1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎፋው ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 2016

“የሠው ልጅ እንደ ድንች ከመሬት እየተቆፈረ ሲወጣ አይቼ አለቀስኩ» ይላሉ በጎፋ ዞን ስለደረሰው አሰቃቂ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለዶቼ ቬለ የገለጹ አንድ የዐይን እማኝ። እስካሁን በተደረገ ቁፋሮ ከ229 በላይ አስክሬን ሲወጣ ሰባት ሰዎች ከአንገት በታች በአፈር ተቀብረው በሕይወት መገኘታቸውን የዞኑ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

የመሬት መናዱ ሰለባዎች
በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተቱ የተጎዱ ወገኖችን ፍለጋው አሁንም ቀጥሏል።ምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

የጎፋው ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ

This browser does not support the audio element.

 

የጎፋው ዘግናኝ አደጋ በነዋሪዎች ዐይን

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በምትገኘው የኬንቾ ሻቻ ቀበሌ ነዋሪዎች ንጋት ላይ የወትሮ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩ ቢሆንም ረፋድ ላይ ግን ያልጠበቁት ነው የገጠማቸው። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ሟቾች በሥፍራው የተሰባሰቡት በሁለት መኖሪያ ቤቶች ላይ የተጫነውን የመሬት ናዳ ለማንሳት ነበር። ነገር ግን ሳይታሰብ ለሁለተኛ ጊዜ የመጣው ተጨማሪ የናዳ ክምር ለበርካቶች ሞት ምክንያት መሆኑን ነው አንድ የመንደሩ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት።

«አስክሬን ከመሬት እየወጣ ነው»

አቶ ዘለቀ ዶሳ የጎፋውን አደጋ እንደሰሙ የቅርብ ዘመዶቻቸውን ለመፈለግ ከአጎራባች የሳውላ ከተማ ተነስተው ዛሬ ረፋድ ላይ የኬንቾ ሻቻ ቀበሌ መድረሳቸውን ይናገራሉ። አደጋው በመገናኛ ብዙሃን ከሚገለጸው በላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘለቀ «የሰው ልጅ እንደ ድንች ከመሬት እየተቆፈረ ሲወጣ አይቼ አለቀስኩ። የተደረመሰው ናዳ ሲነሳ ሬሳ በሬሳ ላይ ነው ተደራርቦ የተገኘው። አሁን ላይ በመንደሩ በርካታ መቃብሮች እየተቆፈሩ ይገኛል። ቀበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት በአንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ ሆኖ ሀዘንተኛው ግን በአንድ የጋራ ድንኳን እንዲቀመጥ ተደርጓል። በአጠቃላይ አደጋው ዘግናኝና ለአእምሮ የሚከብድ ነው» ብለዋል።

የተረፉ ነፍሶች

የጎፋው  የመሬት መንሸራተት አደጋ እስካሁን ከ229 በላይ አስክሬን መገኘቱን የዞኑ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ሰባት ሰዎችም ከአንገታቸው በታች በጭቃ ተቀብረው በሕይወት መገኘታቸውን የገዜ ጎፋ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሀላፊ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

በሕይወት የተገኙት አምስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች መሆናቸውን የጠቀሱት የጽሕፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ የዓለም መሪነህ አስፋው «ሰዎቹ በሕይወት የተገኙት ከአንገታቸው በታች በናዳ ጭቃ ተቀብረው» መሆኑን የጠቀሱት ሀላፊው በእጅ፣ በእግርና በወገባቸው ላይ ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል። ተጎጂዎቹ በአካባቢው ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ለተሻለ ህክምና ወደ ሳውላ ሆስፒታል እንዲወሰዱ መደረጉንም ገልጸዋል።

እስካሁን በአደጋው የሞቱ ከ200 በላይ አስከሬኖችን ማውጣት ተችሏል።ምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

በሳውላ ሆስፒታል ከገቡት ሰባት ተጎጂዎች መካከል ቀላል ጉዳት ያጋጠማቸው ሁለት ሰዎች ታክመው መሸኘታቸውን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶክተር ጊላንዶ ጊሌ የቀሪዎቹ ጉዳት ግን «ከበድ ያለ ስለሆነ እንዲተኙ ተደርጎ የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል» ብለዋል።

የአደጋ ሥጋት  

የጎፋ ዞን መስተዳድር እንዳስታወቀው አሁንም በመሬት ናዳ የተቀበሩ ተጨማሪ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራ እንደቀጠለ ይገኛል።  ያም ሆኖ አካባቢው ለተሽከርካሪ አመቺ ያለመሆን ፍለጋውን አዳጋች እንዳደረገው ነው የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ካሣሁን ዓባይነህ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት።

በአሁን ወቅት እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተያይዞ በሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ አደጋ እንዳይደርስ የጥንቃቄ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል። ሥጋት ባለባቸው ቦታዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በወረዳ ባለሙያዎች አማካኝነት ከአካባቢው እንዲወጡ የማድረግ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም የመምሪያው ሀላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ ገልጸዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበርካቶችን ሕይወት በቀጠፈው የመሬት መንሸራተት አደጋየተለያዩ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ሀዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን በአደጋው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የባንክ ሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ ይፋ ተደርጓል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW