1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚ ዐቢይ ጥሪ ለትግራይ ወጣቶች

ዓርብ፣ ኅዳር 24 2014

ጠ/ሚ ዐቢይ «ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት የተሰለፉ ሁሉ» እጃቸውን በሰላም በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ ጠይቀዋል። «የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ ብለው እንዲጠይቁም»አሳስበዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡት አስተያየቶች አብዛኛዎቹ ጥሪውን የሚደግፉ ናቸው።ዘግይቷል፤ፋይዳም የለው ያሉም አልጠፉም።

Äthiopien China Außenminister Wang Yi
ምስል Seyoum Getu/DW

የህዳር 24 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

ጦር ግንባር ከሄዱ ሳምንት ያለፋቸው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ለትግራይ ወጣቶችና እናቶች ያስተላለፉት ጥሪ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ካነጋገሩ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ ነበር።የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ በዚሁ ጥሪያቸው «ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት የተሰለፉ ሁሉ» እጃቸውን በሰላም በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ ጠይቀዋል። «የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ ብለው እንዲጠይቁም»አሳስበዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡት አስተያየቶች አብዛኛዎቹ ጥሪውን የሚደግፉ ናቸው።ዘግይቷል፤ፋይዳም የለው ያሉም አልጠፉም። «መግደል መሸነፍ ነው።»የሚሊት ኢሳያስ ታደሰ ለሠላም ዕድል መሰጠቱ ተገቢ ነው ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው ሲሉ መክረዋል በፌስቡክ በሰጡት አስተያየት ። ዝምታ ነው መልሴ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ አስተያየትም «አዎ ከእናትና አባታቸው እየተነጠቁ ወደ እሳት ለተማገዱ የትግራይ ወጣቶች ትልቅ እድል ነው ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው ይላል። «አዲስ አበባ ላይም ቁጭ ብሎ እኮ እጅ ስጡ ማለት ይቻል ነበር ። ጥሪ ለማስተላለፍ ለምን መዝመት አስፈለገ?» ሲሉ ወርቅነህ ጌትዬ ከቡልጋሪያ ማዞሪያ ጠይቀዋል። « ወርቅነህ ጌትዬ !፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦር ግንባር ያየውን አይቶ ነው። ስለዚህ ትክክል ነው ለምን ሰው ይሞታል ሲሉ ሪቭ ቴክ ታደሰ በፌስቡክ መልስ ሰጥተዋቸዋል።መላኩ ማሞም ተመሳሳይ ሃሳብ ሰጥተዋል።«የትግራይ ወጣቶችም ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን ናቸውና እንዳይሞቱ በሚል ነው። የትግራይም ወጣቶች ምዕራባዊያኑ በአካል እንደማይደርሱላቸው ተረድተው የመጨረሻው መጨረሻ የሆነውን ይህን ዕድል ሊጠቀሙ ይገባል። ማምለጥ የሌለበት ዕድል ነው። በማለት ጥሪውን አጠናክረዋል። እፍሬም አርባ ግን ሌላ መፍትሄ እንዲፈለግ ነው ሃሳብ ያቀረቡት «ይገርማል! ሰዉ ካለቀ ቡኋላ እጅ ቢሰጥ ባይሰጥ ምንም ትርጉም የለውም።ከዚህ ቡኋላ ሌላ ሰዉ ምናድንበት መንገድ ብንፈልግ ነዉ የሚሻለዉ ይላሉ።ገነት ክፍሌ ደግሞ «እኔ አይገባኝም ሲጀመር ወላጆችም እኮ ግምባር ላይ ናቸው ለማን ነው ሚነገረው ሚችለው በግምባር ማይችለው በፕሮፖጋንዳ ተሰልፏል እኮ ሲሉ እኔው ነኝ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ « እንደሰማነው ብዙዎቹ እናት አባታቸው እንዳይታሰሩባቸው እና እንዳይንገላቱ ብለው ተገደው የገቡ አሉ። በሰውኛ ማሰብ ሚችሉ ከሆነ በስተመጨረሻ እንኳን የቀሩትን የትግራይ ወጣት ለማዳን የነ ጌታቸው ረዳ ቡድን ይህንን ጥሪ ይጠቀምበት ሲል ያሳስባል። «እኔ እምለዉ ጦርነቱ ማ ከማን ጋ ነዉ? የሚለውን ጥያቄ ያስቀደሙት ሊሎ አሞራ «አኔ በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር ቢኖር ወንድምና ወንድም እየተጋደለ በለዉ ግፉ የምንለዉ ኣኮ ለዉጭ ወራሪ አይደለም ስለዚህ ወደ ፈጣሪ መጮህ ይሻላል እንጂ ጦርነት አይጠቅመንም ወገኖቼ ፈጣሪ በቃቹ ይበለን አሜን ሰላሙን ያዉርድልን ብለዋል። 
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ የኢትዮጵያ ጉብኝት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን የተለያዩ አስተያየቶችን ካስተናገዱ የሰሞኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። ጦርነት በሚካሄድበት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን የጎበኙት ዋንግ ይ  በኢትዮጵያ የሚደረግ ማናቸውንም ጣልቃ ገብነት ቻይና እንደምትቃወም አስታውቀዋል።ሚኒስትሩ «ቻይና እንደ ወዳጅ ሀገር በኢትዮጵያ ያለውን ኹኔታ በቅርበት እንደምትከታተል» እንዲሁም «በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚደረጉ የውጭ ኃይላት ሙከራዎችን ትቃወማለች ብለዋል። ቻይና «ዜጎችን ከአዲስ አበባ አስወጡ የሚለውን ጥሪ በጭፍን» እንደማትቀበልም ማሳወቃቸውን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። ሚኒስትሩን ተቀብለው ያስተናገዱት የኢትዮጵያው አቻቸው ደመቀ መኮንን ዋናግ ይ «አዲስ አበባ በአሸባሪ ኃይላት ተከባለች፤ የጸጥታዋ ሁኔታም ተባብሷል» ተብሎ የተነዛውን መሰረተ ቢስ ንግግር ችላ ብለው አዲስ አበባ በመምጣታቸው አመስግነዋለቸዋል። ብርሃኑ ሽፈራው ሀሳናም በፌስቡክ አጭር ምስጋና አቅርበዋል።«የችግር ቀን ደራሽዎች ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን ቻይና። ሲሉ ገበያው ካሳ ደግሞ «ቻይና ውለታ ቢስ አደለችም አለም በሩን ዘግቶ እቤቱ ቁጭ ባለበት በመጥፎዉ ቀን ኢትዮጵያ አሮፕላኗን አዘጋጅታ ጥንቃቄ በተሞላበት ለቻይና አለሁልሽ ከጎንሽ ነኝ ስትል አጋርነቷን ማሳየቷ አይዘነጋም። እምየ ኢትዮጵያ ስትታመም ምዕራባውያን  ሲነክሷት በቃ ብላ መርዝ ለመንቀል ከጎናችን ተሰልፋለች ። በማለት ቻይና ከኢትዮጵያ ጎን መቆምዋን አድንቀዋል። አብነት ውበሽት ደግሞ «ከአዲስ አበባ ውጡ ስትል የነበረው አሜሪካ ምን አለች ይሆን»ሲሉ ጠይቀዋል። የሞሀመድ ኦስማን አጭር መልዕክት ደግሞ «ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ » ይላል። ሰላም እግዚ በተቃራኒው የቻይናን ስራ አሳፋሪ ሲሉ ኮንነው ዋናው ዓላማዋ በስግብግብነት ገንዘብ ማጋበስ ነው።ሰብዓዊነት የላትም ሲሉ ድርጊቷን አጣጥለዋል። እዮብ ጥበበ ግን «እውነተኛ ወዳጅ እሚለየው በንደዚ አይነት ጊዜነው እናመሰግናለን ሲሉ ቻይናን አወድሰዋል። 
«በኢትዮጵያ ላይ ለማሴር ኬኒያ ይመላለሳሉ» ሲሉ የአሜሪካ ባለስልጣናትን የሚከሱት ኃይሉ ደነቀ  በበኩላቸው የቻይና ባለስልጣናት ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር ኢትዮጵያ ይመላለሳሉ።ልዩነቱ ሰፊ ነው ብለዋል። ሞገስ መሰለ ግን የተለየ ሃሳብ ነው ያላቸው «ትናንት ኤርትራን ዛሬ ቻይናን እያስገባችሁ አስወርሩን ነገ ደሞ ማንን ልትጎትቱ ይሆን ?» ሲሉ ይጠይቃሉ።«አገራችን ኢትዮጵያ በጥቂቱ ሰጥተው ብዙ ስገዱልን ብንረግጣችሁም ባላየ እለፉ ከሚሉን አሜሪካና ምዕራባውያን ፊቷን ወደ ሰጥቶ መቀበል መርህን ከሚያቀነቅኑት ቻይናና ሩሲያ እንዲሁም ቱርክ ጋር የበለጠ ለመወዳጀት እየተገደደች ይመስለኛል "ያሉት ደግሞ ኢታኤ ኢብራሂም ናቸው ። 
ሌላው በማኅበራዊ መገናና ብዙሀን በርካቶች አስተያየት የሰጡበት ጉዳይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጾቻቸው እስከ ታኅሣስ 29 ድረስ በመላው ዓለም የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሀገር ቤት እንዲገቡ ያቀረቡት ጥሪ ነው። «የኢትዮጵያውያን ታላቁ ወደ ሀገር ቤት ጉዞ» በሚል የቀረበው ጥሪ የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ በአንዳንድ አካላት እንደሚገለጸው የሚያሰጋ እንዳልሆነ ማሳያ መሆኑን  የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል። 
መርትቻ ደታቦር በፌስቡክ መልካም ሓሳብ ነው፣ ካሉ በኋላ ግን ጊዜው ጥቂት ቀረበ ብለዋል። ጥሪው ጥሩ ነው ምንም ክፋት የለውም የሚሉት ቢንያም በላይ  ግን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የሚለው " አዲስ አበባን " እንዲጎበኙ በሚለው መቀየር አለበት ባይ ነኝ ይላሉ። ዲ ኤስ ኬ ማርኩስ ጥሪው መልካም ሆኖ ሳለ ዳያስፖራው ከጉዞው የሚያተርፈው ምንድን ነው? ሲሉ ጠይቀው ፣ላሊበላ ነፃ መውጣቷ ተሰምቷል ግን ክርስቲያኑ ልደትን ሲያከብር ችግር እንዳይገጥመው ምን ያህል ዝግጅት ተደርጎል? የጥሪው ዝርዝር ሃሳቦች ቢታወቁ መልካም ነው የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።
ጆን ቡርኖ ጣሰው በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ይህ እቅድ በደንብ የታሰበበት አይደለም በማለት ይጀምራል።«አንድ ሚሊዮን ሰዎች እስከ ታኅሳስ 29 ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚጠይቀው ይህ ጥሪ ከዚህ ቀደም ሲል መተላለፍ ነበረበት ምናልባትም ከ6 ወር በፊት ።ይህን ያህል ሰው ማጓጓዝ የሚያስችል በቂ በረራ የለንም። ይላል 
አሚር ቻካ፣« አዲስ አበባ ፣ የህዝብ መጨናነቅ ሊያጋጥም መቻሉስ ታስቦበታል? መቼም ዲያስፖራ ለተወሰነ ጊዜ ቆይታ ምርጫው አዲስ አበባ መሆኑ የሚታወቅ ነገር ነው።» ሲሉ ጠይቀዋል።
ጆናታን ከተማ ከጥሪው ጋር አብሮ መታሰብ ያለበት ጉዳይ እንዳለ ጠቁመዋል« ሲቃወሙ የነበሩ ሊታሰሩ ይችላሉ። ስለዚህ መጀመርያ ለሁሉም ዲያስፖራ ይቅርታ መደረግ አለበት !» በሚለው ማሳሳቢያቸው ።
ራህመት ሰኢድ ከዚህ ጥሪ ይልቅ መቅደም ያለበት ጉዳይ አለ ይላሉ« እስኪ መጀመሪያ በሳኡዲ እስር ቤት ለሚሰቃዩ ወንድም እህቶች ቅድሚያ እድል ይሰጣቸው ፍትህ ፍትህ »

ምስል Seyoum Getu/DW
ምስል Ethiopian Prime Minister's Office//AA/picture alliance

ኂሩት መለሰ 

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW