የጎንደርን ገና ያደበዘዘው ግጭት በጥምቀት በዓል ላይ ጥላውን አሳርፏል
ረቡዕ፣ ጥር 1 2016ገናን የበዓል ድባብ ርቋት ያሳለፈችው የጎንደር ከተማ ካለፈው ሰኞ ወዲህ መረጋጋት ታይቶባታል። የጎንደር ነዋሪዎች ማኅበራዊ ተቋማት እና የሕዝብ መጓጓዣዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማው ነዋሪ “አሁን ሠላም ሆኗል፤ በአሁኑ ሰዓት ምንም ችግር የለም ተረጋግቷል” ሲሉ ተናግረዋል። ሌላ ነዋሪ “አሁን ጎንደር ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል። ሠላም ነው። ምንም ዓይነት ነገር የለም” ሲሉ አስረድተዋል።
ከገና ዋዜማ ጀምሮ በጎንደር ማራኪ ክፍለ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረገው ውጊያ የበዓሉን ድባብ አደብዝዞ ሥጋት የፈጠረ ነበር። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የጎንደር ነዋሪ “የበዓል ቀን ከቤት አልወጣንም። አብዛኛው ሰንጋ ገዝቶ አላረደም፤ ቅርጫ የሚያመጣ አልተንቀሳቀሰም። የትም ቦታ እንቅስቃሴ አልነበረም” ሲሉ ተናግረዋል።
ገና በአማራ ክልል የግጭት ድባብ እና የዋጋ ንረት ተጭኖታል
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ስድስት የጎንደር ነዋሪዎች ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 በማራኪ ክፍለ ከተማ በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደተቀሰቀሰ ይናገራሉ። ግጭቱ የገና ዕለት ማለትም ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 መቀጠሉን ዶይቼ ቬለ መገንዘብ ችሏል።
“ዓርብ ለት ኅዳሴ በሚባለው አካባቢ ግርግር ነበረ። ያንን ግርግር ተከትሎ ወደ ማታ አካባቢ ከዐሥር ሰዓት ጀምሮ ተኩስ እየበዛ ሔደ” የሚሉ የከተማው ነዋሪ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጭምር የተሳተፉበት ግጭት የገና በዓል ዕለት ጭምር ቀጥሎ እንደነበር ገልጸዋል።
“ታጣቂዎች የፋኖ ኃይሎች ገቡ” የሚል መረጃ በከተማው መሠራጨቱን የሚናገሩ ሌላ የጎንደር ነዋሪ “በሰዓቱ ከፍተኛ ተኩስ በርቀት ይሰማ ነበር” ሲሉ የታዘቡትን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። “እየተሯሯጥን ወደ ቤታችን ገባን” የሚሉት ነዋሪ ቀበሌ 18፣ ሸዋ ዳቦ፣ ኅዳሴ በሚባሉት አካባቢዎች “በጣም ከፍተኛ ውጊያ” እንደነበር ገልጸዋል። “እጅግ ከባድ መሣሪያዎች ይተኮሱ ነበር” ሲሉ የጎንደሩ ነዋሪ አክለዋል።
ዶይቼ ቬለ ስለ ግጭቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ የእጅ ስልክ በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ አላገኘም። የጎንደር ከተማ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀውን ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።
ያልተቋጨ ሥምምነት፣ የተቋረጠ የሰላም ንግግር፣ ያልተጀመረ ድርድር፤ ማይክ ሐመር ይሳካላቸዋል?
እስካሁን በውጊያው ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም። “በውጊያውም ሰዓት ባይሆን ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ትንሽ ረገብ ሲል [ወደ ቦታው ሔጄ] አይቻለሁ” የሚሉ ነዋሪ “ብዙ ያልተነሳ የመከላከያ አስከሬን ነበር” ብለዋል።
“በነጋታው እስከ ታኅሣሥ 29 ድረስ ያልተነሳ አስከሬን ነበር። በብዛት ቤቶች ነው የተደበደቡት። እኔ ከአንድ ቤት አምስት ሰው ተመትቶ ሦስት ሲሞት፣ ሁለት ደግሞ ቁስለኛ እንደነበሩ አይቻለሁ። ሌላ ደግሞ በተመሳሳይ ከሌላ ቤት ሁለት ሕጻናት ሲሞቱ አይቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላ የጎንደር ነዋሪ በበኩላቸው “ጦርነት ስለሆነ በተኩስ ልውውጥ መካከል ተፈናቃዮች፤ ከቤታቸው ያሉ ሰዎች እንደሞቱ ነው እኛ የሰማንው” ሲሉ ተናግረዋል።
“ንጹሀን እንዳለቁ ጓደኞቻችን ነግረውናል” የሚሉ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “በጣም የሚያሳዝን ግጭት ነበር የነበረው። [የሞተው ሰው] ቁጥር አይታወቅም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ጓደኞቻቸው “ሰኞ ዕለት ስንቀብር ዋልን” የሚል መረጃ እንደነገሯቸው የገለጹት የጎንደር ነዋሪ በቅዳሜ እና እሁድ ተኩስ የተገደሉ ሰዎች ሥርዓተ ቀብር የተከናወነው ሰኞ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ85 ሺህ በላይ እንስሳት ከድርቅ ጋር በተያያዘ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ
ጎንደር ከሚያዝያ 2015 ጀምሮ በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተደጋጋሚ ትንቅንቅ የተደረገባት ከተማ ነች። በሐምሌ 2015 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ ክልሉ በአራት የጸጥታ ዕዞች እንዲተዳደር ሲወሰን ጎንደር “በሰሜን ምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት” ሥር ተካታለች። ለስድስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ይሁን የተዘረጋው አወቃቀር ግን የአማራ ክልል ለገባበት ቀውስ መፍትሔ አልሆነም።
ገናን በሥጋት ውስጥ ያሳለፉት የጎንደር ነዋሪዎች መጪው የጥምቀት በዓል አከባበርም አስግቷቸዋል። “የጥምቀት በዓል ይከበራል ተብሎ እየታሰበ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ እንግዶች ይገባሉ ነው የሚባለው” የሚሉት አንድ የከተማው ነዋሪ “ነገር ግን እስካሁን ምንም የሚታይ ነገር የለም። የፍራቻው ነገር እንዳለ ነው። እንቅስቃሴው ራሱ ይኸን ያክል አጥጋቢ አይደለም” ሲሉ የግጭቱ ሥጋት በመጪው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ እንዳረበበ አስረድተዋል።
“ሰዉ በልደት በዓል ላይ እንዲህ ዐይነት ችግር ስላጋጠመው ሥጋት ስላለ ነው መሰለኝ በበዓሉ ላይ ምን ዐይነት ነገር ሊኖር እንደሚችል ማወቅ አልተቻለም” የሚሉ ሌላ የጎንደር ነዋሪ “ድንገተኛ የተኩስ ልውውጥ ሊኖር ስለሚችል ሰዉ አሁንም ድረስ በዓሉን በሰፊው ለማክበር ይኸን ያህል ፍላጎት ያለው አይመስልም” ሲሉ የታዘቡትን ገልጸዋል።
ነዋሪዎች ሥጋት ቢጫናቸውም የጎንደር ከተማ እና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ጥምቀትን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ ነው። በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል የሀገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኚዎች ወደ ጎንደር ብቅ የሚሉበት ነበር።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ