1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚንስትሩ 100 ቀናት እና ተቃዋሚዎች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 5 2010

የኢትዮጵያያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በስልጣን በቆዩባቸዉ የመጀመሪያዎቹ መቶ ቀናት ያከናወኗቸዉ ተግባራት መልካምና ሊበረታቱ የሚገባቸዉ ናቸዉ ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።ያም ሆኖ ግን ነጻ የዲሞክራቲክ ተቋማትን በቋቋምና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ዉይይቶች በማካሄድ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ፓርቲዎቹ አሳስበዋል።

Abiy Ahmed Äthiopien
ምስል picture-alliance/AA

Dr. Abiy Ahmed 100 days in Office. - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 አ/ም  በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ ቃላ መሃላ ከፈፀሙ ትናንት ሀምሌ 4 ቀን 2010 አ/ም እነሆ 100 ቀናት ተቆጥረዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ በእነዚህ ቀናት ዉስጥ ፍቅርና ይቅርታ ላይ ትኩረት አድርገዉ  በሰሯቸዉ ስራዎች በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ድጋፍ እየተቸራቸዉ መሆኑ እየተገለፀ ነዉ።ለዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችና  እንዲሁም በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ በበኩላቸዉ የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የ100 ቀናት የስራ ቆይታን እሳቸዉ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸዉ በፊት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ሁኔታና ስጋት አንጻር ያዩታል።አቶ ጌታነህ እንደሚሉት ከእነዚህ ቀናት በፊት የሀገሪቱ ሁኔታ እጅግ ፈታኝና ህዝባዊ ተቃዉሞ ጎልቶ የወጣበትና በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡበት ወቅት ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ወቅት የመጡ መሪ በመሆናቸዉ እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለስ አንፃር ያከናወኗቸዉ ተግባራት መልካም መሆናቸዉን አብራርተዋል።
  «ሲመጡ ሁለቱን ጥያቄዎች መመለስ ነበረባቸዉ።ከዚያ ዉስጥ የመጀመሪያ ያደረጉት በተለይ የፖለቲካና የህሊና ዕስረኞችን መልቀቃቸዉና ከዚያም አልፎ በዲፕሎማሲ ደረጃ ከሀገር ዉጭ ሄደዉ በተለይ ከጎረቤት ሀገሮች ያሉ እስረኞችን እንዲፈቱ ማድረጋቸዉና ባለፈዉ ሳምንት ከኤርትራ መንግስት ጋር የነበረን መቀራረብ እንደገና ምህዳሩን ለማስፋት የተደረገዉ በአጠቃላይ ስናያቸዉ የሚያረጋጋ ቆይታ ነዉ። ባለፈዉ 100 ቀናት የነበረዉ።እና ዉጤታማ ቆይታ ነዉ።»ብለዋል።
በሀገር ዉስጥም ይሁን በዉጭ የሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ግለሰቦች ወደ ሀገራቸዉ እንዲገቡና በፖለቲካዉ መስክ  በነፃነት እንዲሳተፉ መደረጉ ሌላዉ ጥሩ ጅምር መሆኑንም ገልፀዋል።  ያምሆኖ ግን መሳሪያ ያነሱም ይሁን በሰላማዊ መንገድ ይታገሉ የነበሩ የተቀዋሚ ፓርቲዎች ጋዜጠኞች እንዲሁም ህዝቡ ያነሷቸዉ የነበሩ የነጻነት፤ የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በመጠኑ ቢመለሱም አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ መፍትሄ ያላገኑ ጉዳዮች በመሆናቸዉ በቀጣይ ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ይገባል ሲሉ አቶ ጌታነህ አሳስበዋል።። 
«ያኔ የታሰርንበት የተደበደብንበት  ነገር አብቅቶ ከዚህ በኋላ እኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሌሎችም ለሀገር የሚጠበቅባቸዉን ነገር ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል።ከዚያ በኋላ ተቋማት ፍትሃዊ ነፃ ገለልተኛ መሆን አለባቸዉ።»
የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ እንደሚሉት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ እስረኞችን በመፍታትና የዉጭ ግንኑነትን በማጠናከር ረገድ የሰሯቸዉ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸዉ። ቢሆንም የመንግስት ተቋማትን በማጠናከርና በሀገር ዉስጥ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት ረገድ  የሚቀሩ ነገሮች መኖራቸቸዉን ጠቁመዋል።። 
በእነዚህ መቶ ቀናት አንዳንድ የህዝብ ተሳትፎ ይጠይቁ በነበሩ ዉሳኔዎች ላይም እጥረት መታየቱን ገልጸዋል።ለዚህም በቅርቡ የተጀመረዉን የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት ለአብነት አንስተዋል።
«ለምሳሌ በኢትዮ ኤርትራ ግንኑነት የተደረገዉ ስምምነት ጥሩ ሆኖn ግን ተሳትፎ ይፈልጋል።የፖለቲካ ፓርቲዎች የክልል መንግስታት ተሳትፎ የሚፈልጉ ነገሮች ናቸዉ።አጠቃላይ ጥሩ ነገሮች አሉ።ግን በጥርጣሬ የምናያቸዉ ገና ለመቃወምም ለመደገፍም ጌዜ ያስፈልጋል። የጠቅላይ ሚንስትሩ መንገድ አልጠራም።አለየም ብለን የምናስባቸዉ ጉዳዮች አሉ።»ሲሉ ነዉ የገለፁት። 
እንደ አቶ አብርሃ ገለፃ በእነዚህ መቶ ቀናት ጠቅላይ ሚንስትሩ በአጠቃላይ  አመርቂ ዉጤት ያከናወኑ ቢሆንም  ወደ ብሄራዊ መግባባትና ህዝቡን ወደ አንድነት የሚወስዱ ጉዳዮች ላይ በግልፅ የተቀመጠ አቅጣጫና የተሰራ ስራ አለመኖሩ ግን መሰረታዊ ጉድለት መሆኑን ጨምረዉ አመልክተዋል።

ምስል Getu Temesgen
ምስል DW/M. Sileshi
ምስል Yemane G. Meskel/Minister of Information

«ወደ ግጭት የሚያመሩ ነገሮች የሚቀሩበትን መንገድ ነዉ መስራት የነበረብን።ስርዓት ማበጅት ነበረብን ።ብሄር ብሄረሰቦች እንዳይጋጩ በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዳይኖር በነዚህ ነገሮች ላይ መስራት ሲገባን ዝም ብለን  ላይ ተንሳፈን ሰልፍ ጠራን ድጋፍ አድረገን ተደመርን እያልን ዉስጥ ለዉስጥ ጥላቻ የምንሰብክ ከሆነ ግጭቶች ናቸዉ የሚመጡት።  በህዝቦች መካከል አንድነት ከሌለ ደግሞ የሀገር አንድነት አጠያያቂ ነዉ።»ብለዋል።

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ
 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW