የጎርፍ አደጋ ጉዳትን መልሶ ለመጠገን እንቅስቃሴ ተጀምሯል
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 21 2012
ከቀናት በፊት በድሬደዋ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በተለያዩ መሰረት ልማቶች ላይ ያደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመጠገንና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የተባሉ ስራዎችን ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን የድሬደዋ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ቤት አስታወቀ፡፡አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ መደረጉም ተገልፃል ፡፡ የከተማዋ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱሰላም መሀመድ ለDW በስልክ እንደገለፁት አስተዳደሩ አደጋው ካጋጠመበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን እና በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ የሚሆኑ ተግባራትን ለማከናወን በጀት ተመድቦ ወደ ስራ ገብቷል ፡፡ ከቀናት በፊት የተከሰተው ጎርፍ ጉዳት ያስከተለባቸው አካባቢ ነዋሪዎች አንዱ በሰጡት አስተያየት ለውሀ መውረጃ የተሰሩ መውረጃ ዲቾች ጉዳቱን እየባባሱ ነው ብለዋል ፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪም ስራዎች ከመሰራታቸው በፊት ህብረተሰቡን ማወያየት ይገባል ብለዋል ፡፡ ከውሀ መውረጃ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን አቤቱታዎች በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አብዱሰላም ተከታዩን ምላሽ ሰተዋል ፡፡ በሌላ በኩል የአስተዳደሩ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ማስተባበርያ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ በጉረፉ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት የተመለከተ ዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ የተገኘውን ውጤት ገልፀው ውጤቱን መነሻ በማድረግ የምግብ እና ሌሎች ድጋፎች መደረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡ አቶ ሀርቢ የንብረት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በሚመለከት የባለሞያ ቡድን መቋቋሙንና በጥናት ውጤቱ መሰረት አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ፡፡ መስተዳድሩ ለችግሩ መፍትሄ ያላቸውን ስራዎች ለመስራት እያደረግኩት ነው ከሚለው ጥረት በመለስ ስራዎቹን ሰርቶ ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜን ጨምሮ በከተማዋ በሰሞኑ የተከሰተውን ዓይነት የጎርፍ አደጋ ቢያጋጥም ጉዳቱን መከላከል ከባድ መሆኑን አመላካች ነገሮች ብዙ ናቸው ፡፡ ስራዎቹ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ጊዜ የሚወስዱ መሆን ሌላው ተግዳሮት ነው ፡፡ የሰራ ኃላፊዎቹ ህብረተሰቡ መረጃዎችን በመከታተል ራሱን በንቃት እንዲጠብቀ አስገንዘብዋል ፡፡
m,saie t,kelu
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ