1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎፋው የመሬት ናዳ፤የዐቢይና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይት፤የህወሓትና የፌደራል መንግሥቱ ውዝግብ

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2016

«ሙያዊ እገዛ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ያስፈልጋል አብዛኛው የተጎዳው፣ ሰው ለመርዳት ባደረገው ጥረት በመሆኑ በአደጋ መከላከል በሰለጠኑ ባለሙያዎች ሊታገዙ ይገባል»የሚል ሀሳባቸውን ያካፈሉት ተመስገን ታደሰ ናቸው። ሶሊያና «ነፍሳቸውን ይማርልን! የተረፉት ደግሞ ቤታቸው ፈርሶ በረሀብ እንዳያልቁ የቻልነውን እናግዛቸው ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

Äthiopien Rettungseinsatz und humanitäre Hilfe in der Gofa-Zone
ምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department

የጎፋ ዞኑ ዘግናኝ የመሬት ናዳ፤የዐቢይና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት፣ የህወሓት አመራሮችና የፌደራል መንግሥቱ ውዝግብ

This browser does not support the audio element.

የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ዘግናኝ የመሬት ናዳ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ያካሄዱት ውይይት እንዲሁም የህወሓት አመራሮች እና የፌደራል መንግሥቱ ውዝግብ  ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ያስቃኘናል። 
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ ዘግናኝ የመሬት ናዳ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር  እንደሚችል የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጠቅሶ  የተመ የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ በምህጻሩ ኦቻ ትናንት አስታውቋል። እሁድ ሐምሌ 14 እና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት ናዳ እስከትናንት ድረስ 257 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።  የሟቾች ቁጥር ቁጥር ወደ 500 ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስጋትም አላቸው። እነርሱ እንዳሉት ከናዳው ስር በቁፋሮ አስከሬናቸው የወጣው የ226 ሰዎች የቀብር ስነ ስርዓት ተካሂዷል። የተጨማሪ 20 ሰዎች አስከሬን ደግሞ እየተፈለገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ሌሎች የጠፉ ሰዎች ፍለጋም ዛሬም ለአምስተኛ ቀን ቀጥሏል።  «በጎፋ ወረዳው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ግዜ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።»

በዚህ ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ እግዙአብሔር የሟቾችን ነፍስ እንዲምር የተማጸኑና ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኙ ናቸው። ዘመነ ብርሀን «ያሳዝናል ያማል መሪር ነዉ ሀዘኑ»ሲሉ ንጉሴ ፈንታ  «ኡፍ እንዴት ያለ የአደጋ መከራ ነው»በማለት ክብደቱን ለመግለጽ ሞክረዋል።መርዕድ መንገሻ አደጋውን «ልብ ሰባሪ ክስተት» ብለውታል። « እግዚአብሔር አባቴ ሆይ ይቅር በለን፤ ከመጣብን መዓት ሰውረን ፤ለሞቱትም ነፍሳቸውን ይማር፤ ልባችን ተሰብሯል» የሚለው ደግሞ የሚሚ ሙሉነህ መልዕክት ነው። 
አደጋው የደረሰበት የገዜ ጎፋ ወረዳ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማስረሻ ማንአየ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ከአደጋው ጋር በተያያዘ ከሁለት ሺህ ሦስት መቶ በላይ ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።ከዚህ በመነሳት ኑረዲን አማን «ለወገን ደራሽ ወገን ነው!!! ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ሲሉ ለተጎዱት  ድጋፍ እንዲሰጥ አሳስበዋል። 

በጎፋ ዞኑ የመሬት ናዳ የሞተ ሰው አስከሬን ሲጓጓዝምስል Gofa Zone Government Communication Affairs Department


«ሙያዊ እገዛ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ያስፈልጋል አብዛኛው የተጎዳው፣ ሰው ለመርዳት ባደረገው ጥረት በመሆኑ በአደጋ መከላከል በሰለጠኑ ባለሙያዎች ሊታገዙ ይገባል!!! »የሚል ሀሳባቸውን ያካፈሉት ደግሞ ተመስገን ታደሰ ናቸው። ሶሊያና  «ነፍሳቸውን ይማርልን! የተረፉት ደግሞ ቤታቸው ፈርሶ በረሀብ እንዳያልቁ የቻልነውን እናግዛቸው ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።  ነጻነት ኡርጌሳ «አምላኬ ሆይ ፍጥረትህ ነን ይቅር በለን» ሲሉ እግዚአብሔርን ተማጽነዋል። «ዝምታ የጎዳኝ ሰው» በሚል የፌስቡክ ስም የተጻፈ አስተያየት ደግሞ  «ነብስ ይማር ወገናችን ጋሞ ፣ፈጣሪን የሚፈራ የታፈረ ፣እንቁ ህዝብ ፣የእውነት ምሳሌ፣ ሀቀኛ፣ ክቡር ፣አባቶችን የሚያከብር ፣የሀገር ባለውለታ ህዝብ ይሄ ሲደርስበት ሰለ እውነት ያማል ውዶቼ እሱ በቃል ኪዳኑ ይጎብኛችው መፅናናቱን ያድላችው ያለፉትንም ነፍሳቸው በአጸደ ገነት ያኑርልን ብለዋል 

በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጣ ፈንታ
ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያካሄዱት ውይይት ነው። ዐቢይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የፀጥታ፣ የሕገ መንግሥት፣ የኢኮኖሚ እና ሌሎች ጉዳዮች መነሳታቸውን ተሳታፊዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። አስቸኳይ ውይይት እና ድርድር እንዲጀመር የሚሉ ሀሳቦች፣ ለታጣቂዎች ግልጽ ጥሪ እንዲደረግና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚሉ ጥያቄዎችም መቅረባቸውንም ገልፀዋል።  የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡ የተባሉ  እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ የሚጠይቁ ሀሳቦችም ተነስተዋል ተብሏል። ስለውይይቱ በፌስቡክ አስተያየት ከሰጡት አንዱ ከፍያለው አወቀ ናቸው።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.


«ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መሞከር ጥሩ ነው።»ሲሉ ሀሳባቸውን የጀመሩት ከፍያለው ፣የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ነው ከሠፈር ወጥቶ ሀገር ሀገር ሸቶ፣ ስለሀገር የመነጋገር ሞራል ያለው? ሲሉ ጠይቀዋል።መሠረታዊ ያሉትን ችግርም ጠቁመዋል።«  መሠረታዊ ችግሩ በአንድ ላይ ተደራጅተው መታገል ሲኖርባቸው በአካባቢ ተደራጅተው ሕዝባቸው ከማናቆር የተሻለ ምን ሠርተው ነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቢወያዩ ባይወያዩ ለይስሙላ እንጂ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተነጋግረው ተፅእኖ ፈጥረው ለወጥ ይመጣል ብዬ ተስፈ አላደርግም ።መንግስትም ምነም የማድረግ አቅም እንደሌላቸው ስለሚያውቅ አውርተው እንዲሄድ ይፈቅድላቸዋል።» ሲሉ ከፍያለው ሃሳባቸውን ደድመዋል ።

 ዘብይደር መቻ ለከፍያለው አስተያየት በሰጡት መልስ « መሪው ፓርቲ መች ከሰፈር ወጥቶ ያውጣቸው ሲሉ ፣ ዘብይደር በምላሹ« ከእሱ የተሻለ ሆነው መገኘት ነበረባቸው አንሰው መገኘታቸው ነው ፣ከአጃቢነት ቢወጡ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። «ወይ አገሬ ኢትዮጵያ» በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት «ጠንከር ያለ ጥያቄ የጠየቁትማ አሁን የትእንዳሉ አይተናል ። መጀመሪያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መች ይፈለግና» ይላል።«እኔ በበኩሌ የማውቀው የፐርቲዎች ስም ዝርዝር እንጂ በስራ ላይ መሆነቸውን አላውቅም ሲጀመር ሀገርቤት ውስጥ ይሁኑ ከሀገር ውጭ አልገባኝም ያሉት ደግሞ አህመድ ሁሴን ናቸው ።
«ህዝብ የሚያቀው ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፤ተለጣፊ እንጂ ።» ይልላ ኩን በሚል የፌስቡክ ስም የተጻፈ አስተያየት ። ታምራት ወልደ ሚካኤል ደግሞ «ሁሉም የብልፅግና ቅርንጫፎች ናቸው» ሲሉ እንድሪስ መኮንን ደግሞ አጭር አስተያየት ሰጥተዋል፤«ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ የለም» የሚል 
በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች ውስጥ የህወሓት አመራሮች እና የፌደራል መንግሥቱ ውዝግብ  ይገኝበታል። በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ

ህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ህወሓት ሕጋዊነቱ ከምርጫ ቦርድ ተሰርዞ ቆይቷል። ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ደግሞ ወደ ሕጋዊነት እንዲመለስ በተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ይሁንታ አግኝቷል። የህወሓትን ሕጋዊ አካልነት የማስመለስ ሂደት ባልተጠናቀቀበት በአሁኑ ወቅት ጉባኤ ለማካሄድ መታቀዱ በህወሓት መሪዎች መካከል ውዝግብ አስነስቷል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሳምንት ከተቃወሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ህወሓት ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት በሕጋዊ መንገድ መመዝገብ እንዳለበት አሳስበዋል። ያ ካልሆነ ግን «ተመልሰን ወደ ጦርነት እንገባለን» ሲሉም ተናግረዋል።

የህወሓት አርማ

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ማሳቢያ ቢሰጡም፤ ሕወሓት 14ኛውን ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ዝርዝር መርሃ ግብሮችን አውጥቷል። ስለ ውዝግቡና ምልልሱ  ዶቼቬለ ያወያያቸው የፌስቡክ ተከታዮች በርካታ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ከመካከላቸው ጽንፍ የያዙትንና ዘለፋና ዛቻዎችን ያካተቱን ወደ ጎን በመተው ሌሎቹን ስንቃኝ የሮቤል ታንቱን አስተያየት እናገኛለን። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስርዓት ማስከበር አልቻለም አሉ

«በጦርነት ብዙ መከራን አሳልፈናል። ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ነበረ በተለይ ደግሞ የትግራይ፥ የአማራ እና የአፋር ክልል ህብረተሰብ። ካለፈው ጦርነት መች አገገምን እና ነው ሌላ ጦርነት ውስጥ የምንገባው? ህወሀትም ሆነ ብልፅግና ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። በድሃ ልጅ ህይወት ቁማር መጫወት ምን ያህል ልብ ይሰብራል? ሲሉ መዘዙን ጭምር በመግለፅ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል። ተመስገን አልየ «ሰላም 100% ሰለምን ብቻ ነው የሚያስፈልገን»በማለት ሀሳባቸው በአጭሩ ሲገልጹ ሰይድ አል ሀበሻ ደግሞ «ፀብ የለም ህውሀት እና ብልፅግና ተጋብተዋል።መውለድ እና መክበዳቸውን አላህ ቢያቅም ይሄ ውዝግቡ ግን ትኩረት ለመሳብ ነው።አሁን የፍቅራቸው ምልክት የኤርትራ ኩርፊያ እና ማዕቀብ ነው።»በማለት ግምታቸውን በፌስቡክ አስፍረዋል። ክብረበ ገብሩ «አስተውሉ ችግሮቻችሁን በውይይት ብቻ ፍቱ!!!» በማለት መክረዋል። 

ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW