1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሩሲያ ጉዞና አንድምታው

ዓርብ፣ መስከረም 16 2018

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በአለም አቀፍ የአቶሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ አቅንተዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፑቲን ጋር ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል የጋራ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ ለማልማት ስምምነቶች ስለመፈረማቸውም ተነግሯል፡፡

 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር   እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲንምስል፦ Sergei Fadeichev/TASS/picture alliance/dpa

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ውይይት በባለሙያ ዓይን

This browser does not support the audio element.


በርካታ የዓለም መሪዎች በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድረጅት ላይ በቆዩበት በሰሞኑ አቢይ ዓለማቀፍ አጀንዳ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን በአለም አቀፍ የአቶሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ አቅንተዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፎረሙ ተሳትፎ ጎን ለጎን የሩሲያ የኃይል ማመንጫ፣ ግብርና፣ የጤና ጥበቃ ልማት እና የመከላከያ ትብብርን የሚያካቲት የተባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳት ፑቲን ውይይት፤ ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል የጋራ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ ለማልማት ስምምነቶች ስለመፈረማቸውም ተነግሯል፡፡
ለመሆኑ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በመቃቃር ላይ ከምትገኘው ሩሲያ ጋር ጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየመሰረተች ያለችው ኢትዮጵያን ሌላው የዲፕሎማሲ ፈተና ውስጥ ያስገባታልን?
ከሰሞኑ የበርካታ አገራት መሪዎች በኒውዮርክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅ ጉባኤ ላይ ስታደሙ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሩሲያ የአቶሚክ ኒኩለር ፎረም ላይ ነበሩ፡፡ በዚህን ወቅትም ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እና የሌሎች አገራት መሪዎች ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይት ስያደርጉ እንደነበር እየተገለጸ ነው።

ብላድሚር ፑቲን፤ የሩሲያ ፕሬዚዳንትምስል፦ Vladimir Smirnov/TASS/picture alliance

የሩሲያ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መረጃ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የኒኩለር ኃይል ለማበልጸግየሚያስችላትን ስምምነት አኑራለች፡፡ በዚህን ወቅትም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን፤ “ጠቅላይ ሚኒስትር እንኳን ወደ ሞስኮ ከልዑክዎ ጋር በደህና መጡ፤ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የአፍሪካ አጋራችን ናት፡፡ በ1898 ጀምሮ በአገራቶቻችን መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተመስርቶ በሂደትም እያደገ ነው፡፡ ግንኙነታችንም እያጠናከርን አንድ ልዑካችን በዚሁ ዓመት መጀመሪያ ኢትዮጵያን ጎብኝቶአት ነበር፡፡ አሁንም ግንኙነታችን እየተጠናከረ በመጣበት ወቅት እንኳን ደህና  መጣችሁ” ሲሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፊናቸው፤ “ክቡር ፕሬዝዳት ላደረጉልን አቀባበልና ስለጋበዙንም እናመሰግናለን፤ በካዛን በብሪክስ ስብሰባ ከተገናኘን ዓመት ሊሆነን ነው፡፡ ተስፋ የማደርገው በቀጣይ ደግሞ በአዲስ አበባ እንደምንገናኝ ነው፡፡ እርረሶ እንዳሉ የረጅም ጊዜ ግንኙነት በታሪክና በሃይማኖት የተሳሰረ ግንኙነት አለን፡፡ አሁንም የጋራ ትብብራችንን ማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ ይህ ጉብኝታችንም ግንኙነታችንን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርልን ነው” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አቶሚክ ኒኩለር ግንባታ ፍላጎት

በዚሁ ወቅትም ሁለቱ መሪዎችን በልዑኮቻቸው በኩል የኒኩለር ፕሮጀክት ግንባታ ስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት ተፈራርመው መቀያየራቸው ነው የተመላከተው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚያስመርቁበት ወቅት በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ዓላማ የምታውለውን የኒኩለር ግንባታ ፕሮጀክት ከሩሲያ ጋር በመተባበር እንደምታስጀምር መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የኒኩለር ሃይል ግንባታን ጨምሮበትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እራሷን እያስተዋወቀች ነው በሚል አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ በተለይም የኒውክለር ፕሮጀክቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንገስት ከሩሲያ ጋር ያለውን ጥብቅ ግንኙነት ያመለከተ ነው ብለዋል፡፡ “በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጣም ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየተቀረጹ ነው” ያሉት ተንታኙ፤ የአፍሪካ ታላቁ አየርማረፊያን ጨምሮ አሁን ደግሞ የኒኩለር ግንባታው ብሎም የቀይ ባህር ፕሮጀክት ውጥን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙዎችን ለማሳመን የሚጥሩባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ልባሉ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ሌላውደግሞ ኢትዮጵያ ባሁን ወቅት ከሩሲያ ጋር ዲፕሎማሲዋን በላቀ ደረጃ እያጠናከረች ያለችው ከኤርትራ ጋር ምናልባትም ግጭት ውስጥ የምትገባ ከሆነ ሩሲያ ከኤርትራ ጎን እንዳትሰለፍ ለመስራትም ይመስላል ነው ያሉት፡፡

ዐብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርምስል፦ Ethiopian PM Office

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲው መንገድ ወዴት?

በቅርቡ ከዓመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የተካረረ የዲፕሎማሲ ሽኩቻ ውስጥ መግባቷ አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳን ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ከበርካታ የምዕራቡ ዓለም ጋር ኢትዮጵያ ያላት ግንኙነት ነባሩን መልኩን የያዘ ብመስልም ኢትዮጵያ ከምስራቁ ዓለም አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍ እያለ የመጣ መስሏል፡፡ እንደ ፖለቲካ ተንታኙ አስተያየት ግንየኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከሁሉም ዓለም ጋር ሚዛናዊ ነው፡፡ “ኢትዮጵ ሁል ጊዜም ሚዛናዊ የሆነ የውጪ ፖሊሲ ነው ያላት፡፡ በደርግ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ይህን መርህ መንገራገጭ ብገጥመውም ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከምዕራቡም ሆነ ከምስራቁ ዓለም ጋር ሚዛናዊ የውች ግንኙነት ምርህን ለመከተል ስትጥር ነው የሚታየው” በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኒኩለር መርሃግብር ግንባታን ጨምሮ ከምስራቁ ዓለም ጋር የሚሰሩበት ሁኔታ እንደ አሜሪካ ባሉ የምዕራቡ ዓለም አገራት እንደስጋት አለመታየቱንም በምልከታቸው ጠቁመዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ አጠቃላይ ውይይት አካሂደናል።ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸውን።ስፍረዋል።ውይይት ከተከሄደባቸው ጉዳዮች መካከል  የኃይል ማመንጫ፣ ግብርና፣ የጤና ጥበቃ ልማት እና የመከላከያ ትብብርን ያካትታሉ ተብሏል።በተለይም ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል ንፁህ ኃይል ለማቅረብ የጋራ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫ ለማልማት ስምምነቶችን በመፈራረም የጋራ ፍላጎቶቻችንን የሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ተማክረናል።ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ፀሀይ ጫኔ

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW