የጠ/ሚው እንታረቅ ጥሪ፤ ውጥረት በአማራና ትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች
ዓርብ፣ የካቲት 15 2016ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ፦ በአማራ ክልል የተፈጠርውን የሰላም እጦት በሰላም፣ በእርቅና በውይይት ለመፍታት መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን መግለጣቸው የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል ። በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጡ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር አስተያየቶችን አሰባስበናል ። በሰሜን ኢትዮጵያ፦ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ብቻ ተደጋጋሚ ግጭቶች መስተዋላቸውም ተዘግቧል ። ይህንንም የሚመለከቱ አስተያየቶችን ቃኝተናል ። የሶማሊያ ፕሬዚደንት በአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ደረሰብኝ ስላሉት መጉላላት እና የመንግሥት ምላሽን የሚዳስሱ አስተያየቶችንም ተመልክተናል ።
የጠ/ሚው እንታረቅ ጥሪ
ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ፦ በአማራ ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር በተመለከተ ከሰሞኑ ሲናገሩ፦ «ይቅርታ ብለን፣ ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን፣ እንታረቅ፣ እንስማማ» ሲሉ ተደምጠዋል ።
እንዳሽ አክሊሉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «በአንድ ሳምንት ግዳጅ ጨርሰን ሪፖርት ለምክር ቤቱ እናቀርባለን ብለውም አልነበር?» ሲሉ በጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ላይ ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰንዝረዋል ። «ስድስት ወር ጨርሰው ተጨማሪ አራት ወር የክልሉን ሕዝብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ነጥቆ በንፁሐን ሕዝብ ላይ በዚህ በተወደደ ኑሮ ላይ እንዳይሠራ ካገዱና የሚችሉትን ሕዝብ ጨፍጭፈው ሲያበቁ እንታረቅ ማለት የእውነት ለሰከንድ ቆም ብሎ ለሚያስብ ማንኛውም ሰው ምን አይነት ስሜት ይፈጥር ይሆን?» ሲሉም ጥያቄ አስፍረዋል ።
አማራ ክልል ዛሬም ከግጭት እና ጦርነት አልተላቀቀም ። የፌዴራሉ መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት ከሁለት ዓመት ግድም በፊት በጋራ እያካሄድን ነው ባሉት «የሕግ ማስከበር ርምጃ» መጀመሪያ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ታሰሩ ። ከዚያም አማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋ ደግሞ ባለፈው ነሐሴ ወር የተከፈተው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው ።
«እኔ ችግር የለብኝም ። ደስ ይለኛል» አሉ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በሰሞኑ ንግግራቸው ። «ሰላም ነው የምፈልገው ። በውስጣችን ያለውን ጉዳይ ብንፈታ ጥሩ ነው» ሲሉም አክለዋል ጠቅላይ ሚንሥትሩ ። ይህን ያሉት ባለፈው ሰኞ ከአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ከተባሉ አካላላት ጋር በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በተወያዩበት ወቅት መሆኑ ተዘግቧል ።
የጠቅላይ ሚንሥትሩን ንግግር በተመለከተ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ላይ ከተሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶች መካከል፦ አበበ ጩፋ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ጦርነትና ግጭት ውድመት እንጂ ልማት አያመጣም ። ሰላም ለአማራ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ» ሲሉ ጽፈዋል ።
«ከልብ የመነጨ ፍላጎት አይመስለኝም ።» ይህ ደግሞ ኤም ጂ ዜድ ፋክት በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ የተሰጠ አስተያየት ነው ። ሌላኛው ፋ ኢኤስ በሚል ስም አስተያየት ሰጪ ደግሞ፦ «ምን ያጠራጥራችኋል? እንታረቅ ማለት ምንድነዉ ችግሩ? የሚፈልጉት መስፈርት ማስቀመጥ ነዉ እንጂ» ብለዋል።
ሰለሞን ፋንቱ፦ «እቺ ውይይት እኮ መሆን የነበረባት ወደ ጫካ ከመግባታቸው በፊት በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄያችን ይመለስ ብለው የወጡ ሰዓት ነበር ። አሁን ግን መወያየት ካለብህም መደራደር ካለብህም ከጫካዎቹ ነው እንጂ እነኚማ እኮ ማስተዳደር ስላልቻሉ በወታደራዊ እየተዳደረ ነው » ሲሉ ለጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የፌስቡክ ጽሑፍ ምላሽ ሰጥተዋል ።
ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ በአጭሩ «እጅግ ዘግይቷል» ሲሉ የጻፉት ደግሞ ዮሐንስ ኃይለሚካኤል ናቸው ። ጆኒ ኤም፦ «በተግባርም እየሆነ ያለው ትናንትና በድንፋታ ተወጥረው ‘ሰብረነዋል'፣ 'ያልቅሱ መሀረብ ስጧቸው' ሲሉ የነበሩት ዛሬ ክፉ ምት ሲያርፍባቸው ካሳ ከፍለን እንታረቅ እያሉ ነው » ብለዋል ። እዮብ ኃይለማርያም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦«ሰላም ይወርድ ዘንድ ምኞቴ እና ጸሎቴ ነው። መልካም እድል» ብለዋል ።
ግጭት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ታጣቂዎች
ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ሳምንት ከአማራ ክልል ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የመሬት ውዝግብን በተመለከተም ከዚህ ቀደም ሕዝቡን ለማወያየት ኮሚቴ አዋቅረው ወልቃይትና ራያ መላካቸውን ገልጠዋል ። «ሕዝብ አወያይተው መጥተው፤ ትክክል ነው መፍትኄው ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብቱ ተረጋግጦለት፤ ወስኖ እራሱን በራሱ ማስተዳደር ነው የሚል ምላሽ አመጡ» ሲሉም የኮሚቴው ምላሽ ያሉትን በንግግራቸው አሰምተዋል ።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ የካቲት 6 እና 7 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በትግራይ እና አማራ ክልሎች አወዛጋቢ ቦታዎች ላይ ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ተዘግቧል ። ግጭቱ አማራና ትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው ራያ ባላ፣ ራያ አላማጣና ወፍላ አካባቢዎች መሆኑም ተገልጧል ። እዛው ራያ አካባቢ ዛታ ኦፍላ በተባለ ወረዳም ረቡዕ የካቲት 13 ዕለት ለአጭር ጊዜ የቆየ ግጭት በትግራይ ኃይሎች እና በአማራ ክልል ታጣቂዎች መካከል ተቀስቅሶ እንደነበረም ተዘግቧል ።
«ከአሁን በኋላ አማራና ትግራይ በጦርነት ከተፈላለግን የመጨረሻ የጅል ጅል መሆናችን ይሰማኛል» ሲሉ የጻፉት ሞላ ተስፋዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። «አገራዊ ሰላም ለመፍጠር መስዋዕት የሚሆን ትውልድ ጠፋ ። ብቻ በየቀኑ የመሣርያ ድምፅ፤ መንገድ መዝጋት፤ ሰው እንዳይቀሳቀስ ማገድ ብቻ» ሲሉ ቁጭታቸውን የገለጹት ደግሞ አባዲወልደገብርኤል ምስግና የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ናቸው ።
ሃሳብ ሃይል ነው በሚል ሌላ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በሰጡት አስተያየት፦ «የአማራና ትግራይ ኢሊቶች ብልህነት ይጠበቃል። ሁለቱ ክልሎች ዳግም ግጭት ውስጥ መግባት የሚጎዳው ሁለቱን ሕዝቦች እንጂ ስርአቱን አይደለም» ብለዋል ።
የሶማሊያ ፕሬዚደንትና የኢትዮጵያ መንግሥት ውዝግብ
ሌላው በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ውስጥ ገጠማቸው የተባለው ነው ። ፕሬዚደንቱ በ37ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳይገቡ በኢትዮጵያ የፀጥታ አስከባሪዎች ተከልክለው ነበር ሲል የሶማሊያ መንግሥት ገልጧል ። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ያቀረቡት ክስ «የአንዳንድ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ለመሳብ» የተደረገ ሙከራ ሲል አጣጥሏል ።
«እዉነት ከሆነ እንግዳ ወደ ቤትህ ሲመጣ ግርግር የምትፈጥር ከሆንክ በዓለም አደባባይ ቀለህ ትቀራለህ» ሲሉ የጻፉት አኪሊ አስክ ናቸው ። ጥላሁን ጌታቸው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «የሱማሊያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማች ናቸዉ። የሱማሊያ መንግስት የሚያቀርበዉ ክስ ትክክል አይደለም ። ሱማሊያ በጣም ሰፊ የባህር በር ስላላት እሷም ብትሰጠን አብረን እንጠቀም ነበር ። ዉይይቱን ከሚሸሽ» ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ ደረሰብኝ ባሉት ወከባ የተነሳ ስብሰባውን አቋርጠው ወደ ሶማሊያ የበረሩት ወዲያው ነበር ። ባሕረ እስማኤል፦ «ስለ ወደቡ ምንም ሳይናገር ተመለሰ » ብለዋል ። ጽሑፋቸውን በሳቅ ምልክት አጅበዋል ። ሞሐመድ ዓሊ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «በተቻለ መጠን ከጎረቤቶቻችን ጋር መልካም ግንኙነት ቢኖርን ጥሩ ነው » ብለዋል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ