1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጣናንሽ 2 ጉዞ ለምን አዝጋሚ ሆነ?

ዓለምነው መኮንን
ረቡዕ፣ ሰኔ 25 2017

ጣናንሽ ቁጥር ሁለት በከባድ ተሽከርካሪ ተጭና ከጅቡቲ ወደብ ከተነሳች 3ኛ ወሯን ብታስቆጥርም እስካሁን ከመጨረሻ መዳረሻዋ ባሕር ዳር ከተማ መግባት አልቻለችም። አዲስ አበባ ከተማ የደረሰችው ጣናነሽ፣ ባሕር ዳር ለመግባት ሌላ አንድ ወር ይወስድባታል ተብሏል። የጀልባዋ ጉዞ ለምን አዝጋሚ ሆነ?

ጣና ሐይቅ ከነመጓጓዣዎቹ
ጣና ሐይቅ ከነመጓጓዣዎቹ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የጣናንሽ 2 ጉዞ ለምን አዝጋሚ ሆነ?

This browser does not support the audio element.

 

የጣናነሽ 2 አዝጋሚ ጉዞ

በኢትዮጵያ የባሕር ላይ መጓጓዣ አገልግሎት ከሚሰጡ የውኃ አካላት መካከል በሀገሪቱ በስፋቱ የሚታወቀው የጣና ሐይቅ አንዱ ነው። በሐይቁ ውሰጥ 37 ያክል ደሴቶች ሲኖሩ በ19ኙ ገዳማት ይገኙባቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለቱሪስት መስህብ የሆኑ ጥንታዊ መጽሐፍትና የቀድሞ ነገሥታት አፅም በክብር የተቀመጠባቸው ናቸው።

የደሴቶቹ ነዋሪዎች ከቀሪው የአካባቢ ነዋሪዎች ጋር የሚገናኙት በአብዛኛው በውኃ የመጓጓዣ አገልግሎት ነው። ከ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለሰዎችና ለዕቃ ማጓጓዣ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ከደንገል ተክል (Papyrus) በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጀውና በአካባቢው አጠራር «ታንኳ» የተባለው ባህላዊ መጓጓዣ በዚህ ረገድ አገልግሎቱ ከፍተኛ እንደሆነ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

«ዘመናዊ የጀልባ ጉዞ የተጀመረው በጣሊያን የወረራ ወቅት ነበር» አቶ ደምሰው በንቲ

በጣና ሐይቅ ላይ ዘመናዊ ጀልባዎችን ለመጓጓዣ መጠቀም የተጀመረው ደግሞ በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ ወቅት እንደነበር የገለጹልን በኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ናቸው።

«ጣናነሽና ንጋት የመሳሰሉ የአገር ውሰጥ ጀልባዎች ነበሩ፣ ጀልባዎቹ ምንጫቸው ጣሊያን ነው፣ ጣሊያን በወረራ ወቅት ጀልባዎችን ጣና ላይ ለመጓጓዣ አገልግሎት ትጠቀም ነበር። ወራሪዋ ጣሊያን በአርበኞች ተሽንፋ ስትወጣ ጀልባዎቹን በአንድ ገዳም አካባቢ በጥልቀት ቀብራቸው በመሄዷ ሳይገኙ ቆይተዋል፣ ከጊዜ በኋል በቁፋሮ ተገኝተው ከዚያን ጊዜ ጅምሮ እስካሁን እያገለግሉ ናቸው።» ብለዋል።

አሁን ሥራ ላይ ያሉት የመጓጓዣ ጀልባዎች ጣሊያን ከሀገር ሲወጣ መሬት ቆፍሮ ቀብሯቸው በመሄዱ ለተወሰነ ጊዜ የባሕር ላይ አገልግሎቱ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ጀልባዎቹ ምናልባትም ከ1940ዎቹ ጀምሮ አገልግሎት ላይ መዋል መጀመራቸውን ነው ኃላፊው አቶ ደምሰው የተናገሩት።

ጣናነሽ ሁለት ታላቋ ጀልባ

አሁን ደግሞ እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ ጀልባ በመንግሥት ገዥ ተፈፅሞ በጣና ሐይቅ ላይ አገልግሎት ለመስጠት ከጅቡቲ ወደብ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. «ሎውቤድ» በተባል ከፍተኛ የጪነት ተሽከርካሪ አማካኝት ጉዞዋን በየብስ መጀመሯን አቶ ደምሰው ገልጠዋል። «ጣናነሽ 2» የሚል ስያሜ የተሰጣት ይች ጀልባ ጉዞዋን ከጀመረች ሦስት ወራትን ያስቆጠረች ቢሆንም እስካሁን ከአዲስ አበባ ብዙም ማለፍ እንዳልቻለች አመልክተዋል። አንዳንዶቹ እንዴያውም የጀልባዋን ጉዞ «የዔሊ ጉዞ» በማለት ይተቻሉ።

«በጣና ሐይቅ አሁን ሥራ ላይ ያሉት የመጓጓዣ ጀልባዎች ጣሊያን ከሀገር ሲወጣ መሬት ቆፍሮ ቀብሯቸው በመሄዱ ለተወሰነ ጊዜ የባሕር ላይ አገልግሎቱ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ጀልባዎቹ ምናልባትም ከ1940ዎቹ ጀምሮ አገልግሎት ላይ መዋል መጀመራቸውን ነው ኃላፊው አቶ ደምሰው የተናገሩት።ፎቶ ከማኅደርምስል፦ James Jeffrey

ጣናንሽ ሁለት ጉዞዋ ለምን «ዔሊ እርምጃ» ተባለ?

የጀልባዋ ጉዞ ለምን አልፈጠነም? ስንል አቶ ደምሰውን ጠየቅናቸው፣ አቶ ደምሰው እንዳስረዱን ጀልባዋ እጅግ ግዙፍ በመሆኗ በጉዞዋ ውቅት በመንገድ ላይ የሚስተካክሉ ጉዳዮች እንደነበሩ፣ የሚቆረጡና የሚቀጥሉ የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ለጉዞዋ አስቸጋሪ የነበሩ ተለዋጭ መንገዶች፣ የትራፊክ መጨናነቅና ሌሎችም እንቀፋቶች የጀልባዋን ጉዞ አዘግይቶታል ሲሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የተናገሩት።

ጣናነሽ ሁለት ክብደቷ እስከ 150,000 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ 38 ሜትር ትረዝማለች፣ እስከ 200 ሰዎችም የመጫን አቅም እንዳላት አቶ ደምሰው ገልጠዋል።

ለጉዞ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ስላልመቻሉ

ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን የተናገሩት አቶ ደምሰው፣ የተሻለው አማራጭ ሆኖ የተገኘው ግን ጀልባዋን በከባድ ሎውቤድ ማጓጓዝ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ፈታትቶ ለማጓጓዝ ቢሞከርም ጀልባዋ ካላት ስሪት አኳያ እንዳልተቻለ የተናገሩት አቶ ደምሰው፣ ፈታትቶ ለማጓጓዝ ቢሞከር እንኳ እንደገና የመጀመሪያ ቅርጥጿን ይዘት ማምጣት አይቻልም ብለዋል።  ፈታትቶ መገጣጠም የሚያስችል የተሟላ እውቅትም ያለው ባለሙያም ሆነ ማዕከል አገር ውስጥ እንደሌለም አስረድተዋል። ጣናንሽ ሁለት በጣና ደሴቶች ለሚኖሩ ሰዎች ተጨማሪ የመጓጓዣ አማራጭ እንደምትሆን አቶ ደምሰው ጠቁመው ለአካባቢው የቱሪስት ፍሰት መሳለጥም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖራታል ብለዋል።

ጀልባዋ ባለፈችባቸው ከተሞች ሁሉ የሕዝቡ አቀባበል እጅግ አስደሳችና ደማቅ እንደነበር የተናገሩት አቶ ደምሰው ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። ከአንድ ወር በኋላ ጣናነሽ ሁለት ባሕር ዳር ከተማ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ደምሰው አክለው ገልጸዋል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW