1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎፋ ነዋሪዎች የምግብ ርዳታ ጥያቄ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 20 2015

በጎፋ ዞን በድርቅ የተነሳ ለበረታ የምግብ እጦት ከተዳረጉት መካከል በዛላ ወረዳ የገልማ እና የዲሳ ቀበሌ ነዋሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የቀበሌያቱ ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለፉት አራት ዓመታት ያተስተካከለ የዝናብ ሁኔታ አለመኖር በእርሻ ሥራቸው ላይ ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል፡፡

Äthiopien Auswirkungen der Dürre auf die Landwirtschaft in der Zone Gofa
ምስል Gofa Zone government communication

የምግብ እጥረት በጎፋ ዞን

This browser does not support the audio element.


አረንጓዴና ምርታማ አካባቢ ተደርጎ በሚቆጠረው የደቡብ ክልል የድርቅ ክስተትም ሆነ የረሀብ አደጋ መስማት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በምግብ ምርት ራሱን የቻለ ተደርጎ የሚቆጠረው ክልሉ አሁን ላይ የእህል እርዳታ ከሚያማትሩ አካባቢዎች ተርታ እየተሰለፈ ይገኛል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በክልሉ በተከሰተው የዝናብ መቆራረጥ ከጎዳቸው መካከል በጎፋ ዞን የሚገኙት ሶስት ወረዳዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዞኑ በዛላ ፣ በኡባ ደብረፀሐይና በደምባ ጎፋ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶአደሮች ባለፉት አራት ዓመታት ዝናብ ባለመጣሉ አሁን ላይ ለከፍተኛ የምግብ ችግር መዳረጋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑወቅት አነኝሁ ወረዳዎች ከ155 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያሥፈልጋቸው የጎፋ ዞኑ መስተዳድር ባለሥልጣናት ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል፡፡  የገልማ እና የዲሳ ቀበሌ ነዋሪዎች 

በጎፋ ዞን በድርቅ የተነሳ ለበረታ የምግብ እጦት ከተዳረጉት መካከል በዛላ ወረዳ የገልማ እና የዲሳ ቀበሌ ነዋሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የቀበሌያቱ ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለፉት አራት ዓመታት ያተስተካከለ የዝናብ ሁኔታ አለመኖር በእርሻ ሥራቸው ላይ ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የጤፍ ፣ የማሽላ ፣ የበቆሎና ሌሎች የሥራ ሥር ምርቶችን ሊያገኙ እንዳልቻሉ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ የዲሳ ቀበሌ ነዋሪና የስድስት ልጆች አባት መሆናቸውን የሚናገሩት ትንሳኤ ከበደ ላለፉት አራት ዓመታት በነበረው የተዛባ ዝናብ የተነሳ አሁን ላይ ቤተሰቦቻቸውን መመገብ እንዳልቻሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ አስከአሁን በመንግሥት በኩል አንድ ዙር እርዳታ ብቻ መቅረቡን የጠቀሱት ትንሳኤ ‹‹ ይህ ከቤተሰቤ ቁጥር አንጻር በቂ አይደለም፡፡ አጥረቱን ለመሙላት እኔን ጨምሮ በርካታ የቀበሌው ሰዎች ከእርሻ ሥራችን በመራቅ በጉልበት ሥራ ለመሠማራት ተገድናል ›› ብለዋል፡፡ በዚሁ በዛላ ወረዳ የገልማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑር ዶላ ጌዴቦ በበኩላቸው በቀበሌያቸው እስከአሁን ምንም አይነት እርዳታ አለመቅረቡን ይናገራሉ፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳንድ የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመጠጋት መንደራቸውን ጥለው መሄድ ጀምረዋል የሚሉት ዶላ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በአስቸኳይ ድጋፍ ያድረግልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 
መንግሥት የችግሩን ተጋላጮች እንዴት እየደገፈ ይገኛል ? 
በደቡብ ክልል ባለፈው ዓመት በበልግ ወቅት በተከሰተው የዝናብ መዛባት ምክንያት አሁን ላይ 3 ሚሊዮን 479 ሺህ  የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ ክፍተት መጋለጣቸውን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል ፡፡ አሁን ላይ የምግብ ችግሩ ከበረታባቸው የክልሉ አካባቢዎች በጎፋ ዞን የሚገኙት የዛላ ፣ የኡባ ደብረፀሐይና የደምባ ጎፋ ወረዳዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ ፡፡ የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አብረሃም ዞራ አሁን ባለው ሁኔታ በተጠቀሱት ወረዳዎች ከ155 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያሥፈልጋቸው ለዶቼ ቬለ DW ተናግረዋል፡፡ በአሁኑወቅት ከፌደራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተላከ 4 ሺህ 800 ኩንታል አንዲሁም ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና ከዞኑ ነዋሪዎች የተሰባሰበ  ከ2 ሺህ ኩንታል በላይ  የምግብ እህል ለተረጂዎች መቅረቡን የጠቀሱት አቶ አብረሃም ‹‹ በእርግጥ አስከአሁን የቀረበው ዕርዳታ ከተረጂዎች ቁጥር አንፃር በቂ አይደለም ፡፡ ከፌደራል እየቀረበ ከሚገኘው ድጋፍ በተጨማሪ በደቡብ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩልም ተጨማሪ የምግብ አህሎችን ለማቅረብ የሚያስችል የጨረታ ሂደት እየተከናወነ ይገኛል ፡፡ እንዲሁም የዞኑ መስተዳድር ፣ የረድኤት ድርጅቶች ፣ ንግዱ ማህበረሰብና የዞኑ ተወላጆች ድጋፉ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ምግብ ፍለጋ ሳይንቀሳቀሱ ባሉበት አቅርቦቱን ለማድረስ በቅንጅት በመሥራት ላይ ናቸው ›› ብለዋል ፡፡ 

ጎፋ የደረሰዉ ርዳታ በቂ አይደለምምስል Gofa Zone government communication

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW