1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የምክር ቤት ማብራሪያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 6 2015

መንግሥት ከሕወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ያደረገው «በኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት ይፈፀም ብሎ ነው» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ስለ ስምምነቱን አጠቃላይ ይዘትና የወደፊት አተገባበር በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ «እየተዋጉ መኖር አይቻልም» ብለዋል።

Äthiopien Addis Abeba MP Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል

This browser does not support the audio element.

መንግሥት ከሕወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ያደረገው «በኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት ይፈፀም ብሎ ነው» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስምምነቱን አጠቃላይ ይዘትና የወደፊት አተገባበር በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ «እየተዋጉ መኖር አይቻልም» ሲሉ የስምምነቱን አስፈላጊነት አስረድተዋል። በኦሮሚያ ክልል የኦነግ ሸኔ ያደርሰዋል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ «ታጥቆ በኃይል የሚገኝ ጥቅም የለም፣ በፖለቲካ ንግግር ብቻ ነው ችግሮች የሚፈቱት» ብለዋል። የወልቃይት ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ይደረጋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁንና የክልሎች ልዩ ኃይሎች የደቀኑት ሥጋት ተጠቅሶ የመንግሥትን አቋምና ዘላቂ መፍትኄ የተጠየቁት ዐቢይ ለጥያቄው ምላሽ ሳይሰጡበት ማለፋቸውም ተገልጧል። የምክር ቤቱን ውይይት የተከታተለው የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ሰለሞን ሙጬ  ወጣዩን ዘገባ ልኮልናል።

308 የምክር ቤት አባላት በተገኙበት የዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቀረቡት 20 ጥያቄዎች ውስጥ ሦስቱ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቀሪዎቹ በገዥው ብልጽግና ፓርቲ አባላት የቀረቡ ናቸው።

ቀዳሚው ጥያቄ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት ሂደቱ፣ አንድምታው እና ፋይዳውን የተመልከተ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ «እየተዋጉ መኖር አይቻልም» ብለዋል።  «ሰላምና ብልጽግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነት ማቆም በእጅጉ ያስፈልጋል። ለሰላማችን ፣ ለብልጽግናችን ስንል ነው ጦርነት ማቆምን ቀዳሚ ምርጫ አድርገን የምንወስደው። የኢትዮጵያን ኅልውና፣ የኢትዮጵያን ልእልና፣ አንድነት የሚገዳደር ነገር ሲፈጠር ግን ያ ነገር በሰላም መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ መፋለም ግዴታ ነው» ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ገቢራዊነቱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ሙሉ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል። «ከድርድር በኋላ ብዙ ጊዜ በመተማመን እጦት እና ቃል የገባነውን ባለመፈፀም ምክንያት ድርድሮች ይበላሻሉ። በዓለም ላይ 154 ድርድሮች የከሸፉት ከተስማሙ በኋላ ቃላቸውን መጠበቅ ባልቻሉ ወገኖች ነው። እኛ አንድ ርምጃ ሄደናል። ተወያይተናል፣ ተስማምተናል፣ ፈርመናል። ቀጥሎ የሚጠበቅብን የገባነውን ቃል በታማኝነት በመፈፀም ሰላሙን ዘላቂ ማድረግ ነው» ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕንጻ ከውጭ ሲታይምስል Solomon Muchie/DW

የወልቃይት ጉዳይ በሕገ መንግሥታዊ መልኩ ይፈታል መባሉ ተነስቶ የተገቢነቱ ጉዳይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባል ጥያቄ ተነስቷን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ «በሰላማዊ መንገድ በስምምነት ይፈታል» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም ወልቃይትን በሚመለከት «በሚወራው እና በሚናፈሰው አሉባልታ መንግሥት እጁ የለበትም» ሲሉ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ አሸባሪ ብሎ የፈረጀው ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን «የትጥቅ ምንጩ ምንድን ነው? ቡድኑ የደቀነውን ችግር መፍቻ ስልት ኃይል ወይስ ስምምነት?» የሚል ጥያቄም ቀርቦ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

«በመጀመርያ በሽብር የሚገኝ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ እና ክብር የለም። በሽብር መንገድ ዘላቂ ጥቅም ማምጣት አይቻልም። ሸኔ እንኳን ለእኛ ለሚጋልቡትም የማይጨበጥ ሆኗል። ለሸኔም ሆና ለሌሎች ታጥቆ በኃይል የሚገኝ ጥቅም የለም። በንግግር ብቻ መሆን አለበት የሚል አቋም ነው ያለን» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልሰዋል።

የጦርነቱ ተጎጅዎችን በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ መደገፍ ፣ መልሶ መገንባት፣ ተፈናቃዮችን መመለስ ተጠናክሮ የሚከናወን የቀጣይ ሥራ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት በ 7.5 በመቶ እድገት እንደሚኖረውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። መሬት በደላሎች እና ሌቦች ሲሉ በጠሯቸው አካላት እጅ ላይ መውደቁንና ጉዳዩ የምክክር ኮሚሽኑ አንዱ መወያያ እንደሚሆን ተመላክተዋል።

«የትግራይ ሕዝብ ከፍላጎቱና እሳቤው ውጪ ችግር ላይ ሲወድቅ፣ ሲራብና ሲቸገር እኛ ልንደርስበት ይገባል» ያሉት ዐቢይ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ኑባሬ ብልሽት አለ፣ ጎጠኝነትና ነገሮችን ሁሉ ፓለቲካዊ ትርጓሜ የመስጠት ችግር እንደ ባህል እየታየ መሆኑ አሳሳቢ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

የዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት ችግር ገጥሞታል ፣ በተለይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ዜጎች እንዳይገቡ ይደረጋል። የዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ምንድን ነው ? የሚል ጥያቄም ቀርቦ ነበር። ችግሩ በወቅቱ የተከሰተው የአዲስ አበባን የፀጥታ ሥጋት ለመጠበቅ ሲባል የተወሰደ ርምጃ ነበር ብለዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የክልል ልዩ ኃይሎች በአንድ የመከላከያ የፀጥታ መዋቅር ሥር ገብተው እንዲሠሩ መንግስት ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡበትም።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW