የጠፈር ቴክኖሎጂ ለአፍሪቃ ቅንጦት ነውን?
ረቡዕ፣ መስከረም 21 2018
ስለጠፈር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሲነሳ ብዙዎች ወዲያውኑ የሚያስቡት ስለ ሮኬት ማምጠቅ፣ ስለ ህዋ ምርምር እና ወደ ጨረቃ ወይም ማርስ ስለሚደረጉ የጉዞዎች ነው።በዚህ የተነሳ ቴክኖሎጅው በተለይ በድህነት እና በኋላ ቀርነት ስማቸው ተደጋግሞ ለሚነሳው የአፍሪቃ ሀገራት ቅንጦት ተደርጎ የሚታይበት ጊዜ አለ።ነገር ግን የጠፈር ቴክኖሎጂ ከኛ ርቀው የሚገኙትን ፕላኔቶችን እና የጠፈር ምርምርን ብቻ የሚመለከት አይደለም።የጠፈር ቴክኖሎጂ በምንኖርባት ምድር ላይ የሰዎችን የዕለት ተለዕት ህይወትን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት።ቴክኖሎጂው በተለይም የተለያዩ ማህበራዊ፣አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለሚፈትኗት አፍሪቃ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ይሰጣል። ሌጎስ፣ናይጄሪያ የሚገኘውን የአፍሪካ ኢን ስፔስ የተባለ ተቋም መስራች እና የጠፈር ሳይንቲስቱ ቲሚዳዮ ኦኒሰን የሳተላይት መረጃ የህዝብን ህይወት ያሻሽላል ይላሉ።«ለአፍሪካ መሰረታዊው ነገር ህዋ ወደ ፍፃሜ የሚያደርስ መንገድ መሆኑን መረዳት ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ለህዝባችን ህይወት የተሻለ እንዲሆን ልንጠቀምበት የምንፈልገው ነው። እነዚህ ሰዎች ወደ ጨረቃ መሄድ፣ ወይም ወደ ማርስ መሄድ እንፈልጋለን ብለው አያስቡም-።ያን እያሰቡም።እነሱ እያሰቡ ያሉት በመንደሮቻቸው ላሉ ሰዎች ጥሩ መስተጋብር እንዲኖር ሳተላይት መጠቀም እችላለሁ ነው። የጎርፍ ችግር ገጥሞኛል፣ የድርቅ ጉዳዮች አሉብኝ፣ እርሻዬ ጥሩ ምርት አይሰጥም እና የሳተላይት መረጃን ተጠቅሜ ያንን ለማሻሻል እችላለሁ ነው።»
የጠፈር ቴክኖሎጂ ጥቅሞች
እንደ ባለሙያው አፍሪካ ውስጥ ግብርናን ከማሻሻል ጀምሮ ተግባቦትን እስከማሳደግ የጠፈር ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረጉ መሳሪያዎች ብዙዎቹን የአህጉሪቱን የእድገት ፈተናዎች ለመፍታት ያስችላል።በቀላል አነጋገር የጠፈር ቴክኖሎጂ ቅንጦት ሳይሆን፤ የምግብ ዋስትና እጦት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ደካማ መሠረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት የመሳሰሉ ውስብስብ ችግሮች ላሉባት አፍሪቃ፤ አዳዲስ መፍትሄዎችን የሚሰጡ የልማት እና እድገት መሳሪያ ናቸው።ከዚህ አንፃር የጠፈር ምርምር ለበለጸጉ ሀገራት ብቻ የተወሰነ ነገር ቢመስልም ለአፍሪካ እድገት በጣም አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል።- ግብርና እና የምግብ ዋስትና ከማሳደግ አንፃር ፤ሳተላይቶች የሰብል ሁኔታን መከታተል፣ ድርቅን መለየት እና የዝናብ ሁኔታን መከታተል ስለሚችሉ፤በዚህ ክትትል የሚያቀርቡት መረጃ መሰረት፤ ገበሬዎች ስለሚዘሩት የሰብል አይነት እና ስለሚዘሩበት ጊዜ ፣ስለሚጠቀሙት የግብርና ግብዓት የተሻለ ውሳኔ እንዲወስኑ ይረዳል። በአየር ንብረት ለውጥ በተጠቁ ክልሎች የሳተላይት መረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቃሚ መሳሪያ ነው።
ቴክኖሎጂው በአደጋ ጊዜ ምላሽም ቁልፍ ሚና ይጫወታል
በጎርፍ፣ ሰደድ እሳት፣ ወይም አውሎ ንፋስ፣ በተከሰተ ጊዜ፤ በመሬት ምልከታ ሳተላይቶች አማካኝነት የእነዚህን ክስተቶች የመጀመሪያ ምልክቶች ለይቶ በማወቅ፤ መንግስታት ወቅታዊ ምላሾችን እንዲሰጡ ይረዳል።የሳተላይት ምስሎች ጉዳትን በመገምገም የአደጋ ጊዜ ቡድኖች የማዳን ጥረቶችን ያግዛሉ።ይህም የበለጠ የሰው ህይወትን ለመታደግ ያስችላል።በተጨማሪም በእጽዋት፣ በውሃ እና በሙቀት ላይ የሚታዩ ለውጦችን በመከታተል የአየር ንብረት ቁጥጥርን ስራን ይደግፋሉ ።
ለከተማ ንድፍ እና መሠረተ ልማት
በአፍሪካ አስተማማኝ የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነት ውስን በሆነባቸው አካባቢዎች ጠፈር ላይ የተመሰረቱ የመገናኛ ሳተላይቶች የገጠር ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒኮችን እና የንግድ ተቋማትን በማገናኘት የዲጂታል ክፍተትን በመሙላት ላይ ናቸው።ይህም መሠረተ ልማቶች በማይደርሱባቸው ቦታዎች የትምህርት፣ የጤና እንክብካቤ እና የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶችን ለመስጠት ያስችላል።
የከተማ ንድፍ እና መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘም፤የሳተላይት ምስሎች መንግስታት እና የከተማ ንድፍን የሚያወጡ ባለሙያዎች ስለ መንገድ፣ መኖሪያ ቤት፣ የውሃ አስተዳደር እና የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እና ተግባራዊ ስራ እንዲሰሩ ይረዳል። በተጨማሪም የደን መጨፍጨፍ፣ ህገወጥ ማዕድን ማውጣት እና የአካባቢ መራቆትን ለመቆጣጠር ያግዛል።
ያም ሆኖ በአፍሪካ ጥቅም ላይ የሚውለው አብዛኛው የሳተላይት መረጃ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ ወይም በእስያ ከሚገኙ ኤጀንሲዎች የተወሰደ ነው። ነገር ግን የአፍሪካ አገሮች ከምድር ወገብ አካባቢ የሚገኙ በመሆናቸው የአውሮፓ እና ሌሎች የሳተላይት መርሀ ግብሮች ብዙውን ጊዜ የእነዚህን አካባቢዎች ፍላጎቶች አያሟሉም።ብሪታንያ የሚገኘው የፖርትስማውዝ ዩኒቨርሲቲ፣ የስፔስ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ፣የሆኑት ኦሉጉቤኛ ኦሉሞዲሙ እንደሚሉት የአፍሪቃን ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ መረጃ ያስፈልጋል።«አፍሪካ በአብዛኛው በምድር ወገብ ዙሪያ ነው ያለው።.ስለዚህ፣ በዋናነት ከምድር ወገብ አካባቢ ጋር በጣም የሚገናኝ ሳይንስ አለ። ከከፍተኛ ኬክሮስ ዘርፍ በጣም የተለየ ነው። ስለዚህ፣ እዚህ ጋር የሰራኋቸው አንዳንድ መሳሪያዎች በአፍሪካ ተመሳሳይ ነገር ለመድገም ከሞከርኩ አይሰራም። ምክንያቱም የጠፈር የአየር ሁኔታ በምድር ወገብ አከባቢዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ለምድር ዋልታ ቅርብ ከሆኑ አካባቢዎች ጋር ሲነፃጸር ሁኔታው የተለየ ነው። ስለዚህ የምድር ወገብ ላይ ያተኮረ ፊዚክስ መመርኮዝ አለብኝ። ባለሙያ ብትሆን እንኳ የምታውቀውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ። ምን እንደሚሰሩ መረዳት አለብህ።» ሲሉ ገልፀዋል።ሁሉን አቀፍ መረጃ ካለ በአፍሪቃ ቴክኖሎጂውን ለመተግበር ቀላል ነውም ይላሉ ባለሙያው።«እየሰራን ያለነው በአንድ አይነት መለኪያ ሊሰራ የሚችል ሳተላይት የማዘጋጀት ሀሳብ ላይ ነው። በከፍተኛ ፣ በመካከለኛ ኬክሮስ እና በኢኳቶሪያል ክልል ውስጥ ያለውን የህዋ የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ በተመሳሳይ ጊዜ ሊለካ ይችላል። እንደዚህ አይነት ዊሂብ ካለን፤ ዓለማቀፋዊ ሳይንስ የምንለውን መተግበር ቀላል ነው።» በማለት ገልፀዋል።
በአፍሪካ የጠፈር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያሉ ተግዳሮቶች
የጠፈር ቴክኖሎጂ በዚህ ሁኔታ በአፍሪቃ ትልቅ ጥቅም ቢኖረውም ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ በርካታ መሰናክሎች አሉ።ከነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ወጪ፡ ሳተላይቶችን ለመክፈት እና የጠፈር ኘሮግራሞችን ለመገንባት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም በጀት ውስን ለሆኑ ሀገራት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
እንደ ኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ፣ የሳተላይት መረጃ ትንተና ሌሎች ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች የሰለጠኑ የባለሙያዎች እጥረትም ሌላው መሰናክል ነው።የመሠረተ ልማት ውሱንነት፡ የሳተላይት መረጃን ለመተንተን እና ለመጠቀም የኢንተርኔት መዳረሻ እና የውሂብ ማዕከላትን የመሳሰሉ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች አለመኖር እና በውጪ መረጃ ላይ ጥገኛ መሆን ተደራሽነትን ሊገድብ ይችላል።የፖሊሲ እና የማስተባበር ጉዳዮች በተመለከተም፤ ጠንካራ ብሔራዊ የጠፈር ፖሊሲዎች ወይም የአፍሪካ አገሮች ትብብር ከሌለ ዕድገቱ አዝጋሚ እና የተበታተነ ሊሆን ይችላል።
የአህጉሪቱ አወንታዊ እርምጃዎች
ምንም እንኳ በአህጉሪቱ እነዚህን መሰል ተግዳሮቶች ቢኖሩም አዎንታዊ ምልክቶችም አሉ።እንደ ባለሙያው በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ነገሮች እየተሰሩ እ ነው። «በናይጄሪያ የመጀመሪያውን የናይጄሪያ የመገናኛ ሳተላይት ስንጀምር የተወሰነው ስራ በሱሪ ሳተላይት ሴንተር ተሰርቷል። እና የማምጠቁ ስራ የተከናወነው ኤዥያ ነው። አሁን ግን በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ብዙ ነገር እየተካሄደ ነው።ኬንያ ለመሬት ምልከታ የራሷን ሳተላይት ልታጥቅ ነው፣ ወይም ለምሳሌ ናይጄሪያ በሚገኘው አኩሬ የፌደራል ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ቡድን ኪዩብ ሳት ሰርተዋል።»ብለዋል።ከዚህ ባሻገር እንደ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የራሳቸውን ሳተላይት አምጥቀዋል።አፍሪቃውያን ብሔራዊ የጠፈር ኤጀንሲዎችን እየገነቡ ነው። የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ዙሪያ ትብብር እና መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማበረታታት የአፍሪካን የጠፈር ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አፅድቋል።ባለፈው ሚያዚያ 2025 ዓ/ም በግብፅ ካይሮ የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ኤጀንሲ ዋና ቢሮ ተከፍቷል።
መወሰድ ያለባቸው ርምጃዎች
ያም ሆኖ ፤ከጠፈር ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን የአፍሪካ ሀገራት አዳዲስ የጠፈር ሳይንቲስቶችን እና መሐንዲሶችን ለማሰልጠን ትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይጠበቅባቸዋል። የሳተላይት መረጃን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማግኘት፣ ለመተንተን እና ለመጠቀም የአካባቢ መሠረተ ልማትን ማዳበር፣ሀብት እና እውቀትን ለመጋራት አካባቢያዊ ትብብርን ማሳደግ ያስፈልጋል።የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የገንዘብ እና ስልጠና ድጋፍ ለማግኘት ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አጋርነትን መመስረትም ወሳኝ ነው።አዲሱ የአፍሪቃ የጠፈር ኤጀንሲም አህጉሪቱን ያግዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። በአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ የአፍሪካ የውጭ ግንኙነት ባለሙያ ቶማስ ቫይሰንበርግ እንደሚሉት የጠፈር ምርምርን በተመለከተ በአውሮፓ እና በአፍሪቃ መካከል የቆየ ትብብር አለ። ለአፍሪቃ ግን ተግዳሮቱ ቀላል አይደለም ይላሉ።«በተለይ ከ5 እና 8 ዓመታት ወዲህ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል ትብብሩ እየተጠናከረ መጥቷል።ጂኦፖለቲካዊ ምክንያቶች እንዲሁ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።ዛሬ የአፍሪካ የጠፈር ኤጀንሲ እንዴት እንደሚያድግ ትንሽ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ምክንያቱም በአፍሪካ ቀላል አይደለም። አፍሪካ ከአውሮፓ የበለጠ ውስብስብ ነች።»በማለት ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የጠፈር ቴክኖሎጂ ችግሮችን ለመፍታት፣ ሰዎችን ለማብቃት እና ቀጣይነት ያለው የወደፊት እቅድ ለማውጣት ጠቃሚ ነው።በትክክለኛ መዋዕለ ንዋይ፣ ትብብር እና ራዕይ፣ ከተመራ ደግሞ ቴክኖሎጂው አፍሪካ የልማት ግቦቿን እንድታሳካ ብቻ ሳይሆን ወደ አዲስ የፈጠራ ዘመን እንድትሻገር ሊያግዝ ይችላል።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሐመድ