1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጡት ካንሰርን አስቀድሞ በማወቅ መታከም

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 2015

ዕድሜ፣ የዘረመል ለውጦች፣ የቅርብ ቤተሰብ ተጋላጭነት፣ የአመጋገብ ሁኔታ፤ የአልክሆል መጠጥ እንዲሁም የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ለጡት ካንሰር ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ጡት ላይ የሚታዩ ለውጦችን በመከታተል ፈጥኖ ወደ ህክምና መሄድም የመዳን ዕድልን እንደሚያሰፋው የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

Symbolbild Brustkrebs Untersuchung
ምስል Bo Valentino/Zoonar/picture alliance

ጤና እና አካባቢ

This browser does not support the audio element.

በአዳማ ሆስፒታል ስለካንሰር ህመም እና በህክምና መዳን ስለመቻሉ ማኅበረሰቡ በእርስ በርስ የመማማሪያ መድረክ ግንዛቤ እንዲኖረው የተደረገው ጥረት ለሌሎችም አርአያ ስለመሆኑ ባለፈው ማንሳታችን ይታወሳል። የዚህ ጥረት ፋና ወጊ የሆኑት በሆስፒታሉ ሜዲካል ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ቢንያም ተፈራ የማማሪያ መድረኩን ለማመቻቸት ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው ነበር ምላሻቸውን ለዛሬ የቀጠርነው። ዶክተር ቢንያም ለታማሚዎቻቸው መድኃኒት ጽፈው ከማሰናበት አልፈው ችግራቸውን ለመረዳት ሞክረዋል።  

ዶክተር ቢንያም እንደነገሩን ትዳሩ የፈረሰ፣ ቤቱን የሸጠ ሁሉ በዚህ መድረክ በመገኘቱ በተዛባ አመለካከት እና በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የጡት ካንሰር የብዙዎች ኑሮ እንዳናጋ ተረዱ። ከዚህ በመነሳትም እንደ አንድ የህክምናው አካል አድርገው ሊቀጥሉበት ወሰኑ። ጥቂት የማይባሉ ወገኖችም በተመቻቸላቸው መድረክ አንዳቸው ከሌላቸው የህይወት ተሞክሮ መማማር ጀመሩ። 

በአዳማ ሆስፒታል ስለጡት ካንሰር የመማማሪያ መድረክ ተሳታፊዎች በከፊልምስል Biruck Habtamu/Adama University Hospital

ተሞክሯቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካ ላይ በተካሄደው 10ኛው የካንሰር ሀኪሞች ጉባኤ መቅረቡን በሀገር ውስጥም በዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘቱንም ገልጸውልናል። ዶክተር ቢንያም በሚሠሩት የአዳማ ሆስፒታል ከካንሰር ታማሚዎች የጡት ካንሰር ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ነው የሚናገሩት። በየወሩ በሚካሄደው የአቻ ላቻ መማማሪያ መድረክም በህክምና ላይ ያሉም ሆኑ ታክመው የዳኑ 50 የሚደርሱ ወገኖች ይሳተፋሉ። የካንሰር ህክምናን አስቸጋሪ የሚያደርገው የታማሚዎች ዘግይተው ወደ ሀኪም መሄዳቸው እንደሆነ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ይናገራሉ። በመማማሪያው መድረክ እራሳቸው በዚህ የህክምና ሂደት ያለፉ ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነት ለውጥ እንዲመጣ እየረዳ ነው ይላሉ ዶክተር ቢንያም።

ፒንክ ሎተስ፤ ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ ለመስጠት ወይዘሮ ሜሮን ከተባባሪዎቻቸው ጋር ያቋቋሙት የመማማሪያ መድረክ

በህክምናው ሂደት አልፈው ከዳኑት አንዷ ወይዘሮ ሜሮን ከበደ ቀደም ብለው እንዲህ ያለውን የአቻ ላቻ መነጋገሪያ መድረክ ለማቋቋምም ሆነ ሌሎች ከእሳቸው ተሞክሩ እንዲማሩ እየሠሩ ነው። ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ከሚተባበራቸው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመሆን ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ሴቶች የጡት ካንሰር ምርመራ ማድረግ የቻሉበትን ዘመቻ ማካሄዳቸውንም ገልጸውልናል። በአዳማ ሆስፒታልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ስለጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መጀመሩን አበረታች ይሉታል። አዳማ ሆስፒታልን ተሞክሮ መነሻ አድርጎ ለማኅበረሰቡ የመማማሪያ መድረክን ያመቻቸው በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የህይወት ፋና ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ባለሙያው ዶክተር ብሩክ ሀብታሙም ታማሚዎች እርስ በርስ በስነልቡና እንዲደጋገፉ አይነተኛ መድረክነቱን አጽንኦት ይሰጣሉ። ለህክምናውም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አላቸው።

በህይወት ፋና አጠቃላይ ሀኪም ቤት የካንሰር ህክምና ማዕከል ምስል Messay Teklu/DW

ዶክተር ብሩክ እንደገለጹልን በካንሰር ማዕከሉ ውስጥ ወደ ሁለት ሺህ ገደማ ታካሚዎች አሏቸው። ካሉት የካንሰር ታማሚዎች ደግሞ ብዙሃኑ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የጡት ካንሰር ታማሚዎችም ሆነ የሌላ ካንሰር ታማሚዎች ቁጥር በርክቶ ለመታየቱ የምርመራው ስልት መሻሻል ውጤት ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ብሩክ ይገምታሉ። የአኗኗር ዘይቤ እና አበላል ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ያሉት ዶክተር ብሩክ በአንድ ወቅት ኤች አይቪ ተሐዋሲን ለመከላከል የተደረገው አይነት ማኅበራዊ ንቅናቄ ካንሰር ላይም ሊደረግ ይገባልም ባይ ናቸው።

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው የህይወት ፋና ሆስፒታልምስል Messay Teklu/DW

በነገራችን አድማጮች በየዓመቱ የጥቅምት ወርን አስታከን ስለጡት ካንሰር መረጃዎችን ለማካፈል የምንሞክረው ሰዎች ህመሙ በጊዜው ከተደረሰበት ታክሞ መዳን መቻሉን እንዲረዱ ለማስገንዘብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በዚህ በያዝነው የጥቅምት ወር ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ ከመስጠት ጎን ለጎን ምርመራ እንደሚደረግ ተሰምቷል። ከግንዛቤ ማስቀመጫ እንቅስቃሴዎች አንዱ የሆነው የ5000 ሜትር የእግር ጉዞ ከሰሞኑ እንደሚደረግም ለመረዳት ችለናል። 

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW