1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጡት ወተት ባንክ ምንድን ነው?

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰኞ፣ ሰኔ 8 2018

የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ በ2.8 ቢሊየን ብር ወጪ ትናንት በሀዋሳ ለምረቃ ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል የጡት ወተት ባንክ ይገኙበታል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው የተባለው የጡት ወተት ባንክ የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ምጣኔ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ነው በምረቃ ስነሥርዓቱ ላይ የተጠቀሰው።

Mutter beim Stillen
ለጨቅላ ሕጻናት ከእናት ጡት በላይ የሚጠቅም እንደሌለ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ደጋግመው ያሳስባሉ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Olena Mykhaylova/Zoonar/picture alliance

የጡት ወተት ባንክ ምንድን ነው?

This browser does not support the audio element.

 

 የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ በ2.8 ቢሊየን ብር ወጪ ትናንት በሀዋሳ ለምረቃ ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል የጡት ወተት ባንክ ይገኙበታል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው የተባለው የጡት ወተት ባንክ የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ምጣኔ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ነው በምረቃ ስነሥርዓቱ ላይ የተጠቀሰው።

«የጡት ወተት ባንክ በዓለም ላይ የ100 ዓመት ታሪክ አለው» ይላሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ፍፁም ወልደገብርኤል። ነገር ግን ይህ የጤና ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ገቢራዊ መሆን የጀመረው ዘግይቶ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ፍጹም በአፍሪካ እስካሁን በ8 ሃገራት ውስጥ ብቻ አገልግሎቱ እየተሠጠ ይገኛል። ትናንት በሀዋሳ የመጀመሪያውን የጡት ወተት ባንክ በይፋ ሥራ ያስጀመረችው ኢትዮጵያ አገልግሎቱን በማቅረብ ከአፍሪካ ዘጠነኛዋ ሀገር ሆናለች።

የጡት ወተት የመሰብሰቡ ሂደት

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትናንት ካስመረቃቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የጡት ወተት ባንክ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ፍፁም አገልግሎቱ በባህሪው ከደም መለገሥ ጋር እንደሚመሳሰል ገልጸዋል። ወተት የሚለግሱ እናቶች በቅድሚያ ለሕጻኑ በቂ የጡት ወተት መስጠት የሚችሉና ሕጻኑ ከሚፈለገው በላይ በትርፍነት እንዳላቸው የተረጋገጠና ለዚህም ፍቃደኛነታቸውን በፊርም ካረጋገጡ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል።

የተዘጋጀው የእናት ጡት ባንክ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲምስል፦ Hawassa University/DW

ወተት ለጋሽ እናቶች ጥብቅ የጤና እና የደም ምርመራ እንደሚደረግላቸው የጠቀሱት ዶክተር ፍፁም «ወተቱ ከተሰበሰበ በኋላ «PiAstra» በተሰኘዘመናዊ ማሽን በሙቀት የማምከን (Pasteurization) ሂደት ውስጥ ያልፋል። ይህም ተህዋስያንን በማጥፋት ንጥረ ነገሮችን ይጠብቃል። የተሰበሰበው ወተት በእነኚህ ሂደቶች ውስጥ ካለፈ በኋላ በሕክምና ደረጃ በሚዘጋጁ ማቀዝቀዣዎች ውስጥ ተከማችቶ ለሚፈልጉ ሕጻናት ይሰራጫል» ብለዋል።

ባንኩ የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ይታደጋል 

በዓለም ደረጃ የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ስንመለከት አብዛኞቹ ያለቀናቸው በመወለዳቸው ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ የተናገሩት ዶክተር ፍፁም «እነኝህ ጨቅላ ሕጻናት ከሚሞቱባቸው ምክንያቶች አንዱ እንደተወለዱ የምግብ ችግር ሥለሚያጋጥማቸው ነው። አሁን በባንኩ አማካኝነት የአናት ጡት ማግኘት መቻላቸው ከምግብ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የመሞት ዕድላቸውን ከ40 እስከ 30 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል። ምክንያቱም የእናት ጡት ወተት በንጥረ ነገር የበለጸገ ሥለሆነ በቀላሉ በሽታን በመከላከል ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ ነው» ብለዋል።

ትናንት በኮሌጁ ተገንብተው ለምረቃ የበቁትፕሮጀክቶች 2.8 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል። ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል ከጡት ወተት ባንክ በተጨማሪ የቀዶ ሕክምና ማዕከል፣ የጽኑ ህሙማን ሕክምናና እንክብካቤ ፣ የተላላፊፍ በሽታዎች ስርጭት ቁጥጥርና ምርምር ማዕከል እና የኦክስጅንና የተለያዩ ጋዞች ማምረቻ ይገኙባቸዋል። የፌዴራል መንግሥት በመደበው በጀት እና በለጋሽ ሃገራት የቁሳቁስ እና የቴክኒክ ድጋፍ የተገነቡት ፕሮጀክቶች የሲዳማ ክልል እና በዙሪያው የሚገኙ ከፊል የኦሮሚያ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተጠቅሷል።

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW