1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎፋ ሕዝብ ለቅሶ የኢትዮጵያ ሐዘን

Eshete Bekele
ሰኞ፣ ሐምሌ 22 2016

በጎፋ የመሬት መንሸራተት የኢትዮጵያ መንግሥት 231 የአካባቢው ነዋሪዎች 260 ሰዎች እንደሞቱ ይገልጻሉ። በርካቶች የሟቾች ትክክለኛ ቁጥር ተድበስብሷል የሚል ሥጋት አላቸው። አደጋው “ማምረት የሚችሉትን” ሕይወት ነጥቆ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞችን ያለ ረዳት ያስቀረ ነው። አስከሬን ፈልጎ ማንነቱን መለየት በአካባቢው ነዋሪዎች ጫንቃ ወድቋል።

በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ቤተቦቻቸውን አጥተው የሚያለቅሱ እናት
በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የአካባቢው ነዋሪዎች ከ260 በላይ አስከሬኖች ተገኝተው ሥርዓተ ቀብራቸው እንደተፈጸመ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

ማሕደረ ዜና፦ የጎፋ ሕዝብ ለቅሶ የኢትዮጵያ ሐዘን

This browser does not support the audio element.

ትላንት እሁድ ከትንሹ ልጅ ቤት ለቅሶ ነበር። የልጁ አያት ለቅሶ የተቀመጡት ለቀናት የተዘጋ ቤት ከፍተው ነው። ከሳውላ ገስግሰው የመሬት መንሸራተት ያመሳቀላት ቀበሌ የደረሱት አቶ ደጉ ይስሀቅ “ለቅሶ ለመድረስ ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች አሉ። አባት እና እናት፣ ቤተሰብ አልቆ ብቻውን የቀረውን፣ በሩ ላይ የተቀመጠውን ልጅ ተሸክመው እያለቀሱ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨው የሕጻኑ ምስል አደጋው ያስከተለውን ሰብአዊ ቀውስ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በዚያ ምስል የልጁ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት በር በቁልፍ ተከርችሞ ይታያል። ጠይሙ ትንሽ ልጅ በሩ ላይ ተቀምጧል። ግራ እጁን ከግራ እግሩ ላይ ጣል አድርጎታል። ቀኝ እጁ ከቀኝ ጭኑ አካባቢ ሰብሰብ ብላ ትታያለች። ባዶ እግሩን ነው። አቶ ደጉ እንደሚሉት አራት ወይም አምስት ዓመት ይሆነዋል።

ፊቱ ላይ አንዳች ስሜት አለ። እንዲህ በቀላሉ ሊነበብ የማይችል። ልጁን የማሳደግ ኃላፊነት በአያቱ ትከሻ ወድቋል። በትንሹ ልጅ መኖሪያ ቤት ለቅሶ ለመድረስ ጎራ ያሉት የ50 ዓመቱ ቦረና ቦኖ “አቅም የሌላቸው ናቸው የቀሩት። በዚያ ቦታ በይድረስ ጥሪ የሔዱት አቅም ያላቸው፤ ማምረት የሚችሉ፤ ጉልበት ያላቸው ናቸው የተበሉት። አሁን እዚያ አካባቢ የቀሩት አቅመ ደካማ አዛውንቶች ናቸው፤ ሕጻናት ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የዛሬ ሣምንት እሁድ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ኃይለኛ ዝናብ ጥሎ ነበር። አቶ ቦረና ተወልደው ያደጉበት ቀዬ በመጀመሪያው የመሬት መንሸራተት የተመታው ሐምሌ 14 ቀን 2016 እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ነው።  በማግሥቱ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን ከቀኑ አራት ሰዓት ግድም ሁለተኛው ተከተለ።

ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰቱ መንታ የመሬት መንቀጥቀጦች ሕይወታቸውን አጥተው አስከሬኖቻቸው የተገኙ ሰዎች ሥርዓተ ቀብር በመንደራቸው ተፈጽሟል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የቀበሌው ሦስት ቤተሰቦች በሙሉ “ናዳ በላቸው፤ ቶሎ ድረሱ” ብለው የቀበሌው ሊቀ-መንበር ጥሩምባ አስነፉ። አቅም ያለው በተለይ ወጣቱ ሰዎቹን ለማትረፍ ተመመ። “የሞቱትን ማውጣት ሲጀምሩ ከኋላ ናዳ መጣና እነሱም ጠርጎ ወደፊት ይዞ ገባ” ይላሉ አቶ ቦረና የሆነውን መለስ ብለው ሲያስታውሱ።

“እኔም ቤተሰቦቼ እዚያ ነበሩ” የሚሉት አቶ ቦረና ከቦታው ሲደርሱ ሞት ነግሶ ጠበቃቸው። “ከእኛ ቀድመው ከቡልቂ ከተማ የመጡ ፖሊሶች ነበሩ። ከፖሊሶችም ሞቱ። የመንግሥት ሠራተኞች ነበሩ ቤተሰብ ያላቸው እነሱም ገቡ ሞቱ”  ሲሉ የሆነውን ያስረዳሉ።

ታላቅ ወንድማቸው እና ያስተማሯቸው የእህቶቻቸው ልጆች መሞታቸውን ሲረዱ አቶ ቦረና ቡኖ ራሳቸውን ስተው እንደነበር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የ50 ዓመቱ ጎልማሳ እንደሚሉት መረጋጋት የጀመሩት አስከሬን ሲገኝ ነው። አቶ ቦረና በአደጋው ምክንያት 18 ቤተሰቦቻቸውን አጥተዋል።

የመጀመሪያው የመሬት መንሸራተት የቀበራቸውን ሰዎች ለማዳን በተሰበሰበው ሰው ብዛት ምክንያት ሁለተኛው ያደረሰው ጉዳት የከፋ ነበር። ከተደረመሰው ናዳ ራሳቸውን እናታቸውን፣ አባታቸውን እና ሁለት ልጆቻቸውን መታደግ ከቻሉ ጥቂት ሰዎች አንዱ የዳዊት ኦቦሌ ናቸው።

በለቅሶ ብዛት ድምጻቸው የጎረነነው እህታቸው ጸጋነሽ ኦቦሌ በወንድማቸው ብርታት ሕይወታቸው ቢተርፍም እንደ አቶ ዳዊት ግን እድለኛ አይደሉም። “ልጆቼን ጨምሮ ከብዙ ሰዎች ጋር በተንሸራተተው ጭቃ ተውጬ ነበር። ቆፍረው አወጡኝ። ነገር ግን አራት ልጆቼ ሞተው በጭቃ ተቀብረው ቀርተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

መንትዮቹ የመሬት መንሸራተቶች በአብዛኛው የአምራቹን ወጣት ሕይወት ነጥቆ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞችን ያለ ረዳት እንዳስቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የ33 ዓመቱ ሰለሞን ሶማ እንደሚለው ሰባት የወንድሙ እና የአጎቱ ልጆችን ጨምሮ አስራ ሦስት የቤተሰብ አባላቱን ተነጥቋል። ከሟቾቹ መካከል የአስራ ሁለቱ አስከሬን ቢገኝም ለቀናት ጭቃ የቆፈረው ሰለሞን ባለፈው ሣምንት እህቱን እየፈለገ ነበር።

“የወደቀ አስከሬን ተጨማልቆ ፊቱን መለየት” ከባድ እንደነበር የሚናገረው ሰለሞን “በጀሪካን ውኃ ይዘን እየዞርን ልክ አስከሬኑን እንዳወጣንው ውኃ ፊቱ ላይ እየጨመርን” ለመለየት እንሞክር ነበር በማለት ፈታኙን ኃላፊነት ያስረዳል። “ፊቱ አልታወቅ ሲል በድንጋይ፣ ሲበላሽ ደግሞ ልብሱን አጥበን እያወጣን፣ የለበሰውን እያየን፣ አንዳንዱ ከነጭራሹ አልታወቅ ሲል እግር ጥፍራቸውን እያየን በብዙ መከራ አስከሬን ለይተን እያወጣን ነበር” ሲል ተናግሯል።

አስከሬን ሲገኝ ማንነቱን ለይቶ ለቤተሰብ ማስረከብ እንደ ኢያሱ ዙማዩንጋ የመሳሰሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ኃላፊነት ሆኖ ታይቷል። “መጀመሪያ ቀን የወጡ ሰዎች አካላቸው” ሳይፈርስ ይገኝ እንደነበር ኢያሱ ተናግረዋል። እንደ አቶ ኢያሱ የመሰሉ ሰዎች የሟቾች አስከሬን መለየት ስለሚቸገሩ ቤተሰቦች ይጠራሉ። አቶ ኢያሱ “አስከሬኑን ካወጣን በኋላ የማን ቤተሰብ ነው? የማን ልጅ ነው? የማን አባት ነው? የማን እናት ናት ተብሎ ነው የሚለየው” ሲሉ ተናግረዋል።

አደጋው ከደረሰ በኋላ የነበረው የሕይወት አድን ጥረትም ሆነ አስከሬን ፍለጋ በአካባቢው ነዋሪዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ነበር። ወንዶች ሱሪያቸውን ሰብሰብ አድርገው ጥቁሩን አፈር ይቆፍራሉ። ከአነስተኛ ዶማ እና መኮትኮቻ መሰል ዕቃዎች በቀር ይኸ ነው የሚባል መሣሪያ በእጃቸው አልነበረም።

አካባቢው “ማሽን መግባት የማይችልበት ቦታ ነው። ቁልቁለት ነው” የሚሉት አቶ ቦረና የአፈሩ እርጥበት እና የመንገድ እጦት ችግር መሆናቸውን ገልጸዋል። የጎፋ ዞን እና የገዜ ጎፋ ወረዳ ለፍለጋው የሚያግዝ ማሽን ለማስገባት ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር ቀርቶ “ማሽኑ ወደ ኋላ ተመልሷል” ብለዋል።

የመሬት መንሸራተት የተከሰተበት አካባቢ ደፋታማ ከመሆኑ ባሻገር የመንገድ እጦት አስከሬን ፍለጋውን የሚያግዙ ማሽኖች ወደ ለማቅረብ ፈተና ሆኗል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

“ወደ 260 አስከሬን ቀድሞ ተቀብሯል። ዛሬም እየተቆፈረ ነው። ነገም ይቆፈራል” ሲሉ አቶ ቦረና ተናግረዋል። ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለፈው ቅዳሜ በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች ውስጥ “መለየት የተቻለው የ231 ወገኖችን አስከሬን” እንደሆነ አስታውቋል። በአደጋው 257 ሰዎች እንደሞቱ የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለፈው ሣምንት ቁጥሩ እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ገልጾ ነበር።

ዶይቼ ቬለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የጎፋ ዞን እና የገዜ ጎፋ ወረዳ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አደጋው የደረሰበትን ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባለፈው ቅዳሜ ጎብኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዘወትሯቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሐዘናቸውን የገለጹት አደጋው ከደረሰ ከአንድ ቀን ገደማ በኋላ ነው።

በብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ መሠረት 487 ሰዎች በአራት መጠለያ ጣቢያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት 5,600 ተጋላጭ ሰዎች ከአካባቢው ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዘዋወሩ ጠቁሟል።

“አስከሬኖችን የሚለዩ ሰዎች አሉ፣ የተረፉ ሕጻናትን፣ አዛውንቶችን መረጃ እየተሰበሰበ ነው” የሚሉት አቶ ደጉ “የአካባቢው መንግሥት ሌላ ሌላ ጠረንም እያመጣ ስለሆነ እንዳይፈለግ” የሚል ውሳኔ ላይ ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል።

ይሁንና “የእኔ ቤተሰብ የለም እኮ፣ አባቴ አልወጣም፣ ቤተሰቦቼ አልወጡም” እያሉ የሚያለቅሱ በመብዛታቸው ፍለጋው መቀጠሉን አስረድተዋል። አቶ ደጉ “ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እሮብ ዕለት በሰጠው [አቅጣጫ] መሰረት የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል እና የፌድራል ግብረ ኃይል እዚያው ተመድቦ ነው ያሉት” ሲሉ አክለዋል።

ቤተሰባቸውን ያጡ ሁሉ ግን እንዲህ በቀላሉ አስከሬን ማግኘት አልተቻላቸውም። ሣምንቱን ሙሉ የታዩ ምስሎች የጎፋ ሰዎች የገቡበትን ሰቆቃ የሚያሳዩ ነበሩ። ከጭንቅላታቸው ጥቁር ሻሽ ጣል ያደረጉ አንዲት እናት ከመሬት ሊያነሷቸው የሞከሩ ሰዎችን አስቸግረው እየተዝለፈለፉ ወደተቀመጡበት ይመለሳሉ።

በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን እና ጎረቤቶቻቸውን ያጡ ግፋ ሲልም አስከሬን ማግኘት ያልቻሉ የጎፋ ሰዎች ሐዘን እጅግ በርትቶ ታይቷል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

ሌላዋ እናት እጃቸውን ወደ ሰማይ ሰቅለው በእግራቸው ጢብ ጢብ እያሉ ለቅሶውን ተያይዘውታል። ራሱ ላይ ጨርቅ ጣል ያደረገ ወጣት ለያዥ ለገናዥ አስቸግሯል። እምባው ከፊቱ ላይ ይፈሳል።

አብዛኞቹ የሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ማግኘት ባለመቻላቸው ሐዘን የበረታባቸው ናቸው። አስከሬን አግኝተው የቀበሩ በአንጻሩ ዕድለኛ ይባላሉ። ከአምስት ቀናት በኋላ ባለቤቱን ያገኘው ከተማ ቀልስዬ በጣም ደስ ብሎታል።

ከተማ “እሷ ስለተገኘች በጣም ነው ደስ የሚለኝ” ሲል ይናገራል። “በጣም አልቅሼ ነበርኩ እና በጣም ፈልጌ ነበርኩ” የሚለው ከተማ የባለቤቱን አስከሬን የሚያገኝ አልመሰለውም ነበር። “በጭቃ ውስጥ፣ በናዳ ውስጥ በእጅም፣ በዶማም፣ በአካፋም ፈልገን አጥቼ ነበርኩ” የሚለው ከተማ የባለቤቱን አስከሬን አግኝቶ ሲቀብር “እግዚዓብሔር በእጄ አሳልፎ ስለሰጠኝ ደስታ ይሰማኛል” እያለ ያመሰግናል።

የገዜ ጎፋ ወረዳ ቦሎቄ፣ ቡና እና እንሰት የመሳሰሉ ሰብሎች የሚመረትበት ደጋማ አካባቢ ነው። የወረዳው ነዋሪዎች የመሬት መንሸራተት ገጥሟቸው እንደማያውቅ ቢናገሩም አካባቢው ሥጋት እንደነበረበት ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። “ጉዳቱ ከፍተኛ ነው” የሚሉት አቶ ቦረና “እግዚዓብሔር በኃይሉ ካጽናናን ነው እንጂ እኛ እጅግ ነው የተሰበርንው” ሲሉ ይናገራሉ።

“የሚፈናቀሉ ብዙ ሰዎች አሉ። መሬቱ እየተሰነጣጠቀ ያለበት ሁኔታ አለ” የሚሉት የ50 ዓመቱ ጎልማሳ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ መጠለያዎች፣ የሐይማኖት እና የጤና ተቋማት መወሰዳቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። “ምግብ፣ ቤት፣ ውኃ፣ ትምህርት ቤት እና ጤና ተቋም ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ቦረና “እነዚህ ቢሟሉ ሰው ይረጋጋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ባለፈው ሣምንት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ የተከሰተ የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ የአስራ አንድ ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል። 

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ እዬዬ ሲሉ የሰነበቱ ብዙ ናቸው። ለቅሶው የሀገር ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሦስት ቀናት ያወጀው ብሔራዊ ሐዘን ዛሬ ያበቃል። የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ያላገኙ ግን ዛሬም ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW