1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ከመገዳደል መገዳደር» ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ አካባቢዎች ስላሉት ግጭቶች በሰጡት ምላሽ የመንግሥታቸው መሻት ሰላም መሆኑን እና ከመከላከል ውጪ በመንግሥት እቅድ የተደረገ ጦርነት ስላለመኖሩ ዘርዝረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ለምክር አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ
ከግራ ወደ ቀኝ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎምስል AP/picture alliance

 

በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት በየክልሉ የሸመቁ ተዋጊዎች ትጥቃቸዉን  እንዲፈቱ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩዛሬ ከ22 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቃዎች በሰጡት  "ከመገዳደል መገዳደር ይሻላል" ብለዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ባለስልጣኖቻቸዉ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ስለሚያደርጉት ድርድር ቀጥታ ማብራሪያ አልሰጡም።ይሁንና መንግሥታቸው አሁንም ፍላጎቱ ሰላም መሆኑን አስታዉቀዋል። 

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት "በርካታ ነገሮች መስመር ይዘዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ "የቀሩ ሥራዎች አሉ" እነዚህ ጉዳዮች በትብብር እና በውይይት ይፈታሉ ፣ ሆኖም "ቀሪ ሥራ ስላለ ካልተዋጋን ካልን ግን ጥፋት ነው ብለዋል። በሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ለሚነሳባቸው ቦታዎች ሕዝበ ውሳኔ አማራጭ ሆኖ መቅረቡንና ሌሎች አማራጮች ከቀረቡ መንግሥታቸው ለመቀብል ዝግጁ መሆናቸውንም ለፖርላማው ገልፀዋል። 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደሌሎች ሀገሮች የቀይ ባህርንም ሆነ በአካባቢው የሚገኙ ወደቦችን በንግድ ሕግ  መሠረት የመጠቀም መብት እንዳላት ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ሲሆን ግን ማንንም ጎረቤት ሀገር የመውረር ፣ አንድም ጥይት የመተኮስ፣ የማንንም ሉዓላዊነት የመንካት ፍላጎት እንደሌለ ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትምስል Solomon Muchie/DW


ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረቡ ጥያቄዎች 

ርዕሠ ብሔር ሣኅለወርቅ ዘውዴከአንድ ወር በፊት የመንግሥትን የአመቱን እቅድ በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ያቀረቡት ማብራርያ ላይ ተንተርሰው 22 የምክር ቤት አባላት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ ፣ የዜጎችን ደህንነት፣ ኢትዮጵያ ከጦርነት ልትላቀቅ ስላልቻለችበት ምክንያት፣ የብሔር እና የሃይማኖት መካረርና የልዩነት አውድ እየሰፋ ስለመምጣቱና መፍትሔው፣ የታጠቁ ኃይሎች በንፁሃን ላይ ስለሚያደርሱት ጥቃት፣ እየታየ ስላለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ስለ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲሁም የወደብ ጥያቄዎች አስፈላጊነትን የተመለከተ ጥያቄዎችን ተጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች ስለሚታዩ ግጭቶች ምን አሉ ? 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ አካባቢዎች ስላሉት ግጭቶች በሰጡት ምላሽ የመንግሥታቸው መሻት ሰላም መሆኑን እና ከመከላከል ውጪ በመንግሥት እቅድ የተደረገ ጦርነት ስላለመኖሩ ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽምስል Solomon Muchie/DW

"ግጭቶች ይታያሉ ።እነዚህ ግጭቶች የእኛ መሻት ሁልጊዜም ሰላም ነው። እስከዛሬ ድረስ ባለፉት አምስት ዓመታት በእኛ መሻት ፣ በእኛ እቅድ አንድም ጦርነት አልትካሄደም። አሁን በሚደረጉ ትግሎች ግራና ቀኝ መንግሥት ማሸነፍ ይከብዳል" በማለት ሁሉም ትጥቅ ያነገቡ አካላት ወደ ሰላም እንዲመለሱ "ከመገዳደል፣ መገዳደር ይሻላል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአማራ ክልል ያለው ጦርነት ስላደረሰው የጉዳት መጠን ምንም ያላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ክልሉን ከመፍረስ ስለመታደጉ ግን ተናግረዋል። በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ከሰሞኑ ውጊያ ስለማየሉ በተለያየ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ቢገልፁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አማራ ውስጥ አንፃራዊ ሰላም በአስቸካይ ጊዜ ድንጋጌው ታግዞ ስለመስፈኑን ተናግረዋል።
"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንፃራዊ ሰላም አምጥቷል። ይህም የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ አደጋ ታድጓል። ነገር ግን የተሟላ ሰላም አልመጣም። ተጨማሪ ውይይት፣ ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል" ብለዋል። 

ስለ ፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር እና ቀጣይ የአማራ እና ትግራይ ግንኙነት ምን ተባለ?

"የፌዴራል መንግስት በትግራይና በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ አንዱ ተደስቶ ሌላኛው አኩርፎ ቀጣይ ግጭት እንዳይፈጠር ሕዝበ ውሳኔን ማዕከል ያደረግ አካሄድ ብንከተል ጠቃሚ ነው ብሎ ያምናል" የሚል ምላሽ የሰጡት ዐቢይ "ሕዝቡን አወያይተናል። የሕዝቡንም ምላሽ እናውቃለን። ነገር ግን ይህ መፍትሓ ብቸኛ ስላልሆነ የአማራና የትግራይ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተወያይተው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መፍትሔአለን ካሉ በደስታ እንቀበላለን" ብለዋል። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተመታ ታንክምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

 የወደብ አስፈላጊነት 

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በጎረቤት ሀገራት ላይ ወረራ የመፈፀም ፍላጎት እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። "ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም" ነገር ግን እኢትዮጵያ በንግድ ሕግ መሠረት ወደብ ማግኘት እንደምትፈልግ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ከ30 አመታት በፊት ሁለት ወደቦቿን ማጣቷ እና አሁን በጅቡቲ ወደብ ብቻ የምትገለገል መሆኑ በአካባቢው አንዳች ችግር ቢከሰት አሳሳቢ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የወደብ ጉዳይ ስለመነሳቱም አብራርተዋል። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሌሌች ጉዳዮችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW