን ለበጎ ነገር መጠቀም፣ በወጣቶች ላይ አንድነትን ማስረጽ፣ የሃይማኖት ተቋማት ስለ ሰላም አጥብቀው እንዲሠሩ ማድረግ የሚመሩት ተቋም "ሰላምን ለማስፈን" ጥረት እያደረገባቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW