1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎርፍ አደጋ በጋምቤላ በርካቶችን አፈናቀለ

ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2014

በጋምቤላ ክልል ስምንት በሚደርሱ ወረዳዎች ውስጥ ከሳምንት በፊት በደረሰው የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ። የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ወደ መቶ ሺህ መድረሱንና 386 በሚደርሱ ከብቶች ደግሞ በጎርፍ አደጋው መሞታቸውን አክለዋል።

Äthiopien | Südsudan | Grenzregion Gambela
ምስል Alemenw Mekonen/DW

«ጎርፍ በጋምቤላ ጉዳት ማድረሱ»

This browser does not support the audio element.

በጋምቤላ ክልል ስምንት በሚደርሱ ወረዳዎች ውስጥ ከሳምንት በፊት በደረሰው የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ። በአደጋው ከተፈናቀሉ ዜጎች በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁም እንስሳትም መሞታቸውን የቢሮው ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን  ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ወደ መቶ ሺ መድረሱንና 386 በሚደርሱ ከብቶች ደግሞ በጎርፍ አደጋው መሞታቸውን አክለዋል። ከፌደራል መንግሥት እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ሰብአዊ ድጋፍ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ከሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል በደረሰው የጎርፍ አደጋ በክልሉ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። በአደጋው የሁለት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን 1558 ፍየል እና 117 በጎች ደግሞ በጎርፍ እንደተወሰዱ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን  አብራርተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ለማዳረስ 10 ሚሊዩን ብር መመደቡን ኃላፊው አመልክተዋል። በአደጋው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ የክልሉ መንግሥትና የግል ተቋማት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ በክልሉ አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ሰብአዊ ድጋፍ ከፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን  እንዲላክላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡ 
በክልሉ ላረ በተባለ ወረዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው መፈናቀሉንና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳትም ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል። ከዚህ ቀደም ከደቡብ ሱዳን  ከመጡት ተፈናቃዩች በስተቀር በክልሉ በመጠለያ ጣቢያ የሚኖር  ተፈናቃይ እንደሌለ አቶ ጋትቤል አብራርተዋል፡፡ በጋምቤላ በጎርፍ  ለተፈናቀሉ ዜጎች እስካሁን ከ50 በላይ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ነው የተናገሩት። በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ተቋማት  የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ እንዲሳተፉ ጥሪ  ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሁለት ቀን በፊት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ባስተላለፈው መልዕክት የክረምት መደበኛ ዝናብ በሰሜን ምሥራቅ፣ በምስራቅ፣ በመካከለኛው እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖረው አመልክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተጠቀሱት ስፍራዎች በየጣልቃው በሚኖረው ጠንካራ የፀሐይ ሀይል በመታገዝ ከሚፈጠረው የደመና ክምችት ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ

ምስል Gambella Government Communication Office

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW